የፍቅር ስጦታ

 በፍጹም ምራው

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዐቢይ ጾምን በሦስት ክፍል ስትጾም ቆይታለች፡፡ ይህም ማለት የመጀመሪያውን ሳምንት ንጉሥ ሕርቃል የሚታሰብበትን 40ውን ቀን ጌታችን በገዳመ ቆሮንጦስ የጾመውንና የጸለየውን በማሰብ የመጨረሻውን ሳምንት ደግሞ ሰሙነ ሕማማት በማለት ሰቆቃውን፣ መከራውን፣ የደረሰበትን እንግልትና ስቃይ በምንባባቱ፣ በዜማው፣ በስግደቱ ስታስብ ሰንብታለች፡፡

የጌታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ፍቅር ለበደለው ለሰው ልጅ የተዋለ ውለታ ነው፡፡ ‹‹በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸከመ . . . በእርሱም  ቊስል እኛ ተፈወስን፡፡›› ኢሳ. 53፥4 እንዳለ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማስተሥረይ መከራ ተቀበለ፡፡ ለባሕሪው ሕመም ድካም ሞት የሌለበት አምላክ አትብላ የተባለውን ዕፅ በልቶ ለዘመናት እግዚአብሔርን የመሰለ ጌታውን ገነት የመሰለ ቦታውን አጥቶ በዲያብሎስ ሲወገርና ሲቀጠቀጥ የነበረውን የሰውን ልጅ አዳምን መስሎ የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ ካሳ መክፈል የሚገባው ሰው ሆኖ ሳለ በአዳም ተገብቶ እሱ ራሱ እውነተኛ ካሳ ሊከፍል ተገረፈ፣ ተወገረ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ፡፡ ሠለስቱ ምዕት በጸሎተ ሃይማኖታቸው ‹‹በጲላጦስ በሹመት ዘመን ስለእኛ ታመመ ስለእኛም ተሰቀለ ሞተ ተቀበረ›› ብለው ስለኛ የከፈለውን ክፍያ ይናገራሉ፡፡ እንግዲህ ይህ የሚያሳየው ቤተክርስቲያናችን ትንሣኤከ ብላ ከመዘመሯ አስቀድማ ሕማሙንና መከራውን በእንባ በስግደትና በፍጹም ሐዘን ማሰቧ የደስታህ ብቻ ሳይሆን የመከራህም ተካፋይ ነን ስትል ነው፡፡ ይህ ሥርዓቷ ደግሞ ከሁሉም ፋሲካን እናከብራለን ከሚሉ አካላት ይለያታል፡፡

ስቅለቱን ስለ እኛ ብሎ መሞቱን በመቃብር መግባቱን እያሰበች እህል በአፋችን አንቀምስም ብለው የቻሉ ከሐሙስ ማታ ያልቻሉ ደግሞ ከዐርብ ማታ ጀምረው በማክፈል ‹‹ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ›› እያሉ እየዘመሩ ትንሣኤውን በታላቅ ጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ ‹‹እውነት በእውነት ጌታችን ከሙታን መካከል ተነሣ›› በማለት መነሣቱን በማወጅ ቅዳሴ ቀድሳ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ፈትታ ለምዕመናን በማቀበል ሥርዓቱን ትፈጽማለች፡፡

እንግዲህ ከላይ ለማንሳት የሞከርነው ቤተክርስቲያናችን ምን ያህል የክርስቶስን መከራና ሞት ትንሣኤ እንደምታስብ ለማጠየቅ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ደግሞ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከብዙ ዘመናት በፊት የነበራት ሥርዓት ነው፡፡ እንግዲህ ይህችን ቤተክርስቲያን ነው ስለ ክርስቶስ አልሰበከችም ብለው አንዳንድ አካላት የሚናገሩት ግን የቤተክርስቲያን ጌጧ፣ ሽልማቷ፣ ዝማሬዋ፣ ምንባቧ ሁሉ እሱ ራሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ያልተረዱትን ልቡና ይስጥልን ከማለት ሌላ ምን እንላለን፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ ለመላው ሕዝብ ማለትም ለሚያምንም ለማያምንም የተደረገ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅሩ ዘመን የማይሽረው የታተመ ሁሌም ሲወሳ ሲዘከር የሚኖር ነው፡፡ እንግዲህ ሰንበት ት/ቤታችንም ከተመሠረተበት ዕለት አንስቶ እስከ አሁን ጊዜ ድረስ ትንሣኤውን ከካህናትና ከነድያን ጋር እያከበረ ይገኛል፡፡ ሰሙነ ሕማማቱን በስግደትና ጾም ከማሳለፍ በተረፈ ከምዕመናን በረከቱን ያገኙ ዘንድ አልባሳቱንና ማስፈሰኪያውን ያሰባስባል፡፡ በሌሊቱም 55ቱን ቀን ሙሉ በጸሎትና በጾም ሲደክሙ የነበሩትን ካህናት አስፈስኮ ነድያንን መግቦና አልባሳትን አድሎ ሃይማኖታዊ ግዴታውን እየተወጣ በዓሉን ያከብራል፡፡

በመጨረሻም ብዙዎች ይህን የፋሲካ በዓል ከሥጋ ደስታ ጋር ብቻ ያወዳድሩታል ሆኖም ግን  የመንፈስም ደስታዋ ነውና በዓሉን በከብት ሥጋ ብቻ ሳይሆን አማናዊ በሆነው የክርስቶስ ሥጋና ደም ልናከብረው ይገባል፡፡  በመላው ዓለም የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ እያልን ቀሪውን 50 ቀንም በጾሙ ያሳያችሁትን ትሕትና፣ ፍቅር፣ ጸሎትና ከእግዚአብሔር ጋር መሆንን አጠንክራችሁ ትቀጥሉት ዘንድ አደራ እንላለን፡፡ በየ ክፍለ ሀገሩና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ የሰንበት ት/ቤታችን አባላት ፋሲካውን እውነተኛ የፋሲካ በግ የተባለውን ክርስቶስን በመቀበል ነድያንን በመመገብ 50ውን ቀን ታሳልፉ ዘንድ ሰንበት ት/ቤቱ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ሃይማኖታችንን ይጠብቅ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine