ግብረ ሕማማት

†††ጥቂት ስለ መጽሐፈ ግብረ ሕማማት†††

የመጽሐፉ ርእስ፡- መጽሐፈ ግብረ ሕማማት
ደራሲ፡- ገማልያል እና ኢንፎስ
ተርጓሚ፡- ከዐረብኛ ወደ ግእዝ - ብፁዕ አቡነ ሰላማ ብርሃነ አዜብ(ከ134-1380)
- ከግእዝ ወደ አማርኛ - ሊቀ መዘምራን ላእከ ማርያም ወልደ ኢየሱስ
የገጽ ብዛት፡- 1194
በመጀመሪያ የተጻፈበት ጊዜ፡- የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን
ዋጋ፡- 600ብር (አሁን ከዚህም ጨምሯል)
† ግብረ ሕማማት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለዘሩ ድኅነት የተቀበለውን መከራ የሚዘክር መጽሐፍ ነው፡፡ ግብረ ሕማማት ማለት የሕመም ፣ የመከራ ሥራ ማለት ነው፡፡ የጌታን መከራውን ሥቃዩን ሕማሙን በሰዓትና በጊዜ ከፍሎ የሚናገር ፣ እንዲሁም ምን በማን መጸለይ እንደሚገባውም በዝርዝር የሚገልጽ በመሆኑና የጌታችንን ሕማም በምናስብበት በሰሙነ ሕማማት በዋነኝነት አገልግሎት ላይ የሚውል በመሆኑ ግብረ ሕማማት ተባለ፡፡ መጽሐፉ ግብረ ሕማማት እንዲባል በውስጡ የታዘዘ መሆኑን የአማርኛው ትርጉም መቅድም ይገልጻል፡፡

† የግብረ ሕማማት መግቢያ ስለ መጽሐፉ ታሪክ ሲናገር ‹ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል በሚፋጠኑበት ጊዜ፣ ስለ እርሱ ስለ ጌታችን ታሪኩንና ተአምራቱን ይከታተሉ ከነበሩት መካከል የተከበሩና የታወቁ ሊቃውንት በኢንፎስና በገማልያል እጅ ተጽፎ በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም በክብር ቦታ ተቀምጦ የተገኘ ነው፡፡› ይላል፡፡ ይኸው መጽሐፈ ግብረ ሕማማት የመጽሐፉን የትመጣ ታሪክ ሲተነትን፣ በየትኛው ገብርኤል እንደነበር አይታወቅ እንጂ ገብርኤል በሚባል የእስክንድርያ ፓትርያርክ የፕትርክና ዘመን ፣ የአባ መቃርዮስ ገዳም ሊቃውንት በነበረው ይዘቱና አገልግሎቱ ላይ የማሻሻያ /የማሟያ ሥራ/ እንደተሠራለት ያትታል፡፡ /የግብረ ሕማማት መግቢያ/

 

† መጽሐፈ ግብረ ሕማማት በወርቃማው የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ዘመን በካልዕ ሰላማ ወደ ልሳነ ግእዝ ተተረጎመ /ከ1340-1380/፡፡ (ግብረ ሕማማት ዘእሑድ ገጽ 488፡፡) ለዘመናት ከብራና ወደ ብራና በብዙ ድካም ሲገለበጥ የኖረው ይህ መጽሐፍ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዘመነ ፕትርክና ታትሞ ተሰራጭቷል፡፡

† የመጽሐፈ ግብረ ሕማማት ይዘቱ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ/የቤተክርስቲያን/ ሊቃውንት ሥራዎች መድበልም ነው፡፡ የነገረ ሃይማኖት ፣ የታሪክ ፣ የተአምራት ፣ የሥርዐትና የሕግ መጽሐፍ ነው፡፡ የመጽሐፉን ይዘት የሚመረምር ሰው እኚህን ሁሉ ከማግኘቱ ሌላ ብሉይንና ሐዲስን ፣ ነቢያትንና ሐዋርያትን ፣ ሊቃውንትንና አዋልድ መጻሕፍትን በብዛት ያገኛል፡፡ ይኸውም በዕለትና በሰዓት ተከፍሎ በሥርዐት የተዘጋጀ የትምህርትና የጸሎት መዝገበ መጻሕፍት ነው፡፡ ለምሳሌ ወቅቱን የሚመለከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ፣ ኦሪትን ፣ ነቢያትን ፣ ሐዲሳትን ፣ ሃይማኖተ አበውን ፣ ተግሣጽን ፣ ተአምረ ኢየሱስንና ተአምረ ማርያምን… ወዘተ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ለመጽሐፈ ግብረ ሕማማት ይዘት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ፈርጥ የሆኑት ቅዱስ ያሬድና አባ ጊዮርጊስም የድርሻቸውን በዜማ የሚጸለዩትን አካተውልናል፡፡

† መጽሐፉ ከሆሳዕና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ መንፈቀ ሌሊት ድረስ በዕለትና በሰዓት ምን መባል እንዳለበት ከፍሎ ፣ ዲያቆኑ ምን ማለት እንዳለበት ፣ ካህኑ ምን ማለት እንዳለበት ልክ እንደ ቅዳሴ መጽሐፍ በመዘርዘርና አገልግሎቱም እንዴት መፈጸም እንዳለበት ጽና ይያዙ ፣ ጥቁር ይልበሱ እያለ መመሪያን በመስጠት የሚተነትን የሥርዐትና የትምህርት መጽሐፍ ነው፡፡

† ሆኖም መጽሐፉ በመጠን ትልቅ ከመሆኑ የተነሣና ዋጋውም ውድ በመሆኑ እንደልብ በምእመኑ እጅም ሆነ በአንዳንድ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ጋር አይገኝም፡፡ ስለዚህ በተለይ መጽሐፉን መግዛት ላልቻሉ ሰሙነ ሕማማት መጽሐፉን ሲነበብ ለመስማት መልካም ጊዜ ነው፡፡

†††መልካም ንባብ†††

ምንጭ፡- መጽሐፈ ግብረ ሕማማት ንባቡና ትርጓሜው ፣ ትንሠኤ ማተሚያ ድርጅት ፣ 2005ዓ.ም.
-ስምዐ ተዋሕዶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት፣ ከሚያዝያ 1-5፡ 2004ዓ.ም.

©ዘሕሊና

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine