ስግደት

፨፨፨ስግደት፨፨፨
ክፍል 1
፨፨፨፨፨፨፨፨
በፍጹም ልብ በፍጹም ነፍስ በፍጹም ኃይል (ዘዳ.6፡5) የሚወደድ የሆነውን አምላካችን እግዚአብሔርን ስናመልከው ሥጋችንንም፣ ነፍሳችንንም፣ መንፈሳችንንም አስተባብረን መሆን አለበት፡፡ መጻሕፍትን በማንበብ፣ ለብዎትን /ማስተዋልን/ በመጠቀም፣ ዕውቀትን ገንዘብ በማድረግ፣ ነቢብን /ንግግርን/ በማስገዛት፣ ሀልዎትን /መኖርን/ በመሠዋትና በመሳሰሉት እግዚአብሔርን ማምለክ ባሕርያተ ነፍስን ለአምልኮተ እግዚአብሔር ማስገዛት ነው፡፡ ጾም/ከሥጋ ፍላጎት መከልከል/ እና ስግደትን የመሳሰሉት ደግሞ በሥጋ እግዚአብሔርን የምናመልክባቸው፣ ሥጋችንን የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ (ይህ ማለት ግን ስግደት ለሥጋውያን ብቻ የተገባ ነው ማለት አይደለም፤ “መላእክቱ ሁሉ ስገዱለት”/መዝ.97፡7/ እንዳለ መላእክትም የሚሰግዱ ናቸውና፡፡) ፍቅር፣ ቸርነት፣ ምኅረት፣ መመጽወት እና የመሳሰሉት የመንፈስ ሥራዎች ደግሞ ወደ ፍጹምነት የሚወስዱን የሥጋን ድካምና የነፍስን ሐልዮት የምንቀድስባቸው እንዲሁም መንፈሳችንን ለአምልኮተ እግዚአብሔር የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡
ስለዚህ ስግደት የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ዓላማ (የሰው ልጅ የተፈጠረበት ዓላማ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው) ከሚያሳካባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ ካለስግደት ሥጋውን ፍጹም መኮነን(መግዛት) አይችልምና ሰብእናው ምሉዕ አይሆንም፡፡

፨ስግደት ስንት ዐይነት ነው?፨

 

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ከአፈጻጸም ሥርዐት አንፃር ስግደት በሦስት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው የስግደት አፈጻጸም ሥርዐት መሬት ላይ በመውደቅ ወይም ሙሉ በሙሉ ተደፍተው የሚሰግዱት ስግደት ሲሆን በልዩ ስሙ ‪#‎ወዲቅ‬ በመባል ይታወቃል፡፡ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት” የሚለው በሊቃውንት የተዘጋጀው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ይህንን የስግደት ዐይነት ‪#‎ሰጊድ‬ /Prostration/ ብሎ ገልጾታል፡፡(ገጽ 85) ዮሐንስ ወንጌላዊ “ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ።”/ራእ.19፡10/ ያለው ወዲቅን እንደተገበረ የሚያሳይ ነው፡፡ መደፋቱ ከድንጋጤ ወይም ከመፍራት ወይም ከመታመም የመጣ እንዳልሆነ ሲነግረን “ልሰግድለትም” አለ፡፡ በእግሩ ፊት የተደፋው ሊሰግድለት መሆኑን አስረዳ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ” /ዘፍ.19፡1/ “ሰገደም በግንባሩም ተደፋ” /ዘኁ.22፡31/ “በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ” /ኢያ.5፡13/ “ማቅ ለብሰው በግንባራቸው ተደፉ” /1ኛ ዜና.21፡16/ “በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ” /2ኛ ነገ. 2፡15/ “በእግሩ አጠገብ ወደቀች፤ በምድርም ላይ ተደፋች” /2ኛ ነገ.4፡8/ “ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት” /ሐዋ.10፡25/ የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ወዲቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው የስግደት ዐይነት መሆኑን የሚያስረዱ ናቸው፡፡
ሁለተኛው የስግደት ዐይነት ‪#‎አስተብርኮ‬ /Kneeling/ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ስያሜው እንደሚጠቁመው ጉልበትን ሸብረክ በማድረግ፣ በጉልበት በመቆም ወይም በመንበርከክ የሚፈጸም ነው፡፡ ወዶ ፈቅዶ ራሱን ዝቅ አድርጎ በድኅነት ከፍ ላደረገን ክርስቶስ የአምልኮ ስግደትን መስገድ እንዲገባ ሲያጠይቅ “በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ… ነው” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊሊጲስዩስ በላከው መልእክቱ የአስተብርኮ ስግደትን ለክርስቶስ መስገድ እንደሚገባ አስረድቷል፡፡ /ፊል.2፡10/ ምንም እንኳን እያሾፉ ቢሆንም በማር. 15፡19 ላይ አይሁድ ለስም አጠራሩ ክብር ይሁንና ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ “ተንበርክከውም ሰገዱለት” ይላል፡፡ ምንም እንኳን ስግደታቸው የሹፈት፣ የማላገጥ ቢሆንም ጥቅሱ በመንበርከክ መስገድ እንዳለ የሚጠቁመን ነው፡፡ በዚሁ ምእራፍ በማላገጥ እጅ ነሥተውት ነበርና እጅ መንሣታቸው የሹፈት እንደሆነው ሁሉ ስግደታቸውም የማሾፍ ነበር፡፡ እጅ በመንሣት አሹፈዋልና እጅ አይነሣም እንደማይባለው በመንበርከክ ሰግደዋልና በመንበርከክ መስገድ አይገባም አይባልም፡፡
አንዳንድ ሰዎች ተንበርክኮ መጸለይ፣ ተንበርክኮ መስገድ የእኛ ትውፊት አይደለም፤ የቤተክርስቲያን ሥርዐት አይደለም ብለው እንደሚያስተምሩና ተንበርክከው የሚጸልዩትንም እንደሚገሥጹ ጠቅሰው በዚህም የተነሣ ተንበርክኮ መጸለይንና በመንበርከክ መስገድን እንደሚፈሩ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ተግሣጹ ስሕተት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ሌሎች ያዙትና መጽሐፍ ቅዱስን መያዝ የኛ አይደለም እንደማለት አይነት ከንቱ ጨዋነት ነው፡፡ ሌሎች ደጋግመው ጌታ ጌታ ይላሉና ጌታ ማለት የኛ አይደለም እንደማለት ያለ አላዋቂነት ነው፡፡ (በርግጥ በምዕራባውያን ዘንድ ተንበርክኮ “አምልኮ”ን መፈጸም የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም በምሥራቁ ነገረ ሃይማኖት ተንበርክኮ መስገድም ሆነ መጸለይ የተከለከለበት ቦታ የለም፡፡)
ሦስተኛው የስግደት አፈጻጸም ዐይነት ‪#‎አድንኖ‬/Bowing/ ይባላል፡፡አድንኖ ራሥን፣ ግንባርን፣ አንገትን ዝቅ በማድረግ የሚሰገድ ነው - “አድንኑ አርእስቲክሙ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክነ…” እንዲባል በቅዳሴ፡፡ ይህም እንደቀደሙት ሁለቱ የስግደት አፈጻጸም ዐይነቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 49 ቁጥር 23 ላይ “ግንባራቸውን ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል” ይላል፡፡ ካህናትም “በንስሐ ውስጥ ያላችሁ ራሣችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ” ማለታቸው አድንኖን በመፈጸም ስገዱ ሲሉን ነው፡፡

ወዲቅም፣ አስተብርኮም ሆነ አድንኖ የስግደት አፈጻጸም ዐይነቶች ናቸው እንጂ ከስግደቱ ዓላማ ጋር ወይም ከሚሰገድለት አካል አንጻር የሚፈጸሙ አይደለም፡፡ በሌላ አገላለፅ ሦስቱን የስግደት ዐይነቶች ስግደት ለሚገባው ሁሉ እንፈጽማለን - ሦስቱንም ዐይነት ስግደት ለእግዚአብሔርም ለቅዱሳንም እናቀርባለን፡፡ ነገር ግን የመስገዳችን ምሥጢሩ ይለያያል፡፡ ይህንንም እንደሚከተለው እንየው፡፡
ስንዱዋ እመቤት ቅድስት ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ ከዓላማው አንፃር ሁለት ዐይነት ስግደት እንዳለ ታስተምራለች፡፡ በሌላ አገላለጽ ስግደቱ ከሚቀርብለት አካል ማንነት አንጻር ስግደት በሁለት ይከፈላል፡፡

‪#‎የመጀመሪያው‬ ለእግዚአብሔር የምንሰግደው የስግደት ዐይነት ሲሆን የአምልኮ /የባሕርይ/ ስግደት ይባላል፡፡ /የአምልኮ ስንል በባሕርዩ አምላክ ለሆነው ማለታችን ነው፤ በጸጋ አማልክት የተባሉ እንደ ሙሴ ያሉ ቅዱሳን አሉና - ዘጸ.7፡1/ ይህን ስግደት አንድ አምላክ ከሚሆን ከእግዚአብሔር ውጭ ለማንም መስገድ አይቻልም፡፡በዘወትር ጸሎት ላይ “እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐተ ስግደተ - ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደትን እሰግዳለሁ” ማለቱ ይህንን ምሥጢር የሚገልፅ ነው፡፡“አሐተ - አንዲት” የሚለው የስግደቱን መጠን ወይም ቁጥርን ለመግለፅ ሳይሆን ስግደቱ በባሕርዩ ለሚመለክ ለአንድ አምላክ የሚሰገድ ፣ ለሌላ አካል የማይሰገድ የአምልኮ ስግደት መሆኑን ሲጠቁመን ነው፡፡ “አንድ ጊዜ ብቻ ስገዱ” ብሎ ቁጥርን ለማመልከት ቢሆን ዝቅ ብሎ “3 ጊዜ በል” ብሎ አንዲት ስግደት የሚለውን 3 ጊዜ እያልን ሦስት ጊዜ እንድንሰግድ አያዘንም ነበር፡፡ “አንዲት” የሚለውን ቃል እንዲህ መተርጎማችን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነትን ይዘን ነው፡፡ ብሥራተ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሊያበሥር መላኩን ቅዱስ ሉቃስ ሲገልጽ “ወደ አንዲት ድንግል ተላከ” /ሉቃ.1፡27/ ብሏል፡፡ “አንዲት ድንግል” የሚለው ቁጥርን ሳይሆን የድንግሊቱን ልዩ መሆን የሚጠቁም መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ እሷም ድንግልናዋም የተለዩ መሆናቸውን የሚገልፅ ነው፡፡ ቁጥርን የሚገልፅ ነው ከተባለማ በዚያን ጊዜ በምድር ላይ አንዲት ድንግል ብቻ አለች ወይም በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ያሉ ድንግሎች ብዛት ሁለት እንኳን አይሞላም ወደ ሚል ስሌት ይመራናል፡፡ ዕለቱን እንኳን ሺ የሚወለዱ ሕፃናት ደናግላን አሉ፡፡ በተመሳሳይም በዮሐንስ ራእይ “አንዲት ሴት ነበረች” /ራእ.12፡1/ ሲል በምድር ያሉት ሴቶች ሁለት እንኳን አይሞሉም ለማለት ሳይሆን የሴቲቱን ፍጹም የተለየች መሆን፣ ወይም በእሷ ደረጃ የሚገኝ ሌላ ሴት/ፍጡር አለመኖሩን ሲገልፅልን ነው፡፡ ብዙ ሴቶች በምድር እንደነበሩማ መጽሐፍ ቅዱሳችን በብዙ ቦታ መስክሯል፡፡በተመሳሳይም ከላይ ጸሎተ ሃይማኖታችንም አንዲት ስግደት ማለቱ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባ መሆኑን ሲያመለክት ነው፡፡
ሁለተኛው ጸጋ እግዚአብሔርን ላገኙ ቅዱሳን ሁሉ የሚሰገድ የጸጋ ስግደት ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ፣ ቅዱስ መስቀል ፣ ቅዱሳን መላእክት ፣ ሰማዕታት ፣ ፃድቃን ፣ ቅዱሳን ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፣ ቅዱሳን ቦታዎች ፣ ታቦት ፣ ቅዱሳት ንዋያት እዚህ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ የዘወትር ጸሎት “ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደትን እሰግዳለሁ” ብሎ አያቆምም፤ “አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያምም እሰግዳለሁ፤ ዓለምን ሁሉ ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀልም እሰግዳለሁ” በማለት የጸጋ ስግደትን ለቅድስት ሥላሴ ከሚሰገደው የባሕርይ ስግደት ለይቶ እግዚአብሔር ለቀደሳቸው ሁሉ እንደሚገባ የሚያስረዳ ነው፡፡ እኛ የዘወትር ጸሎት የሚባል ነገር አናውቅም… የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አምጡ የሚሉም ካሉ እንደሚከተለው እናስረዳለን፡፡

፨ለቅዱሳን መስገድን ያስተማረው እግዚአብሔር ነው!፨

መጽሐፍ ቅዱስ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ለቅዱሳን መስገድ አንደሚገባ ያስረዳል፡፡ በዘፍ. 27፡29 “አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፥ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን።” ብሎ ልጁን ያዕቆብን የባረከው ይሥሐቅ ነበር፡፡ ይህን ምርቃት ማግኘት የነበረበት የያዕቆብ ታላቅና በኩር የነበረው ኤሳው ቢሆንም ያዕቆብ በእናቱ ብልኃት ታግዞ ተመረቀ፡፡ ይሥሐቅን እንዲህ ብሎ እንዲመርቅ ያደረገው እግዚአብሔር አምላክም የአብርሃም ፣ የይሥሐቅና የኤሳው አምላክ በመባል ፋንታ የአብርሃም ፣ የይሥሐቅና የያዕቆብ አምላክ ተባለ፡፡ አምላካችንን ሙሴ ማነህ ብሎ በጠየቀው ጊዜም ራሱን ሲገልፅ እርሱ ራሱን ለአብርሃም ለይሥሐቅና ለያዕቆብ የሚገለጥና ምድረ ርስትንም ሊሰጣቸው ቃል እንደገባ ለሙሴ ገልፆለታል፡፡ ስለዚህ በይሥሐቅ አንደበት አድሮ ያዕቆብን የመረቀው እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህንን የሚጠራጠሩ ቢኖሩ እንኳን የይሥሐቅን ምርቃት የፈጸመው /እንዲደርስ ያደረገው/ እግዚአብሔር ነው፡፡ ታዲያ አምላካችን ለቅዱሳን የሚገባን ስግደት የሚቃወም ቢሆን ይሥሐቅን “ሕዝብም ይስገዱልህ” ብሎ ሲመርቅ አይገሥጸውም ነበርን? ባይገሥጸው እንኳን “ልጆች ይስገዱልህ” ብሎ የመረቀ ይሥሐቅን ምርቃቱን ባለመፈጸም /እንዲደርስ ባለማድረግ/ ቃሉ ልክ እንዳልሆነ አያሳይም ነበርን? ደግሞስ ለፍጡር በሚገባ መስገድ ስሕተት ቢሆን ከብዙ ዘመን በኋላ ያዕቆብ ከነቤተሰቡ ለኤሳው በመስገድ የአባቱን የይሥሐቅን “ስሕተት” ይደግመው ነበርን?
ከዘፍ.37-41 ድረስ የፃድቁን የዮሴፍን ታሪክ እናገኛለን፡፡ በዚህ ክፍል እግዚአብሔር ለዮሴፍ እንደሚሰገድለት የሚተነብይ ሕልም አሳየው፡፡ “እኔ ያለምሑትን ሕልም ስሙ፡ እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናሥር ነበርና፤ እነሆም የእኔ ነዶም ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከበው እነሆ ለኔ ነዶ ሰገዱ” /ዘፍ.37፡7/፡፡ ወንድሞቹ ከሕልሙ የተነሣ እንደሚሰግዱለት ተረድተው ወንድማቸው ዮሴፍን ይበልጥ ጠሉት፡፡ለቅዱሳን አንሰግድም ብለው ቅዱሳንን የማያከብሩ ሰዎች በትዕቢት ራሳቸውን ከቅዱሳን በላይ በማድረግ፣ ወንድማቸውን ዝቅ ያደረጉትን የዮሴፍን ወንድሞች ይመስላሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን ይህንን እንዲረዱት ዮሴፍ ነዶ በተባሉት በወንድሞቹ ብቻ ተሰግዶለት የሚቀር ሳይሆን በሌሎች ፍጥረታትም ዘንድ እንደሚከብር ሲገልፅላቸው ዮሴፍን ሌላ ሕልም ዐሳየው፡፡ “እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፣ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ ዐየሁ” /ዘፍ.37፡9/፡፡ እግዚአብሔር ተናግሮ ነገር አይቀርምና ወንድሞቹ እንዳይሰግዱለት፣ እንዳይገዙለት ሽተው ሊገድሉት ቢሞክሩም፣ ጉድጓድ ውስጥ ቢጥሉትም፣ ለነጋድያን ቢሸጡትም በሀገራቸው ሊፈጽሙት የከበዳቸውን ሐቅ ርሐብና ድርቅ ሲመጣ በባዕድ ምድር በግብፅ ሊያደርጉት ግድ ሆኖ ወንድሞቹ ለዮሴፍ መስገዳቸው አልቀረም፡፡ “የዮሴፍም ወንድሞች በመጡ ጊዜ በግምባራቸው በምድር ላይ ሰገዱለት” /ዘፍ.42፡6/፡፡ ለቅዱሳን አንሰግድም የሚሉ ሰዎች ምንም እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሊያጠፉት ሽተው ቢሰርዙና ቢደልዙትም፣ በቀላል አማርኛ በሚል ፈሊጥ ቃሉን ቢዘነጥሉትም፣ ጥቅስን ዘንጥሎ በመጣል ጉድጓድ ውስጥ ቢጥሉትም፣ አውጥተው ለሥጋዊ ስሜትና ለዓለም ክህደት ቢሸጡትም ርሐበ ነፍስ ድርቀተ መንፈስ ሲመጣ በሀገራቸው፣ በሕይወተ ሥጋቸው ያላደረጉትን እውነትን በሲዖል እንኳን ለማድረግ መጓጓታቸው አይቀርም፡፡ “የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ” እንዳለ ኢሳይያስ /ኢሳ.60፡14/፡፡ በምድር ምጽዋት የነፈገውን አልአዛርን በሲዖል በአብርሃም አማላጅነት እንደለመነው ነዌ፡፡ /ሉቃ.16፡20-31/፡፡
ጳዎሎስንና ሲላስን ለመሰሉ ቅዱሳን ለእናንተ የሚገባው ስግደት ሳይሆን መታሠር ነው ብለው ደብድበው ካሠሯቸው ሰዎች መኃል አንዱ የሆነው የእሥር ቤቱ ጠባቂ በእሥር ቤቱ ውስጥ በነጳውሎስ ዝማሬ ምክንያት ከደረሰው ታላቅ መናወጽ በኋላ ከሥራቸው ተደፍቶ ሰገደላቸው፡፡ “ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ” /ሐዋ.16፡29/ እንዲል ግብረ ሐዋርያት፡፡ የቅዱሳኑን ዝማሬ ሰምቶ እሥር ቤቱን አናውጾ ጠባቂውን እንዲሰግድ ያደረገው እግዚአብሔር አይደለምን?

እግዚአብሔር ቃል በቃል ለቅዱሳን ስግደት እንደሚገባ የተናገረበት ቦታን ለሚሻ ደግሞ እነሆ፡-

በራእየ ዮሐንስ ምዕራፍ ሦስት ላይ ሁለት የቤተክርስቲያን ጠባቂዎችን እናገኛለን፡፡ አንደኛው በሰርዴስ የሚገኘው መልአክ /ጠባቂ/ ሲሆን አንደኛው ደግሞ የፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን መልአክ /ጠባቂ/ ነው፡፡ የሰርዴሱ ጠባቂ ሥራው በአምላክ ፊት ፍጹም ያልሆነና በቁሙም ሞተሀል የተባለ ሲሆን እንዲነቃና ንስሐ እንዲገባ አግዚአብሔር አዟል፡፡ እንዲህ ካላደረገ ግን እንደሚፈርድበት “እመጣብሃለሁ” ሲል ነግሮታል፡፡ የፊልድልፍያው መልአክ /ጠባቂ/ ግን በእግዚአብሔር ፊት የተወደደና ቅዱስ ነበርና እግዚአብሔር እንዲህ አለው “ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፤ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና ስሜንም አልካድህምና፡፡ እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ” /ራእ.3፡8-9/፡፡
ለቅዱሳን ስግደት አይገባም የሚሉ ምንኛ ያልታደሉ ናቸው? “የተከፈተ በር ሰጥቼሀለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም” የተባለላቸውን ቅዱሳንን የሚመሰገኑበትን የጸጋ በር ሊዘጉ የሚሮጡ ምንኛ ምስኪኖች ናቸው? “እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር” የተባሉ ክርስቲያን ሳይሆኑ ክርስቲያን ነን የሚሉ ነገር ግን የሚዋሹ ምንኛ አሳዛኝ ናቸው? እነሆ ክርስቲያን ሳይሆኑ ክርስቲያን ነኝ በሚል ቅዠት ቅዱሳንን የማይወዱ የሰይጣን ማኅበር አባላት መባላቸው እንዴት የሚደንቅ ነው? እንደ ቅዱሳን ሁሉ እንዲ ሰጣቸው ተፈጥረው እነርሱ ራሳቸው ተላልፈው መሰጠታቸውና ባይወዱም እንኳን በቅዱሳን እግር ፊት መስገዳቸው የማይቀር መሆኑ እንዴት ግሩም ነው? በተዐብዮ ራሳቸውን እኔም እንደ እገሌ ቅዱስ ነኝ የሚሉ ዘባቾች ቅዱሳንን በትሕትናቸውና አንዱ ለአንዱ በመስገዳቸው የሚወድ እግዚአብሔር “እንዴት እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ” ብሎ ለቅዱሳን ቃል መግባቱ እንዴት ያለ ምሥጢር ነው?

(እግዚአብሔር ቢፈቅድ በሁለተኛው ክፍል መቼ መቼ እንደሚሰገድ ፤ ለመላእክት፣ ለቅዱሳንና ለቅዱሳን ንዋያት የሚሰገድ ስግደትን ፤ መላእኩ ዮሐንስን አትስገድልኝ የማለቱን ምሥጢር እናያለን፡፡ በሦስተኛው ክፍልም ከሰሙነ-ሕማማት ጋር በማያያዝ ስግደትን እናነሣለን፤ በተለይ የግዝት በዓላት በሕማማት ቢውሉ ይሰገዳልን የሚለውን ለመመለስ እንሞክራለን፡፡ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡)

 መ/ር /ሕሊና በለጠ

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine