መፃጕዕ

መፃጕዕ ማለት በሽተኛ /ድውይ/ ማለት ነው፡፡ ይህ ቀን የሚያመለክተው የሕመምተኞችን ብዛት የሸፈነው የአብ ጸጋ ክሂሎት ከፍጡራን መካከል ወደር ያልተገኘለት መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ከብዙ ዓይነት በሽታ ከተያዙት በሽተኞች ብዛት ይልቅ በአንድ ጌታ ሥልጣን በብዙ በሽተኞች ላይ የሚካሄደው የፈውስ ጸጋ ጥበቡ በዓለም ላይ እጅግ የበዛ መሆኑ ነው፡፡ ጌታችን ከፈወሳቸው በሽተኞች መካከልም ረጅም ዕድሜ በሕመም ያስቆጠሩ ሰዎች ይገኙበታል፤ ይኸውም ዕድሜ ከ12 ዓመት እስከ 38 ዓመት የሚደርስ ነው፡፡ /ሉቃ. 13፥10 ማቴ. 9፥20/ እንዲሁም ከእናታቸው ማኅፀን ያለ ዓይን ብርሃን የተወለዱ ነበሩ፡፡ ከዚያም ባሻገር ሙተው የተነሡና በሕይወት ዘመናቸው በአጋንንት ፈተና የሚሰቃዩ ብዛት ያላቸው ሰዎች ይገኛሉ፡፡ /ማቴ. 8፥28/ ይህ ታሪክ በየዕለቱ የሚነገር መለኮታዊ ተግባር ቢሆንም ቤተክርስቲያን ከዚህ ለየት ላሉት ትምህርተ መለኮትና ሥነ ምግባር ጊዜ ለመስጠት ይህን ታሪክ በሚያመች መልኩ ረጅሙን ታሪክ ሰብሰብ አድርጋ በዚህ በአራተኛው እሑድ ፈጣሪዋን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈዋሴ ድውያን በማለት ታመሰግናለች፡፡ እንዲሁም በ4ኛው ክፍለ ዘመን /በዘመነ ነገሥት/ በፈሳሽ  ውኃ በሽተኞችን የማጥመቁ ሥርዓት በስፋት ይከናወን ስለነበር ይህ አራተኛ ሳምንት መፃጕዕ ይባላል፡፡

የአዳም ፈጣሪ ለዕረፍት ሰንበትን ሠራ፡፡ አይሁድም በማን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ አሉት፤ እርሱም እኔ እሠራለሁ እናንተም ሥራዬን እመኑ አላቸው፡፡ የሰንበት ጌታ እኔ ነኝ፤ የሰንበት ጌታዋ የአብ አንድያ ልጁ ነው፡፡ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር እል፣ ነጻነትን እሰብክ፣ የዕውራንን ዓይን አበራ ዘንድ አባቴ ልኮኛል አላቸው፡፡

ለአዳምና ለልጆቹ ዕረፍተ ሰንበትን የሠራውን ጌታ የሰንበት ትርጉም ያልገባቸው ሰዎች ይህን ዕረፍት እውን በሚያደርግበት ሰዓት ሰንበትን እንደሚሽር ቆጠሩት፡፡ ለመሆኑ በድቅድቅ ጨለማ ጥላ ሥር ለሚኖር ዓይነ ስውር ብርሃንን ከማየት፣በክራንች ለሚጓዝና በደረቱ ለሚሳብ፣ እንዲሁም በአካል ጉዳት ለሚያዘግም አንካሳ፣ በእግሩ እየዘለለ በፍጥነት ከፈለገው ቦታ ከመድረስ፣ የአእምሮና የማይታዩ የሰውነት ክፍሎች በሽታ ለወደቀባቸው፣ እንዲሁም በሚታየው አካላቸው ላይ ከባድና ቀላል በሽታ ላለባቸው ሰዎች ከበሽታ ተላቆ ያለፈውን የመከራ ጊዜ ከመርሳት የሚበልጥ ዕረፍት አለን? የለም

በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዷል /ማቴ. 12፥12/ በማለት ይህን ቃል የተናገረው ጌታችን ዓላማው፡- የተለያየ ችግር ዕረፍት የነሳቸውን ሰዎች ችግር ከላያቸው ቀርፎ እነርሱ የሚያርፉበትን አዲስ ሕይወት መመሥረት ነበር፡፡ ይህን የማድረግ ሥልጣንና ፈቃድ እንደ ሰዎች ከተያዘበት የበሽታ እሥራት ፈቶ ነጻነትን ሲያድለው በነፍሱም በኩል ያለው ረቂቅ ማሠሪያ አብሮ ይፈታል፡፡

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡- ማሕቶተ ዘመን

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine