ታህሣሥ ፲፱

እንኳን ለመልአኩ ለቅዱስ ገብርኤል በዓል በሰላም አደረሳች

 

 ቤተክርስቲያናችን ዓመታዊ ሆነ ወርሃዊ በዓላትን ስታከብር ካለ ምክንያት አይደለም፡፡ በመሆኑም የቅዱስ ገብርኤልን በዓል ለምን   እንደምናከብር ከዚህ እንደሚከተለው በጥቂቱ እንማማራለን፡፡ እግዚአብሔር ይጨመርበት፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ታማኝ መልአክ   ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ገብርኤል ማለት የእግዚአብሔርን ልጅ የሚመስል ጌታና አገልጋይ ማለት ነው፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ እጅጉን ተፈሪ እና ተወዳጅ መልአክ ነው፡፡ በስዕለት ሰሚነቱ፣ ብሥራት አብሣሪነቱም የሚመሰገን መልአክ ነው፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችንም የቅዱሳን መላእክት ወርኃዊ በዓላቸውን በጸሎት እና በምስጋና የምታከብር በመሆኗ ታህሣሥ ፲፱ ቀን የብርሃናዊው መልአክ የቅዱስ ገብርኤልን በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከዕቶነ እሳት (ከነደደ እሳት) ማዳኑን ምክንያት በማድረግ ታከብራለች፡፡

 

Read more: ታህሣሥ ፲፱

በዓታ ለማርያም

እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከቅዱስ ኢያቄም ከእናቷ ከቅድስት ሐና “እም ሊባኖስ ትወጽእ መርዓት፡፡” ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ ፯ ቀን ተፀንሰች፡፡ ግንቦት ፩ ቀን ሊባኖስ በምትባል አካባቢ በብጽአት ተወለደች፡፡ እመቤታችን በጾም በጸሎትም የተገኘች ናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኀደረ መለኮት (የእግዚአብሔር ማደሪያ) ሆናለች፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችን በእናት በአባቷ ቤት ፫ ዓመት ተቀመጠች “ከመዝ ነበረት ውስተ ቤተ አቡሃ ወእማ ፫ተ ዓመት እንዘ ትጠቡ ሐሊበ እማ” (እንዳለ በነገረ ማርያም)፡፡ ኢያቄምና ሐናም ልጃቸውን ሲያሳድጉ ስላደረገላቸውም ሁሉ እግዚአብሔርን ፈጽመው እያመሰገኑት ፫ ዓመት ኖሩ በጾም እና በጸሎት ተወስነው ለድሆችና ለጦም አደሮች ምጽዋት እየሰጡ በጐ ሥራን አበዙ፡፡

ልጃቸውን እመቤታችንን በንጽሕና እያሳደጉ ፫ ዓመት በተፈፀመ ጊዜ ቅድስት ሐና የተሳሉትን ስዕለት ለቅዱስ ኢያቄም በማስታወስ ስዕለቱን እንዲፈጽሙ በነገረችው ጊዜ ደስ አለው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ‹‹ልጄ ሆይ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ክርስቶስ ውበትሽን /ንጽሐ ባሕርይሽን/ ወድዷልና›› መዝ 44፡10-11 ብሎ እንደተናገረ ለወላጆቿ የብጽአት ልጅ የሆነችው ድንግል ማርያም ሆዷ ዘመድ ሳይወድ አፏ እህል ሳይለምድ ከእናት ከአባቷ ተለይታ ታህሣሥ ፫ ቀን በ፫ ዓመቷ ወደ መቅደሰ ኦሪት ገብታለች፡፡ 

በዓታ ለማርያም ማለትም “የድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ማለት ነው፡፡” ካህኑ ዘካሪያስም ስለምትመገበው ምግብ በተጨነቀ ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ከሰማያት ወርዶ ፩ ክንፉን ጋርዶ ፩ ክንፉን አጐናጽፎ ኅብስቱን አብልቷት ወይኑን አጠጥቷት የብርሃን ጽዋ እና የብርሃን መሶብ ይዞ ወደ ሰማይ ወጥቷል፡፡ እመቤታችንም ከዚህ በኋላ ኅብስት ሰማያዊ እየተመገበች ስቴ ሕይወት እየጠጣች ከመላአክት ጋር እየተጫወተች ፲፪ ዓመት በቤተ መቅደስ ተቀመጠች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የበላኤ ሰብዕ እመቤት እመቤታችን እኛንም በምልጃዋ ትጎብኘን አሜን

ደብረ ቊስቋም

ደብረ ቊስቋም በደቡብ (ላዕላይ) ግብጽ የምትገኝ ቅድስት ቦታ ናት፡፡ ቊስቋም የሚለው ስያሜ የመጣው ከተራራው በታች በነበረና በጠፋ ቊስቋም ከሚባል ከተማ ነው፡፡ ቊስቋም የሚለው ቃል ቅብጥኛ ሲሆን የሐለፋ (በበረሃ የሚበቅልና እንደ ሰሌን የሚያገለግል) መቃብር ማለት ነው፡፡ ደብረ ቊስቋም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜን ይዛ በስደቷ ጊዜ ያረፈችባት፤ የባረከቻትና የቀደሰቻት ቦታ ናት፡፡ ቦታዋ ደብር (በግእዝ ተራራ ማለት ነው) የተባለችው ቊስቋም በተባለ ተራራ ሥር በመገኘትዋ ነው፡፡ ግብጻውያንም የቊስቋም ተራራ በማለት ይጠሩዋታል፡፡

ቊስቋም ከካይሮ የሚመጣው አስፋልት ትቶ በስተምዕራብ አቅጣጫ የሚገነጠለው መንገድ ላይ 11 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ ይገኛል፡፡ እመቤታችን ጌታችንን ይዛ ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ ደብረ ቊስቋም ስትደርስ ከሚያሳድዷት እጅግ እንደራቀች ስላወቀች ደስ ተሰኝታ ልትቀመጥባት ወሰነች፡፡ ቦታዋም በግብጽ የመጨረሻው ጠረፍ አካባቢ የምትገኝ ነበረች፡፡ በተራራው እግር ሥር የጉድጓድ ውሃ ስለነበር እመቤታችን ጌታችንን በዚያ አጥባዋለች፡፡ ጌታችን በዚህ ውሃ ከታጠበ ጀምሮ ውሃው ስለተቀደሰ ተአምራት የሚያደርግ ሆኖአል፡፡ እመቤታችን ቦታዋ ላይ ክፉ ሰው የሌለበትና ውሃ ያለበት በመሆኑ በዚያ ለመቀመጥ ወሰነች፡፡

Read more: ደብረ ቊስቋም

መርዳት ለምትፈልጉ

ሰንበት ትምህርት ቤታችን ከቅድስት ቤተክርስቲያን የተቀበለውን መንፈሳዊ አደራ ለመወጣትና የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት ከመቼውም በበለጠ ጠንክሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

እርሶም ይህን የሰ/ት/ቤቱን አገልግሎት በገንዘብዎ ለመርዳት ከፈለጉ በዳሽን ባንክ የረር ቅርንጫፍ አካውንት ቁጥር 5008679804004 በማስገባት የበረከቱ ተካፋይ ይሁኑ፡፡

የመስቀል በዓል ደመራ አከባበር 2005

ጾመ ፍልሰታ

‹‹ፍልሰታ›› የሚለው ቃል የእመቤታችንን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሳቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡ የእመቤታችን ትንሣኤ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደውኃ ፈሳሽ የተደረገ ሳይሆን በቅዱሳት መጻሕፍት በትንቢተ ነቢያት የተገለጸ ነው፡፡ ከነቢያት አንዱ ክቡር ዳዊት ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦትም ይላል›› መዝ. 131፥8 በዚህም ፈጣሪዬ ሆይ ምዕመናንን ወደ ምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህ ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሣ አለ፡፡ ታቦት የጽላት ማደሪያ እንደሆነ ሁሉ እመቤታችንም ለክርስቶስ ማደሪያ በመሆኗ አማናዊት ታቦት ትባላለች፡፡
ንጉሥ ሰሎሞንም ‹‹ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነዪ›› መኃ.2፥10  እዚህ ላይ ‹‹ወዳጄ ውበቴ›› የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ምክንያቱም የሰው ዘር በሙሉ በሰይጣን ባርነት ተይዞ በጨለማ በነበረበት ጊዜ ብርሃን ክርስቶስን ያስገኘች የፀሐይ መውጫ በመሆኗ ‹‹ወዳጄ›› ይላታልና፡፡ እመቤታችን በውስጥ፣ በአፍአ፣ በነቢብ፣ በገቢር፣ በሐልዮ ፍጹም ነቅዕ የሌለባት ድንጋሌ ሥጋ ድንጋሌ ነፍስ ድንጋሌ ኅሊና የተባበሩላት በነፍስ በሥጋ በልቡና ንጽሕት ቅድስት ልዩ በመሆኗ ‹‹ውበቴ›› ይላታል፡፡ እንዲህ ሆና በመገኘቷም ለእናትነት መርጧታል፡፡ መርገመ ሔዋን ያልወደቀባት ለአምላክ እናት የተባለች መሆኗን ሲገልጽም እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹በእኔ ዘንድ ሁለንተናሽ ያማረ ነው ምንም ምን ነውር ነቀፋ የለብሽም›› እመቤታችንን በእኔ ዘንድ ሁለንተናሽ ያማረ ነው ገቢረ ኃጢአት የለብሽም›› ነቢብ የለብሽምሐልዮ የለብሽም እንዳላት መናገሩ ነው፡፡ መኃ. 4፥7

Read more: ጾመ ፍልሰታ

Page 15 of 17

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine