ምጽዋት

 ‹‹በሰንበት ት/ቤቱ በጎ አድራጎት ዋና ክፍል››

ምጽዋት ሰው ለሚሹት ሰዎች ወጥቶ ወርዶ በድካሙና በወዙ ባሻው ገንዘቡ አበድሬ እቀበላለሁ ሳይል የሚፈጽመው ርኅራኄ ነው፡፡ ስለሆነም ምጽዋት ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ጻፈው የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ምጽዋት፣ ቸርነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ንጽሕና ነው፡፡ ሰንበት ት/ቤታችንም ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱን ለመፈጸም ነድያንን እና አረጋውያንን ይመግባል ያለብሳል፡፡ እንዲሁም በመጻሕፍት የሰማይ አባታችሁ ቸር ርኅሩኅ እንደሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ ተብሎ የታዘዘውን ትእዛዝ መሠረት በማድረግ እንደ ቤተክርስቲያን ልጅነታችን የተራበውን ቆርሶ ማብላት፤ የተጠማውን ማጠጣት፤ የታረዘውን ማልበስ፤ የተቸገረውን በመርዳት አገልግሎታችንን በእግዚአብሔር ፈቃድ እናከናውናለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጻሕፍት እንደተናገረው ‹‹ገንዘባችሁን ሸጣችሁ ለነዳያን ምጽዋት ስጡ›› በማለት አዝዞናልና፡፡ ምዕመናንን በማስተባበር ከበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑና ትእዛዙንም እንዲፈጽሙ በማድረግ የሚያስደስት አገልግሎትን እንፈጽማለን፡፡ ነድያን (ድሆች) የሚባሉትም የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ የሌላቸው ጦም አደሮች ናቸው፡፡ ሙሉ አካል ኖሯቸው ዕድሜአቸውን በልመና ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡ የአካል ጉድለት ደርሶባቸው ወጥተው ወርደው ራሳቸውን መርዳት ባለመቻላቸው የሰውን እጅ ለማየት ይገደዳሉ፡፡ ማንኛውም ሰው ከእናቱ ማኅፀን ራቁቱን እንደወጣ ወደ መቃብር ሲወርድም የሚያስከትለው ሀብት የለም፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቸርነት የጎደለው ሞልቶለት የጠመመው ተቃንቶለት የሠራው ተባርኮለት ምድራዊ ሀብት እያለው ድሆች በረሃብ ሲረግፉ እያየ ብዙ ሀብት ላከማች ከማለት ይልቅ ለድሆች ሊያካፍል ይገባዋል፡፡ ያዕ. 5፥1-4

ምጽዋት ሀብትን ብል በማይገኝበት፤ ዝገት በማያጠፋበት፤ ሌቦችም አጥሩን ጥሰው፥ ግድግዳውን ምሰው፥ ግንቡንም አፍርሰው በማይወስዱበት ሥፍራ ኅልፈት ጥፋት በሌለበት በሰማያዊ መዝገብ ማከማቸት ነው፡፡ ገንዘብን ይጠፋል ተብሎ በማያሰጋበት በማይጠረጠርበት ቦታ በሰማይ ባንክ ቤት ማስቀመጥ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንቀጸ ምጽዋትን በሰማያዊ መዝገብ መስሎ ሲናገር እንዲህ አለ፡፡ ‹‹ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮሮጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ መዝገባችሁ ባለበት (ምጽዋታችሁ ባለበት) ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና›› ሉቃ. 12፥33

ሰንበት ት/ቤታችንም እነዚህን ትዕዛዛት በማስመልከት በፋሲካና በሰንበት ት/ቤቱ ዓመታዊ በዓል ላይ ድሆችንና አረጋውያንን ይረዳል፡፡ የሚረዳበትም ዋና ምክንያት የሚከተሉትን ትእዛዛትና ግዴታዎችን ለመፈጸም እንዲሁም መንፈሳዊ በረከትን ረድኤትን ለማግኘት ነው፡፡

  1. ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በማሰብ ‹‹ጥቂት የዘራ ጥቂት መከሩን ያገኛል፡፡ ብዙ የዘራ ብዙ መከሩን ያገኛል››  መዝ. 111፥9 ‹‹ ገንዘቡን ለነድያን በተነ መጸወተ ጽድቁ ለዘለዓለም ይኖራል›› ስለዚህም የሚመጸውት ሰዋ ያተርፋል፡፡ እግዚአብሔር የምጽዋቱን ዋጋ ያበዛለታል፡፡
  2. እግዚአብሔርን ማክበር ነው፡፡ ‹‹ለድሀ ምሕረትን ማድረግ (መመጽወት) እግዚአብሔርን ማክበር ነው›› ምሳ. 14፥31 የሰው ልጅ በዚህ ዓለም ሲኖር መልካም ሥራ በመሥራት ትሩፋትን ምግባራትን መሥራት አለበት ካልሠራ ግን በሰፈረው መስፈሪያ ይሰፈርበታል፡፡ ማር. 4፥24
  3. ለነድያን ስንመጸውት ለአረጋውያን ስንረዳ እግዚአብሔርን መርዳት ነው፡፡ ማቴ. 25፥40 ‹‹ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት›› ይህን ቃል ይዘን ብልህ አዋቂ ሰው ከፈጣሪው ይችን ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናኖረው በወደድንም ጊዜ የምንቀበለው የአደራ ገንዘባችን ነው፡፡

‹‹ኃጢአትን በሚሠራና ምጽዋትን በማይመጸውት ዘንድ በጎ ሥራ የለም›› ሲራ. 12፥3

‹‹ሳትሞት ለባልንጀራህ በጎ አድርግ እጅህንም ዘርግተህ የተቻለህን ያህል ስጥ›› ሲራ. 14፥13

ከላይ የተዘረዘሩትን የእግዚአብሔርን ቃል በማሰብ ከአምላካችን ፍርድ እንድንድንና በረከትን እንድንቀበል ነዳያንን አረጋውያንን በመሰብሰብ ምዕመናንን በማስተባበር የተለመደውን በፋሲካ በዓል እንመግባለን፡፡

     ቤተክርስቲያን ሲባል የድሆች መጠጊያ መሰብሰቢያ ማለት ነው ለዚህም ነው ድሆችን የምንመግበው ከብዙ በጥቂቱ ይህን ይመስላል፡፡

                                  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine