ትምህርተ ሃይማኖት

ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት

ሃይማኖት የሚለው ቃል ሃይመነ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ማመን ፣ መታመን ፣ አመኔታ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ቅድመ ዓለም ከሁሉም በፊት የነበረ ፍጥረታትን የፈጠረ ማዕከላዊ ዓለም ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ ድህረ ዓለም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ለእርሱ ግን አስገኝ አሳላፊ የሌለው መሆኑን በአንድነት በሦስትነት ያለ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳለ ማመን ማለት ነው፡፡ ሮሜ 10.9 ሃይማኖት ፈጣሪና ፍጡር የሚገናኙበት ረቂቅ መንገድ ነው፡፡ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ማግኘት ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ዕብ 11.6

 

v    ሃይማኖት ለዓለም ፈጣሪ አለው ብሎ ማመን ነው፡፡

v    ሃይማኖት ለሚቀበሉት የድል ወይም የድኅነት መሣሪያ ነች

v    ሃይማኖት አንዲት ናት፡፡ ኤፌ 4.5 ኤር 6.16 በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው የእውነት ግንኙነት አንድ ነውና፡፡

 

በአጠቃላይ ሃይማኖት በዓይን የማይታይ በእጅ የማይዳሰስ በጆሮ ብቻ ሰምቶ ይህ እንዴት ሊደረግ ይችላል? ሳይሉ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብለው በእምነት ሕሊና አምነው የሚቀበሉት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡ ሉቃ 1÷26-37 ፣ ዘፍ 18.14 ፣ ዕብ 11÷1-3 ፣ ሮሜ 4÷3

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን የምትመራባቸው ሦስት የትምህርት መመሪያዎች አሏት፡፡ እነርሱም፡-

 

ሀ. ዶግማ፡- ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም የማይለወጥ፣ የማይቀየር የማይሻሻል፣ የማያረጅ ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ዶግማ ነው፡፡

ምሳሌ፤ አስርቱ ትእዛዛት ፣ስድስቱ ቃላተ ወንጌል፣ አምስቱ አዕማደ ምስጢር፡፡ ዶግማ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ሰው እንደፍላጎቱ እንደምኞቱ ሊጨምርበት፣ ሊቀንስበት ወይም ሲያሸሽለው አይችልም፡፡ 2ኛ ጴጥ 1.20፣ ዕብ 1.1-3 ፣ ማቴ 24.35

 

ለ. ቀኖና፡- እንደ ዶግማ የግሪክ ቃል ነው፡፡ የቃሉ አመጣጥ ‹‹ሸንበቆ›› ከሚለው ነው፡፡ የጥንት አባቶች ሸንበቆን ርዝመት መለኪያ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የክርስቲያኖች ሥርዓታዊ ሕይወት መለኪያ ሆኖ እንዲያገለግል የቤተክርስቲያ አባቶችና ሊቃውንት በጉባዔ ወይም በሲኖዶስ የሚወስኑት ውሳኔ ቀኖና ይባላል፡፡

 

ቀኖና እንደወቅቱና ጊዜው በሲኖዶስ ሊለወጥ ወይም ሊሻሻል ይችላል፡፡የቀኖና ምሳሌዎች ጾም ዶግማ ሲሆን የጾም ጊዜ ቀኖና ነው፡፡ ቅዳሴ ዶግማ ሲሆን የቅዳሴ ጊዜ ቀኖና ነው፡፡

 

እግዚአብሔር ሁሉን በሥርዓት ያደርጋል፡፡የእጁ ፍጥረታት የሆኑት መላእክትና ሰው በሥርዓት እንዲያመልኩት ሕግና ሥርዓቱን እዲጠብቁ ይፈልጋል፡፡ 1ኛ ቆሮ 11.34፣ 1ኛ ቆሮ 14.40፣ ቆላ 2.5 የሐዋ.ሥራ 16.4፣ 2ኛ ተሰ 3.6፣ 1ኛ ቆሮ 12.2

 

ሐ. ትውፊት፡- ‹‹አወፈየ›› ከሚለው የግእዝ ገስ የወጣ ሲሆ ትርጉሙም ውርስ፣ ውርርስ፣ ርክክብ፣ ቅብብል ማለት ነው፡፡ ይኸውም አንድ ትውልድ ከእርሱ በፊት ከነበሩት የሚወርሰው የሚያገኘውና የሚቀበለው ነገር ነው፡፡ ሂደቱም በዚህ የሚያበቃ ሳይሆን እርሱም በተራው ለተተኪው ያስተላልፋል፡፡ ትውፊት ቅዱሳት መጻሕፍት ከመጻፋቸው በፊት የነበረ ነው፡፡

ምሳሌ፡- የአቤልና የቃየል መስዋዕት ማቅረብ፡፡

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine