አርብ /ስድስተኛው ቀን/

ð  ይህች ቀን አዳም ኋላም ሔዋን የተፈጠሩባት፣ ከገነት ተሰደው የወጡባት ዕለት ናት፡፡ ጌታም ቀድሞ የሥነ ፍጥረት ሥራውን እንደፈጸመበት አሁንም የድኅነት ሥራውን ፈጸመባት፡፡ በዚህች ዕለት በአምላካችን ላይ የተፈጸመው መከራ እጅግ አሰቃቂ ነበረ በፍጡርም ሊገለጹ የማይችሉ ናቸው፡፡

ð  የክብርን ባለቤት ጭፍሮች ይዘው በሊቀ ካህናት ቢት አቀረቡት፡፡ ሊቀ ካህናቱም ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆንክ ንገረን›› አለው ጌታም ‹‹አንተ አልህ . . . የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ›› ቢለው ሊቀ ካህናቱ ተሳደበ በማለት ፊቱን ነጨ ልብሱን ቀደደ፡፡ በኦሪት ሕግ እንዲህ ያደረገ ይሻር ትል ነበር፡፡ ጌታ እንደተሾመበት እርሱ እንደተሻረበት ለማጠየቅ፡፡

ð  ጌታ እንደተናገረው ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ካደው በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ ጌታ ያለውን አስታውሶም እንዲህ ሲል አለቀሰ ‹‹ከሁሉ ይልቅ እኔ እወደው ከሁሉ አስቀድሞ እኔ እክደው›› ብሎ ከልቡ ስላለቀሰ ንስሐውን ተቀብሎታል፡፡

ማቴ. 2669-75      ማር. 1466-72

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት በየሰዓታቱ የተፈጸመበት ድርጊቶች፡-

1.  ዐሥራ ሁለት ሰዓት ፡- በፍርድ አደባባይ ቆመ

-    በፍጥረታት ሁሉ ላይ የሚፈርደውን ሰማያዊ ንጉሥ በምድራዊ ንጉሥ ሊፈርዱበት በአደባባይ አቆሙት፡፡

2.  ሦስት ሰዓት ፡- ተገረ

-    ጲላጦስ መርምሮ  ወንጀል አጣበት ሕዝቡ ግን ስቀለው እያሉ መጮሃቸውን በቀጠሉ ጊዜ ቢገረፍ ልባቸው ይራራለት ይሆናል በማለት አስገረፈው፡፡ እነሱ ግን እንኳን ሊራሩ አርባ ጅራፍ ብቻ መግረፍ ሲኖርባቸው እየተፈራረቁ ክንዳቸው እስኪዝል /6666/ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪታይ ገረፉት፡፡

3.  ስድስት ሰዓት ፡- ተሰቀለ

-    ሱራፌል ኪሩቤል ያለ ማቋረጥ የሚያመሰግኑትን ክፉዎች አይሁዶች ዘበቱበት መላእክት በፍርሃት የሚያመሰግኑትን ተፉበት መቃም ይዘው ራሱን መቱት ከዚህ በኋላ ለመዘባበት ያለበሱትን ቀዩን ግምጃ ገፈው ወደ ሚሰቀልበት ቀራኒዮ ከባዱን መስቀል አሸክመው ወሰዱት፡፡ ከባዱን መስቀል መሸከሙ ከባዱን ኃጢአታችንን እንደተሸከመ የሚያጠይቅ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹. . . ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ›› እንዳለ /1ጴጥ. 222-24/

-    በግራም ሆነ በቀኝ የሚመጡ ወንበዴ እንዲመስላቸውና ‹‹ደግ አደረጉ የሥራው ነው›› እንዲሉ በግራና በቀኝ ወንበዴዎችን አድርገው ሰቀሉት፡፡ አሳይያስ በትንቢቱ ‹‹ከዓመፀኞች ጋር ተቆጠረ›› ያለው ተፈፀመ፡፡ /ኢሳ. 5312/

4.  ዘጠኝ ሰዓት ፡- ሞተ

-    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐሥራ ሦስት ሕማማተ መስቀል ከተቀበለ በኋላ የሰው ልጅ ያጣውን ሕይወቱን በሞቱ ለመካስ መራራ ሞትን በፈቃዱ ተቀበለ፡፡

ዳን. 926 ‹‹ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል በእርሱም ዘንድ ምንም የለም››   

ኢሳ. 536 ‹‹ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ፡፡››  

ዕብ. 926-28 ‹‹. . . አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል፡፡  . . .››

-    ስለዚህ በክርስቶስ ሞት በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም የገባው ሞት ተወግዷል ማለት ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕፀ መስቀል ላይ ሳለ ከመሞቱ አስቀድሞ ሰባቱን አጽርሐ መስቀል ተናግሯል እነርሱም፡-

1.   ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? /አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?/  ማቴ. 2746

2.   አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ /አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው/  ሉቃ. 2334

3.   ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት /ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ/  ሉቃ. 2343

4.   አባ አመሐፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ /አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ/   ሉቃ. 2346

5.   ነዋ ወልድኪ ነዎ እምከ /እነሆ ልጅህ እነኋ እናትህ/ ዮሐ. 1926

6.   ከመ ይብጻሕ ቃለ መጽሐፍ ይቤ ጻማዕኩ /መጽሐፍ በመብሌ ውስጥ ሐሞት ጨመሩ/ መዝ. 6821 ያለው ይፈጸም ዘንድ ተጠማሁ አለ፡፡ ዮሐ. 1928 እና 29                         

7.   ወይቤ ተፈጸመ ኵሉ /ሁሉ ተፈጸመ/   ዮሐ. 193

5.  ዐሥራ አንድ ሰዓት ፡- ተቀበረ

-    የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ ነበርና ሥጋቸው በመስቀል እንዳይውል ጭናቸው ተሰብሮ እንዲሞቱ ጲላጦስን ለመኑት እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ ሊሰብሩት ሲመጡ ግን ሞቶ አገኙት በዚህ ጊዜ ለንጊዎስ የሚባል ወታደር መሞቱን ሲያጣራ ጎኑን በጦር ሲወጋው ከጎኑ ደም እና ውሃ ፈሰሰ ይህም የምንጠመቅበት ማየ ጎቦ ነው፡፡

-    በሥውር የጌታ ተማሪ የሆነው የአርማትያሱ ዮሴፍና የአይሁድ አለቃ ኒቆዲሞስ ሥጋውን ከጲላጦስ ለምነው ሲፈቅድላቸው እንደ አይሁድ የአገናነዝ ሥርዓት ከሽቶ ጋር በተልባ እግር ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት›› እያሉ ገንዘው ማንም ባልተቀበረበት በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡

-    ምነው ቀዱሳን ነቢያት ባረፉበት መቃብር ያልተቀበረ ቢባል፡፡ ኋላ በትንሣኤ ሲነሳ የነቢያት አጽም አስነሳው እንጂ መች በስልጣኑ ተነሳ ባሉ ነበርና እንዲያ እንዳይሉ በአዲስ መቃብር ተቀበረ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ማርያም መግደላዊትና የዮሳ እናት ማርያም ይመለከቱ ነበር፡፡

ማቴ. 2757-61     ማር. 1542-47       ሉቃ. 2350-56      ዮሐ. 1931-37

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine