ኒቆዲሞስ

የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ ኒቆዲሞስ የተባለ አይሁዳዊ ማታ ማታ ጌታ ዘንድ እየተገኘ ይማር ነበር ይህ ይታሰብበታል፡፡ ዮሐ. 3፥1-15

ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን ሲሆን በኢየሩሳሌም በሀብት ቢሉ በእውቀት እንዲሁም በሥልጣን የአይሁድ አለቃ ነበር፡፡

እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ‹‹መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህ ተአምራቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለንና አለው›› ዮሐ. 3÷2

በሌሊት ይመጣ ነበር ለምን አለ?

አይሁድ ‹‹ማንም ከእኛ ወገን ከሆነ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ከሆነ ሀብትና ንብረቱ ይወሰድ፣ በቤተመቅደስ አይግባ፣ መሥዋዕት አይሰዋ›› ብለው ነበርና አይሁድን ፈርቶ ሀብት ንብረቱን ወዶ እንዳይታወቅበት በሌሊት ይመጣ ነበር፡፡

በሌላ በኩል የቀን ልብ ባካኝ ነው፡፡ ዓይን ብዙ ያያል ሐሳብ ይበታተናል፡፡ በተሰበሰበ ልብ ለመማር፣ በተጨማሪ ሊቅ ነኝ እያለ እስከ ዛሬ ትምህርት አልጨረሰም እንዳይሉት በሌሊት ይመጣ ነበር፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳን ለመማር የመጣውን እሱን ይቅርና ጌታችን እየሄደ ያስተምር  ነበርና ኒቆዲሞስ ምንም በሌሊት ቢመጣም ማወቅን ፈልጎ ነውና ስለ ዳግም መወለድ፣ ስለ ጥምቀት፣ በእግዚአብሔር ልጅ ስለማመንና ስለ ጽድቅ ሥራ በዝርዝር አስተምሮታል፡፡

ኒቆዲሞስ በመጨረሻው ቀን በዕለተ ዓርብ በስቅለቱ ጊዜ ከመስቀል ላይ ሥጋውን ለማውረድና ገንዞ ለመቅበር ቀድሞ ተገኝቷል፡፡  ዮሐ. 19፥38

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine