ትምህርት

እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት

በስመ አብ ወወለድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አምላክ አሜን

በክረስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉድ በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊያን የተሰኛችሁ  እግዚአብሔር ቤተሰቦች የድንግል ማርያም የአስራት ልጆች የጻድቃን የሰማዕታት የቅዱሳን መላዕክት ወዳጆች በወደደን ባፈቀረን ስለ እኛ እራሱን አሳልፎ በሰጠን በልዑል እግዚአብሔር ሰላምታ አንደምን ሰነበታቸሁ፡፡ አሜን በግሩም ጥባቆቱ ጠብቆ በቸርነቱ ጎብኝቶ አስከ እዚች ስዓት ያደረሰን የአምላካችን ስም በእኛ በልጆቹ አንደበት ከትውልድ እስከ ትውልድ የተመሰገነ ይሁን አሜን፡፡ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ፡፡ እግዚአብሔር ቢፈቅድና ቢወድ በዓሉን በተመለከተ አጭር ትምህርት ይዤላችሁ ቀርቤአሉ የልድያን ልብ የከፈተ አምላካችን እኔ የምናገርበትን አንደበት ለእናንተ የምታስተውሉበትን ልቦናና አእምሮ አምላካችን ማስተዋል ጥበቡን ያድለን፤ ለአባቶቻችን የላከውን መንፈስ ቅዱስ ለእኛም ይላክልን፡፡

ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኒት ተወልዶላችኋል ይኸውም ቡሩክ ክርስቶስ ነው፡፡ሉቃ2÷11

ቃሉን የተናገረው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሲሆን የተናገረውም ለእረኞቹ ነው፡፡ የቃሉን ፍች ስንመለከተው ከሁሉም ታናሽ ክፍል በምትሆን በኤፍራታ ክፍል በቤተልሔም ነቢያት ተስፋ ያደርጉት ሱባኤ የቆጠሩለት የዓለም ሁሉ አዳኝ ፈዋሽ መድኃኒት ተወለደ፡፡ መርገመ ስጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል የዓለም መድኀኒት የሚሆን የባሕርይ አምላክ በዳዊት ከተማ ፍጹም ሰው ሆኖ ተወልዷልና፡፡ የነቢዩ ኢሳይያስም እንዲህ ብሎ የተናገረው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ በኛም መካከል ተመላለሰ ከኛም ጋር አደረ ሕሙማንንም ሲፈውስ ተመለከትን አየን አለ፡፡ ኢሳ 7÷14 ‹‹ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወይሰመይ ስሙ አማኑኤል ዘበትርጓሜሁ እግዚአብሔር ምስሌነ›› ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች  ሰሙንም አማኑኤል ትለዋለች ትርጉሙም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው፡፡

 

እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ በውስጧ ያለውን ሁሉ  ፈጠረ፡፡ ዘፍ 1÷1 ሌሎች ፍጥረታት ለአንክሮ ለተዘክሮ ሲፈጠሩ ሰውና መላእክትን ግን ስሙን ይቀድሱ ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ተፈጠሩ፡፡ አምላክም ለሰው ልጅ (ለአዳም) የሚያስፈልገውን አዘጋግጅቶ እውቀትን ስልጣንን ሰጥቶ አማልክት ዘበጸጋ አድርጎ ሾሞታል መመሪያ ሰጥቶት በክብር እንዲኖር ነጻ ፍቃድ ሰጠው፡፡ ዲያብሎስም አምላክነትን በመሻቱ ተዋርዶ ሳለ አዳምንም በተዋረደበት ምኞትና ፍላጎት እንዲወድቅ ክብሩን እንዲያጣ ከአምላኩ እንዲለይ አደረገው፡፡ የስው ልጅም ፀጋው ተገፈፈ ባህሪውም ጎሰቆለ በረከቱን ሹመቱን አጣ፡፡ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ መሪ አስተዳዳሪ ይህን ስልጣኑን አጥቶ ለዲያብሎስ ተገዥ ሆነ፡፡ አዳምም ከእግዚአብሔር በመለየቱና ክብሩን በማጣቱ ተፀፅቶ ንስሐ ገባ ለስርየተ ኃጢአት የሚሆን መስዋእትን አቀረበ፡፡ እግዚአብሔር አምላክም መስዋዕቱን ልመናውን ተቀብሎ እርሱን ዘሩን ለማዳን ቃልኪን ገባለት ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀል ላይ ተሰቅዬ አድንኅ አለው፡፡ ይህ የተስፋ  ዘመንም በአምለክ ዘንድ 5ቀን ተኩል ነው በሰው ዘንድ ግን 5500 ዓ.ዓ ነበር፡፡ አዳምም ይህን አላሰተዋለም ነበር፡፡ አዳም ይህችን ቀን በጉጉት በተስፋ እየተጠባበቀ ኖረ ለልጆቹም ቃል ኪዳኑን በጾም በስግደት በሱባኤ በተስፋ እንዲጠብቁት አስተማራቸው ልጆቹም ሱባኤ እየቆጠሩ ትንቢት እየተናገሩ ያችን የድኅነት ቀን ጌታ ይወለዳል የተባለባትን በተስፋ ጠበቋት ከእነዚህም መካከል የሚከተሉትን እንመልከት፡፡

1/ የመጀመሪው ሱባኤ ገብተው የተስፋውን ቃል ሲጠባበቁ ከነበሩት መካከል አንዱ ሄኖክ ነው፡፡ እንዲህም በማለት ተናግሯል፡፡ መ.ሄኖክ 35÷1-2 ‹‹8ኛቱ ሰንበት ጽድቅንና ኩነኔ የሚታወቅባት ሱባኤ ናት፡፡ ሰይፍም ለእርሷ ይሰጣታል ታላቁ ንጉሥ የሚመሰገንበት ቤትም በእርስዋ ይሠራል፡፡ምስጋናውም ለዘለዘለም ነው፡፡ ›› ሊቃውንቱ ሲያመሰጥሩትም ለእርስዋ ሰይፍ ይሰጣታል ማለቱ ጽድቅን  ኩኔን የሚታወቅባት ወንጌል ያንጊዜ በዓለም ሁሉ ትሰበካለች ማለቱ ነው፡፡ የታላቁ ንጉሥ ቤት ይሠራል ማለቱ የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሚመሰገንበት ቤተ ክርስቲያን ትሠራል ትታነጻለች ማለት ነው፡፡ ምስጋናውም ለዘለዓለዊ ነው ማለቱ ሰውና መላዕክት በአንድነት ሆነው ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ››እያሉ ዘወትር ያመሰግናሉ ማለት ሲሆን ስምተኛይቱ ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠችበትን ዕለተ ልደተ ክርስቶስ ናት ብለው ያመሰጥሩታል፡፡

2/ዳንኤል 70 ዘመን በተፈጸመ ጊዜ እጎበኝቻለሁ ተብሎ ት.ኤር 29÷10 የተነገረውን የትንቢት ቃል እያሰበና እየተማጸነ ሲጸልይ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው ተገልጾ እንዲህ ብሎታል፡፡ ዳን 9÷22-25 አመፃን ይጨርስ ኃጢአትንም ይፈጽም በደልንም ያስተስረይ የዘለዓለምንም ጽድቅ ያገባ ነው፡፡

3/ ኤርሚያስከባቢሎን እንደተመለሰ በፈረሰው ቤተመቅደስ ውስጥ ሆኖ ሲጸልይ ሳለ ራእይ አየ በ3ኛው ቀን እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ ‹‹ፈጣሪአችንን በአንድ ቃል አመስግኑ የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አመስግኑ ከዚህ ዓለም ይመጣል 12 ሐዋርያትንም ይመርጣል›› ብሎ በአጭር ግልጥ በሆነ ኃይለ ቃል ተናግሯል፡፡ እግዚብሔርም ቃሌ ከሚያልፍ ሰማይና ምድር ቢያልፉ ይቀላል ብሎ ተናግሯልና፡፡ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም፡፡ ማቴ 24፣25 የጌታ ቃል ለዘላለም ይኖራል፡፡ 1ጴጥ 1፣25 ይህንንም ቃሉን በማክበርጊዜው በደረሰ ጊዜ ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተወለደ፡፡ ፍቅሩን ይገልጽልን ዘንድ ከሰማየ ሰማያት ወረደ በዚችም ምድርም ተመላለሰ ጎባጣዎችን አቀና ሽባዎችን ተረተረ ለዓይነ ስውሮች ብርሃን አደላቸው ለእኛም በጨለማ ውስጥ ለምንኖር ብርሃን ወጣልን፡፡ኢሳ 9፣2

የነቢያት ትንቢትም ተፈጸመ እውን ሆነ ተረጋገጠ ት.ሚክ 5፣2 አንቺ የኤፍራታ ምድር ቤተልሔም ሆይ አእላፍት መካከል ትሆኝ ዘንድ ታናሽ ነሽ ነገር ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ለዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ከአንቺ ይወጣል፡፡ ብሎ የተናገረው የነቢዩ ሚክያስ ቃል እንዲሁም የሌሎችም ነቢያት ተፈጽሟል፡፡ በቤተልሔም ተወለደ ሰባ ሰገልም ለተወለደው ለሕፃኑ ለክርስቶስ ከሩቅ ምስራቅ ተነሥተው እጣን ከርቤ ወርቅ ይዘው ወደ ቤተልሔም ሄዱ ሰገዱለት ወርቅ ዕጣኑንም ከርቤውንም ገበሩለት አመስገኑትም፡፡ የጥበብ ሰውች ለክረስቶስ ሊሰግዱ ሄደዋል እኛስ ወደ የት ነው? ወደ ባዕድአምልኮ ወደ ዳንስ ቤት መስከር መጠጣት ነውን እንዲህ ባለ መንገድ ነውን? የጌታችንን ልደት ማክበር የለብንም አይደለም ይህን አይነቱን በዓል እግዚአብሔርም ይጠላዋል፡፡‹‹ዓመት በዓላችሁንም ጠልቼዋለሁ አርቄዋለሁም›› ት.አሞጽ 5፣21 ደካሞችን የዕለት ጉርስ ምግብ ልብስ የሌላቸውን በማካፈል ማክበር አለብን ፡፡

በፍቅር በሰላም በአንድነት በኅብረት ሆነን ልክ አንደ መላእክት እና እረኞቹ ለክርስቶስ እንደ አንድልብ መካሪ ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ምሰጋና እንዳቀረቡት እኛም ከወንድሞቻችን ጋር አብረን ያለንን ተካፍለን ልናከብር ያስፈልጋል፡፡

ሌላው ስውነታችንን ለአምላካችን አስገዝተን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር የጽድቅ የጦር መሳሪያ አድርጉ ሮሜ 6፣13

ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት ተወልዶላችኋል፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በደሳለኝ አላምሬ ዘኆኅተ ብርሃን

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine