ዐቢይ ጾም

‹‹ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ››       በሚኪያስ ታደሰ ዘደብረ ኆኅተ ብርሃን

ጾም ማለት ለተወሰነ ሰዓት ለተመረጡ ቀናት ሰውነትን ከሚያበለጽጉ ፍትወትን ከሚቀሰቅሱ ምግቦች መከልከል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት በታወቁ ዕለታት (በሰባቱ አጽዋማት)  በታወቀው ሰዓት እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ከምግብና ውኃ ተከልክሎ ሥጋን ለነፍስ ማስገዛት ነው፡፡ ጾም ይህ ብቻ ሳይሆን ዓይን ከሚያየው፣ ጆሮም ከሚሰማው፣ አፍ ከሚናገረው፣ እጅ ከሚሠራው ክፉ እና መጥፎ ነገሮች በመከልከል ሕዋሳቶቻችንን ሁሉ ከኃጢአት ሥራ መቆጠብ ማለት ነው፡፡

ዐቢይ ጾም መባሉ በምሥጢሩም ሆነ በቀናት ብዛቱ ከአጽዋማት ሁሉ የበላይ ስለሆነና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ስለሆነ ነው፡፡ የጌታ መጾም ትሩፋት ለመሥራት፣ ኃጢአት ኖሮበት ለሥርየት ሳይሆን መብል ለኃጢአት መሠረት እንደሆነ ጾምም ለምግባር፣ ለትሩፋትና ለድኅነት መሠረት መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ሠራዔ ሕግ ነውና ጾምን ሕግ አድርጎ መስጠቱን ለመግለጽ ጾመ፡፡

 ጌታችን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ፤ በዲያብሎስ ተፈትኖ፤ የጾምን ኃይል ያሳየበት ነው፡፡ ፈታኙም ዲያብሎስ በስስት ቢመጣበት በትዕግሥት፤ በትዕቢት ቢፈትነው በትሕትና፤ በፍቅረ ነዋይ ቢፈትነው በጸሊዓ ነዋይ ድል የነሣበት ነው፡፡

ይህም ጾም ከዚህ እስከ እዚህ ነው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ በመሆኑ በኢየዐርግና በኢይወርድ ተወስኗል፡፡ ይኸውም መግቢያው ከየካቲት 1 እስከ መጋቢት 5 ባሉት 35 ቀናት ሲሆን የሚደመደምበት ደግሞ ከመጋቢት 26 እስከ ሚያዝያ 30 ይሆናል ማለት ነው፡፡

ጾሙ ለ55 ቀን የሚጾም ሲሆን ሦስት ክፍሎችና ስምንት ሳምንታት አሉት፡፡

            ስምንቱ ሳምንታት

  1. ዘወረደ
  2. ቅድስት
  3. ምኲራብ
  4. መጻጕዕ
  5. ደብረዘይት
  6. ገብርኄር
  7. ኒቆዲሞስ
  8. ሆሣዕና

            ሦስቱ ክፍሎች

1.  ዘወረደ (ጾመ ሕርቃል)፡- ይህም ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሑድ ድረስ ያለው 7 ቀን ነው፡፡

2.  የጌታ ጾም፡- ይህም ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሣዕና ዋዜማ ዓርብ ድረስ ያለው 40 ቀን ነው፡፡

3.  ሕማማት፡-  ይህም ጌታችን በአልአዛር ቤት ለማዕድ ከተቀመጠበት የሆሣዕና ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ሥዑር ቅዳሜ ያለው መከራን የተቀበለበት 8 ቀን ነው፡፡

ይህም 7 + 40 + 8 = 55 ማለት ነው፡፡

1. ዘወረደ (ሕርቃል)

ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ የወረደ ማለት ነው ይኸውም የአምላክን ሰው መሆን ያመለክታል፡፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም ካለው  ከጌታ ቃል በመነሳት ሊቁ በዚህ ዕለት ዋዜማ ‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ›› ድጓ ዘአስተምህሮ ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት ሁን ብሎ የማዳን ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም ብሎ ተናግሯል፡፡ ቤተክርስቲያናችን ይህ ድርሰት የጾሙ መጀመሪያ ዕለተ ሰንበት ዋዜማ መግቢያ ሁኖ በየዓመቱ ይቆማል፡፡ በመሆኑ የሳምንቱ ስያሜ ከዚህ የተወሰደ ነው፡፡

ጾመ ሕርቃል ያሰኘው ታሪክ በአጭሩ በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የሚባል የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት ያደርሳል፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ቤተ መዘክር ውስጥ ንግሥት ዕሌኒ አስቀምጣው በክብር የነበረውን የጌታ ኢየሱስን መስቀል ከሙዚየም ይወስዳል፡፡ ካህናቱን ይገድላል፣ ከተማይቱንም ያቃጥላል በዚህ ወቅት ስድሳ ሺህ የሚደርሱትን አቁስሎና ገድሎ ሦስት ሺህ የሚሆኑትን ማርኮ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህን ጊዜ ከጦርነቱና ከጥፋቱ ሰለባ ያመለጡት በየዋሻውና ጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉት ተሰባስበው ከአስራ አራት ዓመት በኋላ በ628 ዓ.ም ጩኸታቸውን የደረሰባቸውን በደል ለፈጣሪቸውና ለክርስቲያኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡ እሱም ነገሩን አስቦበት ሁሉም የአንድ ሳምንት ጾም እንዲያዙለት ይጠይቃል፡፡ ሁሉም ጾሙን በሚገባ ጹመውት አንድ ሳምንቷ እንዳበቃች በምርኮ የሄደውን የኢየሱስን መስቀልና የተማረኩትን ክርስቲያኖች ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሣበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡ የተማረኩትም በሙሉ ነጻ ወጡ፡፡ በዚህ መሠረት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ ስለዚህ ከጌታ ጾም ጋር አያይዘን እንጾመዋለን፡፡

 

ቅድስትን በሚቀጥለው ሳምንት ይጠብቁን . . .

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

   ምንጭ፡- ü ማሕቶተ ዘመን

     ü የመናፍቃን ማንነትና መልሶቻቸው

     ü ኪዳነ ጽድቅ

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine