የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

በኢ/ት/ኦ/ተ/ቤ/ክን ስርአትና ደንብ እየተዘጋጀ በቦሌ ኆ/ብ/ቅ/ድ/ማርያም ቤ/ክን ሰንበት ት/ቤት ስለመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱሳን መጻሕፍት ዙሪያ በትምህርት ክፍል እየተዘጋጀ የሚቀርብ ተከታታይ ኮርሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ትምህርት፡፡

 

መግቢያ


‹‹በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም አፊ አዝዟልና መንፈሱም ሰብስቧቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም ›› ኢሳ 34÷16 ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የነፍስ ምግቦች ናቸው፡፡ ሰዎች ለቁመተ ስጋ ምግብና ውኃ እንደሚያስፈልገን ሁሉ ነፍሳችን ደግሞ እንዲሁ ምግበ ነፍስ ያስፈልጋታል፡፡ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ምድራዊ ሕይወታችንን ጭምር እንዴትና በምን አኳኋን ማራመድ እንደሚገባን የሚያስተምር የሚመክርና የሚገስፅ መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው ታላቅ የሕይወት መመሪያ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔር

መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርት ለተግሣፅ ልብንም ለማቅናት በፅድቅም ለሰው ምክር የሚጠቅም ስለሆነ 2ኛ ጢሞ 3÷16 ከመጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ትርጉም አንስቶ ተከታታይ ትምህርቶችን እንሰጣለን፡፡

 

1.1 መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ምን ማለት ነው

 

መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ሐረግ ‹‹መጽሐፍ›› እና ቅዱስ ከሚለው ሁለት ቃላት የተገኘ ሐረግ ሲሆን መጽሐፍ የሚለው ቃል ተጠቃሎ በአንድ ጥራዝ ስር የተሰበሰበ ጽሑፍን ሲገልጥ ‹‹ቅዱስ›› የሚለው ቃል በእብራይስጥ ክዱስ በሱርስት ካዲሽ በግእዝና በአረብኛ ቅዱስ ካለው ቃል የተገኘ ነው፡፡ ትርጉሙም የተለየ የተከበረ ማለት ነው፡፡

 

1.2 መጽሐፍ ቅዱስ ስለምን ቅዱስ ተባለ

 

1 ስገኝው እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ቅዱስ ተብሏል፡፡

 

የእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ ቅዱስ ስለሆነ፡፡

‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፡፡›› ዘሌ 1÷92

‹‹የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡›› 1ኛ       ጴጥ 1÷15

 

2  ሰውን ወደ ቅድስና የሚያደርስ ስለሆነ ቅዱስ ተብሏል፡፡

 

 የከበሩ መጽሐፍትን አምኖ መቀበል የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ነው፡፡

‹‹የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው፡፡›› ራዕ 1÷27


3  በእግዚአብሔር መንፈስ የተነሳሱ ቅዱሳን ሰዎች የፃፉት በመሆኑ ፡፡

 

‹‹በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ እራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ 2ኛ ጴጥ 1÷1-11

 

4. የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊት ያለውን ሁኔታ በእርግጠኝነት የሚናገር በመሆኑ

 

በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ የተከወነ ሁኔታ ሲገለጽ በይሆናል ወይም በግምት ሳይሆን በእርግጠኝነት ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ›› እንዳለ ዘፍ1÷1

 

5   ወደፊት ስለሚመጣው በእርግጠኝነት የሚናገር ስለሆነ

 

መጽሐፍ ቅዱስ ያለፈውን በእርግጠኝነት እንደሚያስቀምጥ ሁሉ የሚመጣውንም ድርጊት ያለምንም ጥርጥር በእርግጠኝነት የሚናገር በመሆኑ ልዩ ነው፡፡ ሌሎች መጻሕፍት ወደፊት ስለሚመጣው ነገር በእርግጠኝነት ሣይሆን የራሣቸውን መላምት ፣ በጥናትና በምርምር ወይም በግምት እንዴት እንዲ ሊሆን ይችላል ቢሉ እንጂ እንዲህ ይደረጋል ብለው በእርግጠኝነት አይናገሩም፡፡

 

ለምሳሌ ነብዩ ልዑል ኢሣይያስ ‹‹እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች›› ኢሳ 7÷14 አለ እንጂ ትፀንስ ይሆናል አማኑኤል ሊባል ይችላል አላለም፡፡

 

6   የሚያነቡትንና የሚሰሙትን ስለሚባርክ፡፡

 

ሌሎች መጻሕፍትን በማንበብ ምክርና እውቀት ይገኛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ እና ቃሉን በመስማት ግን ቡራኬም ይገኛል፡፡ ራዕ 1÷3

 

7   ዘመን የማይሽረው በመሆኑ

 

 መጽሐፍ ቅዱስ የማያረጅ የዘመን ብዛት የማይገታው ዘላለማዊ ነው፡፡

‹‹የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ፀንታ ትኖራለች›› ኢሳ 40÷8

‹‹ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም›› ማቴ 24÷35

‹‹የጌታ ቃል ለዘለአለም ይኖራል›› 1ኛ ጴጥ 1÷25

 

8   ክብረ ቅዱሳንን የሚዘክር ስለሆነ

 

ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፣ ስለቅዱሳን መላእክት ፣ ስለቅዱሳን ፃድቃን እና ሠማእታት የሚናገር ነው፡፡

በአጠቃላይ በጽሐፍ ቅድስ የመንፈስ ምግብ ነው፡፡ ማቴ 4÷4 ኤር 15÷16 የመንገዳችን መብራት ነው መዝ 118÷105 በሁለት በኩል የተሣለ ሰይፍ ነው፡፡ ዕብ 4÷12 ያንፃል ዮሐ 15÷3 ያለመልማል መዝ 1÷3  

 

 


1.3 የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ

 

1.3.1 መጽሐፍ ቅዱስን ማን ጻፈው

 

የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤቱ እግዚአብሔር ሲሆን ጸሐፊዎቹ ግን ከእርሱ የተላኩ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው፡፡ ብዛታቸውም ከዐርባ በላይ ነው፡፡

‹‹አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክርታስ ውሰድ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብ ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት፡፡›› ኤር 36÷2

‹‹በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ፡፡›› 2ኛ ጴጥ 1÷5-11

 

1.3.2  መጽሐፍ ቅዱስ መቼና የት ተጻፈ

 

መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ሰዎች እንደተጻፈ ሁሉ የተጻፈበት ዘመንና ቦታም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፍ መጽሐፈ ሄኖክ ከተጻፈበት ከ 1476 ዓ.ዓ ጀምሮ የመጨረሻው ዮሐንስ ራእይ እስከተጻፈበት እስከ ከ 96 ዓ.ም ድረስ ብዙ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለመጻፍ 4100 ዓመት በላይ ወስዷል ማለት ነው፡፡

 

ከላይ እንደተገለጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያት እንደተጻፉ ሁሉ የተጻፉባቸው ቦታዎችም እንደዚሁ የተለያዩ ናቸው፡፡ ምሳሌ

 

ቅዱሳት መጻሕፍት                     የተጻፉባቸው ቦታዎች

 

·         የኦሪት መጻሕፍት……………….…..…….ሲና ምድረበዳ

·         መጽሐፈ ኢያሱ……………..……………..ምድረ ከነዓን(በእስራኤል)

·         መጽሐፈ አስቴር………………………….ፋርስ

·         ትንቢተ ዳንኤል…………………………….ባቢሎን

·         የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት

ወደ ቆላስይስ………………………………….ሮሜ

·         የዮሐንስ ……………………………………..ፍጥሞ ደሴት


1.3.3  መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በምን ቋንቋ ተጻፈ


አብዛኞቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በእብራይስጥ ሲሆን ትንቢተ ዳንኤል የተጻፈው ግን በአረማይክ ቋንቋ ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት በዕብራስጥ ከተጻፈው ከማቴዎስ ወንጌልና በሮማይስጥ ከተጻፈው ከማርቆስ ወንጌል ውጭ የተቀሩት የተጻፉት በዘመኑ የአብዛኛው ሕዝብ መነጋገሪያ በነበረው በፅርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነበር፡፡


1.4  መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኢትዮጲያ እንዴት መጣ

 

ኢትዮጲያ በዓለም ላይ ከሚገኙት ብዙ ሀገሮች ተለይታ በዘመነ ብሉይ እና በዘመነ ሐዲስ ሁለቱንም ኪዳናት በመቀበል ብቸኛ ሀገር ናት፡፡ ምንም እንኳን በዘመነ ብሉይ የቃል ኪዳን ሕዝብ ተብለው የሚታወቁት እስራኤላውያን ቢሆኑም ኢትዮጵያም በወቅቱ የዚህ ቃል ኪዳን ተካፋይ ለመሆን የበቃች ሀገር ናት፡፡ ‹‹እናንተ እስራኤላውያን ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን›› አሞ 9÷72 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት


ብሉይ ኪዳን ማለት የቆየ፣ የጥንት ውል ወይም ስምምነት ማለት ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን የአንድ አምላክ አማኞች የሆኑትን የዕብራውያንን ታሪክ ይተርዳል፡፡ በውስጡም ብዙ የተስፋ ቃሎችን የያዘ ነው፡፡ ስለ መሲሕ ክርስቶስ መምጣትም የተነገሩ ትንቢቶች በብዛት አሉበት፡፡ ኢሳ 7÷14

 

ብሉይ ኪዳን ከሐዲስ ኪዳን ተነጥሎ አይታይም፡፡ ምክንያቱም ብሉይ ኪዳን የሐዲስ ኪዳን ትንቢት ሲሆን ሐዲስ ኪዳን የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ ነው፡፡ ሐዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን ውስጥ አለ፡፡ ሆኖም ግን ነቢያት የተነበዩለት አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘመኑንና ጊዜውን ቆጥሮ በተገለጠ ጊዜ ስውር የነበረው ሐዲስ ኪዳን ተገልጸል፡፡

 

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከተጻፋት ጊዜ ፣ ከያዙት ሀሳብና ከአጻጻፋቸው ሁኔታ አንጻር በዐራት ምድቦች ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም፡-

 

2.1 የሕግ መጻሕፍት

 

የሕግ መጻሕፍት የሚባሉት መጽሐፍ ኦሪትም በመባል ይታወቃል፡፡ ኦሪት ቃሉ የሱርስት ሲሆን ሕግ ማለት ነው፡፡ የሕግ መጻሕፍት በቁጥር አምስት ሲሆኑ የእነዚህ መጻሕፍት ጸሐፊም ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አምስቱ የሙሴ መጻሕፍትም ይበላሉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት እንደየይዞታቸው የተለያ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ስያሜዎቻቸውና የየመጻሕፍቱ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 

 

 

 

1.     ኦሪት ዘፍጥረት /ዘልደት/


ይህ መጽሐፍ የሥነ-ፍጥረትን ልደት፣ አጀማመርና አመጣጥ የሚያስረዳ በመሆኑ ይህን ስያሜ አግኝቷል፡፡ ከሕግ መጻሕፍትም ሲጻፍ የመጀመሪያው ነው፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት 50 ምእራፎች ያሉት ሲሆን የመጽሐፉም ይዘት እንደሚከተለው በአራት ዋና ዋና ክፍሎች በመክፈል ሙሉ ታሪኩንና ትምህርቱን ማጥናት ይቻላል፡፡ እነዚህም ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

2.     ኦሪት ዘጸአት

3.     ኦሪት ዘሌዋውያን

4.     ኦሪት ዘኁልቁ

5.     ኦሪት ዘዳግም

     


ምንጭ

  1. የመጽሐፍ ቅድስ ጥናት (ቁጥር 1) በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን በ/ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማሕበረ ቅዱሳን ፤ በመ/ር አባይነህ ቸሬ አበበ እና በዲ/ን ቴዎድሮስ በየነ
  2. የመጽሐፍ ቅድስ ጥናት ጥራዝ በመናገሻ ገ/ድ/ቅ/ጊ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤት

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine