ትምህርት

ጾመ ገሃድ/ጋድ

© ሕሊና ዘኆኅተብርሃን

ሰሞኑን ብዙ የክታበ ገጽ / ፌስቡክ / ወዳጆቼ የገሃድ ጾምን፣ ልደትንና ጥምቀትን የተመለከቱ የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ጥያቄዎችን በተደጋጋሚጠይቀውኛል፡፡ በክታበ ገጽ ብቻ ሳይሆን በስልክም በአካልም ከብዙዎች ጋር ተወያይተናል፡፡ በየዓመቱ በዚህ ወቅት ተመሳሳይ ጥያቄዎችበተደጋጋሚ የሚነሡ መሆናቸው ልማድ እየሆነም መጥቷል፡፡ ስለሆነም ለብዙ ወዳጆቼ ቃል እንደገባሁት በጉዳዩ ላይ መጻሕፍትን በማገላበጥይህችን ጽሑፍ አዘጋጅቻለሁ፡፡ ( የተጠቀምኋቸውን መጻሕፍት በግርጌ ማስታወሻ ጠቁሜአለሁ፡፡ )

ጥያቄ፡ - የልደት በዓል የገሃድ ጾም አለውን ? ልደት ረቡዕ በመዋሉ ይጾማልን ?

መልስ፡ - እንደሥርዐተ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ማንኛውም ክርስቲያን ሊጾማቸውየሚገቡ የአዋጅ አጽዋማት 7 ናቸው፡፡ እነዚህም ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ፍልሰታ፣ ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ገሃድ፣ ጾመ ነነዌእና ጾመ ድኅነት ( የዓርብና ረቡዕ ጾም ) ናቸው፡፡ የገሃድ ጾም ከ 7 ቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዱ ነው ማለት ነው፡፡

ስያሜውናትርጉሙ=

“ ገሃድማለት “ ለውጥ፣ ልዋጭ ” ማለት ነው፡፡ … ወይም እንደ ዘይቤው “ ግልጥ ” ማለት ነው፤ “ ይፋ ” ማለት ነው፡፡ በግልጥ፣ በይፋ ሲሉበገሃድ እንዲሉ፡፡ …”[1]

 

ገሃድማለት “ መገለጫ፣ ግልጥ፣ ይፋ ማለት ነው፡፡ ” “ ገሃድ ” የሚለውን “ ጋድ ” ብሎትም ልናገኘው እንችላለን፡፡ ጋድ ማለት “ ለውጥ፣ ልዋጭ ” ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ረቡዕ፣ አርብ ሲውል በዚያ ለውጥ ማክሰኞ፣ ሐሙስ ይጾማልና ጋድ አለው፡፡ [2]

 

“ ገሃድየቃሉ ትርጉም መገለጥ፣ መታየት ነው ”[3]

ገሃድእና ጋድ ከሚለው በተጨማሪ ፍትሐ ነገሥቱ ጾሙን “ ጾመ ድራረ ጥምቀት / ጾመ ድራረ ልደት ” በማለት ጠርቶታል፡፡ “ ድራር ” የሚለውንዲ . ቃኘው ወልዴ ከሥር በተጠቀሰው መጽሐፉ ሲተረጉመው “ ድር እንዲል ትግሬ በጥምቀት ዋዜማ ከምግብ መከልከል ነው፡፡ የሚቆርብ ሰውአክፍሎ የሚያድር ስለሆነም የጥምቀትን ድራር ( ራት ) መጾም ነው፡፡ ” ብሏል፡፡

 

“ ገድ ” የሚለውን ቃል የአቡነ ጎርጎርዮስ “ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ” ፣ የብርሃኑ ጎበና “ ዓምደ ሃይማኖት ” እና “ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት፣ሥርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት ” የሚሉት መጻሕፍት እንዲሁ እንዳለ ይጠቀሙታል፡፡ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ያሳተመው ፍትሐነገሥት እና የዲያቆን ቃኘው ወልዴ “ ጾምና ምጽዋት ” ደግሞ ከ “ ገ ” እና “ ድ ” መካከል ያለችውን ፊደል ራብዕ ሳያደርጉ በግእዙ “ ገድ ” በማለት ጽፈውታል፡፡ የእሥራ ምዕቱ መጽሐፍ ደግሞንባቡን ከአቡነ ጎርጎርዮስ መጽሐፍ ቢወስድም ቃሉን ሲጽፈው ግን ሐመሩ “ ሐ ” ን በመጠቀም “ ገድ ” እያለ አስቀምጦታል፡፡ ( ለዚህ ጽሑፍ ገሃድ ብለን ተጠቅመናል፡፡ )

 

የልደት በዓል ገሃድ አለውን ?

አቡነጎርጎርዮስ በጻፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ “ ገሃድ የጥምቀት ብቻ ነው፤ ጥምቀት ረቡዕና ዓርብ በሚውልበትጊዜ በኋላው የሚገኙት ማክሰኞና ሐሙስ የፍስክ ቀንነታቸው ወደ ጾምነት ተለውጦ ይጾማሉ፡፡ በነሱ ለውጥ ጥምቀት የሚውልባቸው የጾምቀኖች ( ረቡዕና ዓርብ ) የፍስክ ቀን ሁነው ይከበራሉና፡፡ ገሃድ የረቡዕና የዓርብ ለውጥ ነው ብለናል፡፡ ነገር ግን በሌላም ቀንቢውል የጥምቀት ዋዜማ ይጾማል፡፡ ” በማለት ስለ ገሃድ ጾም ገልፀዋል፡፡ ለልደት ገሃድ የሚባለው በልምድ እንደሆነም ሲያብራሩ “ ገሃድለጥምቀት ብቻ ነው፤ በልማድ ግን የልደትንም ዋዜማ ገሃድ እንለዋለን፡፡ ነገር ግን ልደት የሚውልባቸው ዓርብ ወይም ረቡዕ የፍስክቀን ሁነው እንዲከበሩ ቢታዘዙም፤ በዋዜማው የሚገኙት ማክሰኞና ሐሙስ ከጾመ ነቢያት ጋር የተያያዙ ስለሆኑ መጾማቸው የግድ ነው፤የማይጾሙ ሰዎች ግን መላውን ጾመ ነቢያት ሲበሉ ቆይተው ዋዜማውን ብቻ ገሃድ ነው ብለው ይጾማሉ፡፡ ” በማለት ለልደት ገሃድ እንደሌለውናዋዜማው የጾመ ነቢያት እንደሆነ ገልፀው፣ ነገር ግን ከሥርዐት ውጪ ሆነው ጾመ ነቢያትን ሳይጾሙ ቆይተው ገሃድ ብለው የልደትን ዋዜማእንደሚጾሙ ጠቆሙ እንጂ ድርጊታቸው ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን ሳይገልፁ በአሻሚነት ትተውታል፡፡

 

ቤተክርስቲያናችንበቅርብ ጊዜያት ለዚህ ትውልድ እንዲሆኑ አድርጋ ካሳተመቻቸውና እንደ ማጣቀሻ ከሚጠቀሱት መጻሕፍት መካከል ሁለቱ እጅግ ይመሰገናሉ፡፡የመጀመሪያው በሐምሌ 1988 ዓ . ም . “ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ሥርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት /THE ETHIOPIAN ORTHODOX TEWAHEDO CHURCH FAITH, ORDER OF WORSHIP AND ECUMENICALRELATIONS” በሚል ርእስ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የታተመው ሲሆን ሁለተኛው ድግሞ ለእሥራ ምዕት / ሚሊኒየም / በዓል “ የኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ . ም . (2000)” የሚለው ነው፡፡ የእሥራ ምዕቱ መጽሐፍስለ አጽዋማት ባስነበበበት ክፍሉ ስለ ገሃድ ሲገልፅ ሙሉ በሙሉ ከላይ የጠቀስነውን የአቡነ ጎርጎርዮስን ጽሑፍ ያስነበበ ሲሆን ከአንድገጽ በኋላ ግን እንደገና ወደጉዳዩ በመመለስ “ አቡነ ጎርጎርዮስ እንዲህ ቢሉም ፍት መንፈሳዊ ግን ለልደትም ለጥምቀትም ገሃድ እንዳለውያስረዳል ” በማለት ትክክለኛው የቱ እንደሆነ ሳይገልፅ እንዲሁ አሻሚ አድርጎ አልፎታል፡፡ [4] “ የኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ሥርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት ” በሚል ርእስ ቀደም ብሎ የተዘጋጀው መጽሐፍ ደግሞገሃድን በተመለከተ “ ይህ ጾም በልደትና በጥምቀት ዋዜማ የሚጾም ጾም ነው፡፡ ልደትና ጥምቀት ረቡዕና ዓርብ ሲውሉ በሌሊት ስለሚቀደስናስለሚበላ በለውጡ በዋዜማው ሐሙስና ማክሰኞ ይጾማል፤ ይህም ጾም በያመቱ እንዲጾም በቀኖና ቤተክርስቲያን ተወስኗል፡፡ ” በማለት ብቻያልፈዋል፡፡ [5]

 

ብርሃኑጎበና ዓምደ ሃይማኖት በተሰኘው የታወቀ መጽሐፉ ለጥምቀት፣ ለልደት ብሎ ሳይጠቅስ እንዲሁ በደፈናው “ የገሃድ ጾም ጥር 10 ቀንለ 11 አጥቢያ ነው፡፡ ” በማለት ጽፏል፡፡ [6] ዲያቆንቃኘው ወልዴም “ ጾምና ምጽዋት ” በተሰኘው መጽሐፉ የልደት ዋዜማ ምንጊዜም በነቢያት ጾም ውስጥ የሚቆጠር በመሆኑ መጾሙ ግድ እንደሆነአስታውሶ የነቢያትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች ግን መላውን ጾሙን ሲበሉ ቆይተው በዋዜማው ገሃድ ብለው መጾማቸው ስህተት እንደሆነ ይጠቁማል፡፡በመቀጠልም “… ለልደት ገሃድ የለውም፡፡ የጥምቀት ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለጾመ ነቢያት ገሃድ እንዳለው የሚናገሩም አሉ፡፡ለዚህም የሚያቀርቡት ማስረጃ እስከ ምሽት መጾሙን ነው፡፡ ”[7] በማለትለልደት ገሃድ ብለው የሚጾሙ እንዳሉ ጠቅሶ ትክክለኛው የቱ እንደሆነ በማስረገጥ ሳይጠቁም አልፎታል፡፡

 

የቤተክርስቲያናችንየሥርዐት ምንጭ የሆነው ፍትሐ ነገሥትበእንተ ኩሎሙ አጽዋም - ስለጾሞች ሁሉ በሚለው አንቀጽ 15 የሚከተለውን ደንግጓል፡ -

“… ወእምኔሆሙዘይከውን በአምሳለ ጾም ዐባይ በተጠናቅቆ፡፡ ወይእቲ ሰሙነ ሕርቃል ዘትከውን እምቅድመ ጾም ዐቢይ ወጾመ ሰብአ ነነዌ ፫ቱ ዕለታት፡፡ወጾመ ድራረ ልደት ወጾመ ድራረ ጥምቀት፡፡

… ከእነርሱምእንደ ዐቢይ ጾም በመጠንቀቅ የሚሆን አለ፡፡ ይህችውም ከዐቢይ ጾም አስቀድማ የምትሆን የሕርቃል ጾም ናት፡፡ የነነዌ ሰዎች ጾም 3 ቀን፤ የልደትና የጥምቀት ዋዜማ ጾም፤ ( ገሀድ ) ፡፡ ”[8]

ማጠቃለያ

ፍትሐነገሥት የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ምንጭ በመሆኑ እኛም መጽሐፉ እንደሚለው ልንመራ ግድ ነው፡፡ በልማድ የገቡ ብዙ ጽድቅ የሚመስሉስህተቶች አሉና ትክክለኛውን ለመያዝ ከምንጩ መነሣት አግባብ ነው፡፡

በመሆኑም “ የልደት በዓል ገሃድ አለውን ?” ለሚለው ጥያቄ መልሳችን “ አዎን የልደት በዓል እንደ ጥምቀት ገሃድ አለው ” የሚል ይሆናል፡፡ ለዚህምምንጫችን የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዐት ምንጭ የሆነው ከላይ ያስነበብነው የፍትሐ ነገሥት ንባብ ነው፡፡ እንዴት በጾመ ነቢያት ላይ ደምረን ገሃድን እንጾማለን ? የሚል ካለም መልሳችንየሚከተለው ነው፡፡ ጾመ ነቢያት / የገና ጾም ከኅዳር 15 ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 28 ቀን ለ 44 ቀናት ይጾማል፡፡ ከእነዚህም መካከል 40 ው ቀን ጾመ ነቢያት፣ 3 ቱ ጾመ አብርሃም ሶርያዊ ሲሆኑ የቀረው 1 ቀን ደግሞ የገሃድ ጾም ነው፡፡ በልደት የሚጾመው የገሃድጾም በጾመ ነቢያት ውስጥ ተካቶ ይጾማል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት በዐቢይ ጾም ውስጥ ጾመ ሕርቃልና ሰሙነ ሕማማት ተካትተው እንደሚጾሙማለት ነው፡፡ ( ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 565 ፣ 567) ፡፡ በዘመነ ዮሐንስ በዓለ ልደት በታኅሳስ 28 ነውና የገና ጾምየሚጾመው ለ 43 ቀናት ነውና የዘመነ ዮሐንስ ገና ገሃድ የለውምን ? የሚል ጥያቄም ከተነሣ መልሱ ልደት በዘመነ ዮሐንስም ገሃድ አለውየሚል ነው፡፡ ይልቁንም በዐቢይ ጾም፣ በጾመ ሐዋርያት፣ በጾመ ፍልሰታ፣ በጾመ ነቢያትና በጾመ ነነዌ ጾመ ድኅነትን ( የረቡዕና ዓርብጾምን ) ደርበን እንደምንጾም እንዲሁ ገሃድን በጾመ ነቢያት ውስጥ ደርበን እንጾማለን፡፡

 

ዐቢይጾምን ሳይጾሙ ሰሙነ ሕማማትንና ጾመ ሕርቃልን እንደማይጾሙት ጾመ ነቢያትን ከኅዳር 15 ጀምሮ ሳይጾሙ ለልደት የገሃድ ጾምን መጾምጸያፍ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ለማይጾም ሰው ብላ የምትሠራው ሥርዐት የለምና “ ለማይጾም ሰው ገሃድ አለ ” ማለት ሞኝነት ነው፡፡ ጾመነቢያትን ሳንጾም ገሃድን ጾመን ልደትን እናክብር ማለት ንስሐ ሳንገባ ሥጋ ወደሙን እንቀበል እንደማለት ያህል ስንፍናና ድፍረትነው፡፡

የጌታየልደት በዓል ገሃድ የለውም የሚሉት የሚያቀርቡት አንድ ምክንያት “ ሰላም ዕብል ለጾመ ዕለት ዋሕድ ዘስሙ ገሃድ - ገሃድ ለተባለውለአንዱ የጾም ዕለት ሰላም እላለሁ ” የሚለውን የስንክሳር የጥር 10 ንባብ ነው፡፡ ሆኖም “ ዋሕድ - አንድ ” የተባለው በተከታታይቀናት ሳይሆን ለአንድ ቀን ( በልደትና በጥምቀት ዋዜማ ) የሚጾም በመሆኑና ከሰባቱ አጽዋማት እንደ አንዱ የሚቆጠር በመሆኑ ነው፡፡ከ 7 ቱ አጽዋማት መካከል የሚቆጠሩ አጽዋማትን አንድ ብለን እንደምንቆጥር ገሃድንም አንድ ማለቱ ነው፡፡

 

ልደት ረቡዕ በመዋሉ ይጾማልን ?

ለስምአጠራሩ ክብር ይግባውና የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሰውን ብቻ ሳይሆን ፍጥረትን ሁሉ ያስደሰተ ልዩበዓል ነው - ወኩሉ ፍጥረት ተፈስሐ በምፅአትከ እንዲል ሊቁ፡፡ በመሆኑም በዚህ ልዩ የደስታ ቀን ማዘን፣ መጸጸት አይገባም፡፡ የክርስቶስልደት ለሥጋችንም፣ ለነፍሳችንም፣ ለመንፈሳችንም ድኅነት ነውና በዕለቱ በሥጋም በነፍስም በመንፈስም ሐሴት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡በመሆኑም በዕለቱ ሥጋችንን በጾም መለጎም አይገባም፡፡

ከላይየተጠቀምናቸው መጻሕፍት ሁሉ የልደት በዓል ረቡዕም ዋለ ዓርብ የቤተክርስቲያን ሥርዐት እንዲገደፍባቸው እንደሚያዝ ያብራራሉ፡፡

 

ፍትሐነገሥትም ስለ ጾመ ድኅነት ( የረቡዕና የዓርብ ጾም ) ሲያብራራ “ ዓዲ ረቡዐ ወዓርበ በኩሉ ሱባኤ ዘእንበለ መዋዕለ ፶ ወበዓለ ልደትወጥምቀት ሶበ ኀብሩ ቦሙ፡፡ ወይጼምዎሙ እስከ ፱ቱ ሰዓት በከመ ተጽሕፈ፤ - ዳግመኛም በየሳምንቱ ሁሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡በዓለ ሃምሳ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው፡፡ ” በማለትዓርብና ረቡዕ በበዓለ ሃምሳ እንዲሁም ልደትና ጥምቀት ሲውሉባቸው እንደማይጾሙ ያዛል፡፡

 

ጥምቀት ሰኞ በመሆኑ የገሃድ ጾምን እሑድ እንዴት ነው የምንጾመው ?

ሰንበትንመጾም እንደማይገባ የቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ማዘዙ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን በባዶ ሆድ ጾም አይዋልባቸውም እንጂ ከጥሉላት ምግቦችመከልከልን ሥርዐቱ አያግድም፡፡ በመሆኑም በዐቢይ ጾም፣ በጾመ ሐዋርያት፣ በጾመ ፍልሰታ እና በጾመ ነቢያት ሰንበቶች እንደምናደርገውገሃድ ቅዳሜ ወይም እሑድ ሲውል ከጥሉላት ምግቦች በመከልከል ብቻ እንጾመዋለን፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጥምቀት ሰኞ ከዋለ ገሃዱን ቅዳሜእስከ ስድስት ሰዓት እንዲሁም እሑድ እስከ ተወሰነ ሰዓት መጾም እንደሚገባ የሚናገሩት ምንም አይነት የሥርዐት ምንጭ የሌለው ነው፡፡ [9]

በዚህምመሠረት የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ሰኞ በመሆኑ ዋዜማውን ማለትም እሑድ ጥር 10 ን ከጥሉላት ምግቦች ( ጾም ካላቸው ምግቦች ) በመከልከልእንጾማለን ማለት ነው፡

ጥቆማ

1. ለምዕመናን ፡ - በጾም ላይ ክርክር ከተነሣ ለጾም ማድላት እንደሚገባ ቤተክርስቲያን ትመክራለችና ለጾም ማድላት ተገቢ ነው፡፡

 

2. ለሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና ለቅዱስ ሲኖዶስ ፡ - ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻተጠያቂው አካል ነውና ክርክር የሚነሣባቸውን ጉዳዮች በመሰብሰብ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ በመጽሐፍም ሆነ በማናቸውም የመገናኛመንገድ ምላሽ እንዲሰጥ ቢያደርግ መልካም ነው፡፡ ሊቃውንቱም እስኪታዘዙ ሳይጠብቁ ዝምታን ከመምረጥ ይልቅ አንድ የሚያደርግ ምላሽቢሰጡ መልካም ነው፡፡

 

ነቢዩኢዩኤል በትንቢቱ “ ጾምን ቀድሱ ”( ኢዩ . 2 ፡ 15) እንዳለ በጾማችን ከምግብ በዘለለ አስበንና ጾማችንን ቀድሰን በዓላቱን በመንፈሳዊነትእንድናከብር እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን፡፡

[1] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንታሪክ፣ አባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ፣ ሰኔ 1974 ዓ . ም . ፣ ገጽ 130

[2] ጾምና ምጽዋት፣ ዲ . ቃኘው ወልዴ፣ ሚያዝያ 1995 ዓ . ም . ፣ ገጽ 54

[3] ዓምደ ሃይማኖት፣ ብርሃኑ ጎበና፣ የካቲት 1985 ዓ . ም . ፣ ገጽ 160

[4] “ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ . ም . (2000) ፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀ፣ 2000 ዓ . ም . ፣ ገጽ 35-36

[5] “ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንእምነት ሥርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት / THE ETHIOPIAN ORTHODOX TEWAHEDO CHURCH FAITH, ORDEROF WORSHIP AND ECUMENICAL RELATIONS ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያዘጋጁት፣ 1988 ዓ . ም . ፣ ገጽ 74

[6] ዓምደ ሃይማኖት፣ ብርሃኑ ጎበና፣ 1985 ዓ . ም . ፣ገጽ 160

[7] ጾምና ምጽዋት፣ ዲ . ቃኘው ወልዴ፣ 1995 ዓ . ም . ፣ ገጽ 54

[8] ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ ብፁዕ ወቅዱስአቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሆኑ በ 6 ኛው ዓመት ለ 5 ኛ ጊዜ የታተመው፣ትንሣኤ የመጻሕፍት ማሳተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 1990 ዓ . ም . ፣ አንቀጽ 15 ቁጥር 567 ገጽ 150

[9] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንታሪክ፣ አባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ፣ ሰኔ 1974 ዓ . ም . ፣ ገጽ 130

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine