ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ተራራ ማለት ነው፡፡ ደብር መባሉ ከፍታውን ሲገልጽ ዘይት ደግሞ አካባቢውን የሸፈነው የወይራ ዘይት ስለነበረ፤ ከፍሬውም ዘይት ስለሚገኝ ደብረ ዘይት ተብሏል፡፡ ይህም የወይራ ዛፍ የበዛበት መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህም ቦታ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ካለው ከቄድሮስ ሸለቆ ራቅ ብሎ የሚገኝ፣ ርዝመቱ 2 ኪሎ ሜትር ከፍታው ደግሞ ከኢየሩሳሌም ከተማ በላይ 62 ሜትር ያህል ከፍ በማለት ያለ ተራራ ነው፡፡ /ዘካ. 14፥4፤ ሕዝ. 11፥23/ ይህ ተራራ ጌታ የሚመጣበትን ምልክት የገለፀበትና /ማቴ. 24፥1/ የዚህን ዓለም ተልኮ ሲያጠናቅቅ የዐረገበት ተራራ ነው፡፡ /ሐዋ. 1፥12/ ጌታችን የሆሣዕና ዕለት ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ከደብረ ዘይት ሲሆን ቤተ ፋጌና ቢታንያም የሚገኙት ከዚሁ ተራራ ግርጌ ነው፡፡ /ማር. 11፥1/  ይህ ደብረ ዘይት የሚባለው ሰንበት ስለምጽአት የተነገረበት ከመሆኑም በስተጀርባ በዚህ ዕለት ምጽአት እንደሚሆን ይታመናል፡፡ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ስለ ቅድመ ምጽአቱ ምልክት በተናገረበት ተራራ ስም ደብረ ዘይት እየተባለ ይጠራል፡፡

 

የእግዚአብሔር ዳግም ምጽአት እንደ ቀዳማዊ ምጽአት ዐዋቂዎችን ባለማወቅ ገድቦ በአንድ ቦታ ብቻ የሚታይና የሚሰማ ሳይሆን እንደ ፀሐይ አወጣጥ፣ እንደመብረቅ ብልጭታ፣ እንደዘመነ ኖኅ ውኃ ለሁሉ በተዳረሰና ለሁሉ በተገለጠ መንገድ የሚከናወን ነው፡፡  ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን ግለሰባዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ የሆኑ ፈተናዎችን በራስ ሕይወት ላይ ማሳለፍ ግድ ይላል ስለዚህ ቀን የተናገረበትን ዕለት እንጂ ይህ ዕለት መች እንደሆነ ተጠንቅቀን ከመኖር የላቀ ክሂሎት አልተሰጠንም፡፡ ምልክቶቹንም ለማወቅ /ማቴ. 244/ ጀምሮ መመልከት ይቻላል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 ምንጭ፡- ማሕቶተ ዘመን

ኪዳነ ጽድቅ

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine