ምኵራብ

ምኵራብ ማለት ሰቀላ መሰል አዳራሽ ማለት ነው፡፡ አይሁድ ስግደትና መሥዋዕት በኢየሩሳሌም ባለው መቅደስ ብቻ ነው ብለው ቢያምኑም /ዮሐ. 4፥20/ በተበተኑበት ቦታ ምኵራብ ሠርተው ትምህርተ ኦሪትን እየተማሩ ሃይማኖታቸውን ያፀኑ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ከጊዜ በኋላ ኢየሩሳሌም በሮማውያን ቅኝ ግዛት ሥር ወደቀችና ጭቆናው ከጊዜ ወደ ጊዜ በተራው ሕዝብ ላይ እየበረታ ሄደ፡፡ በመሆኑም ይህ ጭቆና የኑሮውን ውድነት ከዕለት ወደ ዕለት ያባብሰው ጀመር፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም እያንዳንዱ ለራሱ በሚመቸው መልኩ ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ በመምረጡ ሕዝቡ የማይወጣው ከፍተኛ ጫና ወደቀበት፤ ግማሹ የቄሳርን የሥራ አመራር በመጠጋት በገበያ ይቀርጣል፣ ሌላው የሃይማኖትን ነጻነት ሽፋን በማድረግ ፖለቲከኞችን አሳምኖና ከቀረጥ ነጻ ትሆናላችሁ በማለት ሕዝቡን አባብሎ ገበያውን ወደ ቤተመቅደሱ አንደኛ ግቢ ውስጥና በየምኵራቦቹ ውስጥ እንዲሆን አስወስኖ በቤተመቅደስ ዙሪያ በተለያየ ምክንያት ዘረፋውን ያጧጡፋል፡፡ እንዲህ መሆኑም መንፈሳዊያን ፖለቲከኞችና የጥገኝነት ፖለቲካ አራማጆችን ችግሩ አንድም ቀን ነክቷቸው አያውቅም፡፡ ይህ በመሆኑም የደሀው ኅብረተሰብ ንብረት በካህናት እጅ በተለያየ ስልት ሙልጭ ብሎ ገባ እንጂ ሕዝቡ አሁንም ቢሆን ያወቀው፣ የተረዳው ነገር አልነበረም፡፡

ይህ በሚሆንበት ጊዜ ስለሰው የሚጨነቀው ጌታ በኢየሩሳሌም ለነጻነት ተወልዶ ነበርና አዋቂዎቹንም ሕፃናቱንም  ከኃጢአት እሥራት ለመፍታቱ ምሳሌ፡- በዚህ ቀን በመለኮታዊ ጥበቡ ጅራፍ ለሽያጭ የታሠሩትን ሁሉ፡- ከብቱንም በጉንም ከእሥራታቸው ፈትቶ አሰናበተ፡፡ በራሳቸው በኃጢአት ሰንሰለት የታሠሩ ወንበዴዎች ሁሉ በእርሱ ተፈተውባታልና በዚህ ጊዜ የአባቴ ቤት ለመፈታትና ደግሞ ላለመታሠር የጸሎት ቤት እንጂ ለእሥራትና ለታሣሪዎች የወንበዴዎች ዋሻ አይደለችም አለ፡፡ እናም ይህ ቀን የቤተመቅደሱ የማንጻት ሥርዓት የተካሄደበት ዕለት በመሆኑና የምኵራብ ሥራ በይበልጥ የተስፋፋው በ3ኛው ክፍለ ዘመን በዘመነ ነገሥት በመሆኑ ይህ 3ኛው ሳምንት ምኵራብ ተብሏል፡፡

ኢየሱስ አይሁድ ምኵራብ ገብቶ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት መገናኛዋ እኔ ነኝ፡፡ የአብ አንድያ ልጅ የሰንበት ጌታ ነው፡፡ የአባቴን ቤት የሽፍታ መጠጊያ አታድርጉት፤ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፡፡ እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡፡ ከምኵራብ ገብተው ፀጥ ይሉ ዘንድ መከራቸው፤ ከቃሉ ግርማ፣ ከአነጋገሩ ጣዕም፣ ከአንደበቱ ቅልጥፍና የተነሳ በትምህርቱ ተገረሙ፡፡ /ማቴ. 7፥12፤ ማቴ. 21፥12፤ ማር. 11፥18/

የእግዚአብሔር ቤት የሆነው የጸሎት ቤት /ቤተመቅደስ/ ወይም የሰው ልቡና የመተሳሰብና የመረዳዳት ቤት እንጂ የሥጋ ገበያ ሊሆን እንደማይገባውም አስጠነቀቀ፡፡  የጸሎትና የመሥዋዕት ሥርዓተ አምልኮ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የሚኖረው ምግባር ሲቀና፣ ሃይማኖት ሲፀና ብቻ ነውና አንዱ ብቻውን ምንም ግዳጅ ስለማይፈጽም በእምነት ውስጥ ካለ አንድ ግለሰብ ሃይማኖትና ምግባር የሚጠበቅበት መሆኑን በጉልህ አሳየ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡- ማሕቶተ ዘመን /የዘመን መብራት/

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine