በዓለ ጥምቀት ሥርዓቱና ትውፊታዊ አከባበሩ 2004

በሕሊና በለጠ

     የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ከምታከብራቸው በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል ከዋነኞቹ ተርታ የሚመደብና ሥርዓቱና አከባበሩም ለብዙ ዘመናት ብሔራዊ በመሆን የቆየ ነው፡፡ የጥምቀት በዓል አከባበሩ ጥንታዊ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን አይሁድ ከኢአማንያን ወገን የሆነ ሰው ወደ እምነታቸው ሲቀላቀል እንዲገረዝና በውኃ እንዲታጠብ ወይም እንዲጠመቅ ያደርጉ ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም አማናዊት ጥምቀት ከመመሥረቷ በፊት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ "እኔስ ለንስሓ በውኃ አጠምቃችኋለሁ ጫማውን እሸከም ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል" ማቴ 3÷11 ብሎ እንደተናገረው ሕዝቡን ለንስሓ በሚሆንና ለአማናዊት ጥምቀት የሚያዘጋጅ ጥምቀት ያጠምቅ ነበር፡፡

በባሕርይው ጻድቅ የሆነ ኃጢአት ያለበትን ሁሉ ሊያነጻ የሚቻለው እርሱ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ክብርና ምስጋና ይድረሰውና ከፈሳሾች ውኃን፤ ከባሕሮች ዮርዳኖስን፤ ከቅዱሳን ዮሐንስን፤ ከዘመናት 30ኛውን ዘመኑን እርሱ በሚያውቀው ምክንያት መርጦ አዳም በ30 ዘመኑ ያገኘውን የሥላሴ ልጅነት ያጣበትን በዮርዳኖስ የተቀበረውን የእዳ ደብዳቤ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ባርነታችንን በመፋቅ ጥምቀትን በታላቅ ምሥጢር መሠረተልን፡፡ ይኽም ጥምቀት የሃይማኖታችን ምሰሶ /አምድ/ የቤተክርስትያናችን የአምልኮ ምሥጢር ሆነ፡፡ ሊቃውንቱም የዕውቀት ባለቤት የሆነ ልዑል አምላካችን በገለፀላቸው መሠረት በመጻሕፍት አመሥጥረውትና ተርጉመውት በማስቀመጣቸው ሥርዓቱን ትውፊቱን፣ የሃይማኖት መሠረትነቱን፣ አከባበሩንና ትርጉሙን በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችንም በ 34 ዓ.ም በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ (ሐዋ.8፥26 ) አማካኝነት ክርስትና ተቀብላ በአብርሃና አጽብሐ ዘመን በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብሔራዊ ሃይማኖት ማድረጓ ይታወቃል፡፡ 

 

 

        አብርሃ ወአጽብሐ ነገሥተ ኢትዮጵያ

ይሁንና አሁን የሚታየው የበዓሉ አከባበር የተጀመረው በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ገብረመስቀል ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ንጉሡ በጊዜው ከተስፋፋው የቅዱስ ያሬድ ዜማ ጋር በተያያዘ ታቦታቱ ጥር11 ቀን ጠዋት ወጥተው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ባሕረ ጥምቀት በመሄድ የዛኑ ዕለት ወደ ማታ እንዲመለሱ ያዙና ይህም ተግባራዊ ይሆን ነበር፡፡ ይህም አከባበር እየተለመደና እየረተስፋፋ ብሔራዊ መልክ እየያዘ መጣ፡፡

በቅድስናውና በአገልግሎቱ ታላቅ መሆኑን ሕያው ሥራዎቹ የሚመሰክሩለት ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላም ታቦታቱ በተናጠል መሄዳቸውን አቁመው ወደ ባሕረ ጥምቀት ሲሄዱ በአቅራቢያ ያሉት በአንድ ላይ እንዲሆኑ አዘዘ፡፡ ይህም ለበዓሉ ድምቀት ታላቅ አስተዋጽኦን አበረከተ፡፡ በተጨማሪም ንጉሡ በጊዜው ለብህትውናና በስብከተ ወንጌል ቤተክርስትያንን በትጋት እያገለገሉ የነበሩትን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን በመማፀን በአክሱም፣ በላስታ፣ በሸንኮራ፣ በአንኮበር፣ መቀሌና በመርጡ ለማሪያም የሚገኙ ባሕረ ጥምቀቶችን እንዲባርኩ አድርጓቸዋል፡፡

ከዚህ በኃላም በርካታ ሥርዓትንና መጻሕፍትን በማዘጋጀቱ ቤተክርስትያን ልዩ ቦታ ያለው ንጉሥ ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ታቦታቱ ዕለቱን ወጥተው ዕለቱን መግባታቸውን ቀርቶ ጥር 10 ወደ ማታ ወደየ ባሕረ ጥምቀቱ ሄደው ጥር 11 እንዲመለሱ ሥርዓትን ሠርቶ ተግባራዊ አደረገው፡፡ ታቦታቱም ሀገሩን ሁሉ በኪደተ እግራቸው እንዲባርኩ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ አዘዘ፡፡ሕዝቡም በዋዜማው በባሕረ ጥምቀቱ ከትሞ በማደር ሊቃውንቱም ሌሊቱን ስብሐት በማቅረብ ታቦቱን ከበው ማደር ጀመሩ፡፡ አባቶቻችን እነዚህን ሥርዓቶች የሠሩት ካለምክንያት አይደለም፡፡ ታቦቱ የጌታችን ታቦቱን የሚሸከሙት የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ፣ ታቦቱ ከማደሪያው ወጥቶ ወደ ባሕረ ጥምቀት መሄዱ ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ለመሄድ ምሳሌ ስለሆነ ነው፡፡

በመሆኑም ከአንድ ሺህ ዘመናት በላይ አባቶቻችን ጠብቀውት ለኛ ያስረከቡንን ይህንን ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ሀብት እኛም እንደ አባቶቻችን ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዴታ አለብን፡፡ በተለይ አሁን አሁን በባሕረ ጥምቀት በረከትን ከማግኘት ይልቅ ሥጋዊና ስሜታዊ ድርጊቶች በወጣቱ ዘንድ እየተከናወኑ መሆናቸው የበዓሉ  ፍጹም ሃይማኖታዊነትን ከማደብዘዝ አንፃር ስጋት በመሆኑ ሁላችንም በጥንቃቄና በተመስጦ ሆነን ከማክበር ባሻገር የበዓሉ አከባበር ትውፊቱን እንዳይለቅ ልንጠነቀቅለት ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine