ሰሙነ ሕማማት

ሰሙነ ሕማማት

መድኃኔዓለም ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ የተመላለሰው ከክብሩ የተዋረደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ ሊመልሰው ፈቅዶ ነው፡፡ ይህንኑ ሲያጸና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር ይኸውም ዲያብሎስ ነው በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡›› /ዕብ. 21415/ብሏል፡፡ አምላክ በፍጹም ፍቅር ተስቦ የሰውን ልጅ ሊያድን ቢወድም የሰው ልጅ ግን በመልካም አልተቀበለውም፡፡ ‹‹የእርሱ ወደ ሆነው መጣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም››  /ዮሐ. 111/ ቢራቡ ስላበላቸው ቢታመሙ ስለፈወሳቸው ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር›› ሆነና እንዲሞት ተማከሩበት፡፡ ከመሆኑ ከመታሰቡ አስቀድሞ ሁሉን የሚያውቀው አምላክ ግን ብዙ ጊዜ ሊይዙት ቢሞክሩም ጊዜው አልደረሰም ነበርና በእጃቸው አልወደቀም ነበር፡፡

ነገር ግን የዚህ ዓለም ሥራውን ሲፈጽም የሰው ልጅ ድኅነት እጅግ ውድ የሆነ ካሳን የሚጠይቅ ነበርና ያን ለመክፈል በፈቃዱ ራሱን ለሕማምና ለሞት አሳልፎ ሰጠ ይህም ድኅነታችን የእግዚአብሔር ልጅ ደሙን እስኪያፈስለት ድረስ የቱን ያህል ውድ መሆኑን የሚያስተምር ነው፡፡ ዮሐንስ በራእይ መጽሐፉ ‹‹መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ታርደሃልና በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው በምድርም ላይ ይነግሣሉ፡፡›› /ራዕ. 5910/ በማለት ድኅነታችንን በታላቅ የደም ካሳ የተገኘ መሆኑን የገለጸው፡፡

ሰሙነ ሕማማት የሚለውም ቃል ይኸው የድኅነት ሥራ የተፈጸመበትን ሰሙን (ሳምንት) የሚያመለክት ነው፡፡ ሕማማት የሚለው ቃል ሐመ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ሕማማት እያልን የምናነሳው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ ድኅነት ሲል ወዶ የተቀበላቸውን ልዩ ልዩ ጸዋትዎ መከራዎች የሚመለከት ነው፡፡

በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ በፊት ያለው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ሰሞን ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን ቤተክርስቲያን ባወጣችው ሥርዓት ጸሎት መሠረት የተደረገላቸውን ታላቁን ውለታ በማሰብ በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው ከበፊቱ አብዝተው በመጾም በመጸለይና በመስገድ ከኃጢአት እርቀው የሕማሙን ነገር የሚያወሳ ዜማ ሲያዜሙ ግብረ ሕመማት በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ ሲያነቡ ይሰነብታሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ ሕመማትን መቀበሉ ስለምን ነው ቢሉ፡-

ð  ፍቅሩን ለመግለጽ፡- ለፍጥረቱ ይልቁንም ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅሩን ይገልጽ ዘንድ  ‹‹. . . እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡ ›› /ዮሐ. 316/ ‹‹ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከማኖር ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም፡፡›› /ዮሐ. 1513/ ምንም በደል ሳይኖርበት ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡

ð  የኃጢአት ፍዳ ከባድነት ለማሳየት፡- እርሱ ጻድቅና ንጹሕ ሆኖ ሳለ ሰውን ወዶ ይህን ያህል መከራ ከተቀበለ ሰው ኃጢአት በመሥራት ቢመላለስ የኃጢአትን ውጤት ከባድነት ያስተምረናል፡፡ ራሱ ጌታችንም ከጲላጦስ ግቢ እስከ ቀራንዮ አደባባይ መስቀል ተሸክሞ ሲንገላታ ላለቀሱለት ለኢየሩሳሌም እናቶች ‹‹በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ በደረቀውስ እንዴት ይሆን?›› /ሉቃ. 2331/ በማለት ገልጽዋል፡፡

ð  ቤዛ ለመሆን፡- በኦሪት ዘመን ሰዎች ለሠሩት ኃጢአት ኃጢአታቸውን ለማስተስረይ ነውር የሌለበትን በግ ቤዛ እንዲሆናቸው መስዋዕት ያቀርቡ ነበር ይህ ግን ከአዳም የተወረሰውን ኃጢአት ማስቀረት ስላልቻለ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ መጣ፡፡ ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› /ዮሐ. 129/

ð  እርግማናችንን ለማስቀረት፡- ‹‹በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለእኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን›› /ገላ. 313/ በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው እርግማናችን ተሸክሞ ሕማማትን መቀበሉ የቀድሞው ኃጢአት ምንም ያህል ከባድ ቢሆን በታላቅ መስዋዕትነት እንዳስቀረልን ሊያስተምረን ነው፡፡

ð  የድኅነታችንን ክቡርነት /ውድነት/ ሊያስረዳ፡- ድኅነታችን የእግዚአብሔር ልጅ ደሙን እስኪያፈስለት ድረስ እጅግ ውድ መሆኑን ሊያስተምረን፡፡

 የሰሙነ ሕማማት ዕለታት

1.  እሑድ /ሆሣዕና/

      የመጀመሪያው ቀን ሆሣዕና ይባላል ትርጉሙም ‹‹እባክህ አሁን አድን›› ‹‹መድኃኒት›› ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን የማዳን ሥራውን ወደ ሚፈጽምባት ወደ ኢየሩሳሌም መግባት ይነገርበታል፡፡ ሲመጡም ሳሉ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ ያስፈልጉኛልና የታሰሩትን አህያና ውርጫ ይዛችሁልኝ ኑ ብሎ ላካቸው፡፡ በምሥጢሩ እኛን ከታሰርንበት የኃጢአት ማዕሰር ሊፈታን እንደ መጣ ለማጠየቅ ነው፡፡ እነርሱም እንደታዘዙት ይዘው መጡ ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተመቅደስ 16 ምዕራፍ ሲሆን 14ቱን በእግሩ ሂዶ 2ቱን በአህያ ሂዶ ቤተመቅደሱን 3 ጊዜ በውርንጫዋ ዙሮ ወደ ቤተ-መቅደስ ገባ፡፡ ቀድሞ ነቢያት ዘመነ ጸብዕ (ጥል) በሆነ ጊዜ በፈረስ ተቀምጠው የጦር ዕቃ ይዘው ይታዩ ነበር ዘመነ ሰላም የሆነ ጊዜ ደግሞ በአህያ ተቀምጠው መነሳነስ ይዘው ይታያሉ እርሱም ዘመነ ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲል በአህያ ተቀምጦ መጣ፡፡ ‹‹ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል፡፡›› /ሉቃ. 1942/ ነቢዩ ዘካርያስም በትንቢቱ በአህያ እንደሚመጣ ሲናገር ‹‹ . . . ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡›› /ዘካ. 99/ በግራና በቀኝ የነበሩትም እንኳን አንተ የተቀመጥክባትም አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም እያሉ ግማሹ ልብሱን ግማሹ የዘንባባ ዝንጣፊ አነጠፉለት፡፡ አብርሃም ይስሐቅን ይስሐቅ ደግሞ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ እስራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ ዮዲት ሆሎፎርአስን በገደለች ጊዜ ዘንባባ ይዘው አመስግነው ነበርና በዚያ ልማድ ጌታችንንም ዘንባባ ይዘው ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ አመሰገኑት፡፡

      ከዚህ በኋላ ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ በዚያ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል እናንተ ግን የወንበዴ ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ በመቆጣት የለዋጮችን ገበታ እየገለበጠ አስወጣቸው፡፡ አይሁድም ሕጻናት ሲያመሰግኑት ሰምተው በቅንአት በታወረ ልቦናቸው ‹‹ዝም አስብላቸው እንጂ›› ቢሉት ‹‹ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋና ለራስህ አዘጋጀህ›› /መዝ. 82//የሚለው የመጽሐፍ ቃል ጠቅሶ አሳፍሮአቸዋል፡፡

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine