የፋሲካው በግ

 ለትምህርታችን መነሻ የሚሆነን ብርሃን ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ምእመናን በጻፈው መልዕክቱ ‹‹በፋሲካነ ተሰቅለ ክርስቶስ በፋሲካችን ክርስቶስ የተሠዋ አይደለምን?›› በማለት ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም እንደተሠዋ በማስገንዘብ ከኃጢአት እንዲጠበቁ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ 1ቆሮ. 57

 

አባቶች ሲናገሩ ‹‹ነገር ከሥሩ ውሃ ከጥሩ›› ይላሉ ስለዚህ በቀጥታ ወደ ትምህርታችን ከመግባታችን በፊት ፋሲካ የሚለው ቃል ትርጉም ምን እንደሆነ እንገልጻለን፡፡

Yefasikaw Beg  1. ፋሲካ ከግእዝ ቋንቋ አስተፈሰከ ደስ አሰኘ ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን ፋሲካ ማለት ደስታ ማለት ነው፡፡

       2. በእብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ፓሳሕ›› ሲሆን ትርጉሙም ማለፍ ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ፋሲካ ትርጉሙ ደስታ ወይም ማለፍ ሲሆን መነሻ ታሪኩን ስንመለከት ታሪኩ ከሕዝበ እስራኤል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እስራኤላውያን ለ430 ዓመታት በግብፅ አገር በባርነት ይኖሩ ነበር ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ መከራቸውን በመመልከት በባሪያው በሙሴ አማካኝነት ከግብፅ ባርነት እንደሚያወጣቸው ቃል ገባላቸው፡፡ ወይቤሎ እግዚአብሔር ለሙሴ ርእየ ርኢኩ ሥቃዮሙ ለሕዝብየ እለ ውስተ ግብፅ ወአወያቶሙ ሰማዕኩ አምነዳዕተ ገባር ወአእመርኩ ፃዕሮሙ ወወረድኩ ከመ አድኅኖሙ እም እደ ግብፅ ወእወስዶሙ ውስተ ምድር ሠናይት ወርኅብት እግዚአብሔርን ሙሴን በግብፅ ያለ የወገኖቼን መከራ አይቼ በሠራተኞች የተሾሙት ሹማምንቱ ካመጡባቸውም መከራ የተነሣ ጩኸታቸውን ሰምቼ መጨነቃቸውንም አይቻለሁ አለው ከግብፃውያን እጅ አድናቸው ዘንድ ወደ አማረች ወደ ተወደደች ሰፊ ወደምትሆን ወደ ከነዓንም እወስዳቸው ዘንድ ወረድኩ፡፡ ዘጸአት ትርጓሜ

 

እግዚአብሔር እንደ ተስፋ ቃሉ በሙሴ መሪነት ከባርነት ነጻ ሊያወጣቸው ሙሴን ላከው፡፡ ነገር ግን ከግብፅ ሲያወጣቸው አንድ ነገር እንዲያደርጉ አዟቸዋል፡፡ ይኸውም ሙሉ ታሪኩ በዘጸ. 021-፶1 ተመዝግቦ እንደምናገኘው እስራኤላውያን አንድ የበግ ጠቦት እንዲያርዱና ደሙን በየመቃናቸው እንዲቀቡ ነበር፡፡

‹‹ወንግር ለኵሎ ማኅበረ ደቂቅ እስራኤል ወበሎሙ በዐሥሩ ለዘወርኅ ትንሣኤ ሎቱ ብእሲ በቤቱ ወበዘመዱ ወለ ማኅበሩ በግዐ›› ሙሴንና አሮንን ለይቶ ሚያዝያ በገባ በዐሥረኛው ቀን አንዱም አንዱም በየቤቱ በየዘመዱ በጉን ይያዝ ብለህ ለእስራኤል ልጆች ወገኖች ሁሉ ንገር አለ፡፡ ዘጸ.023

እግዚአብሔር አምላክ ለእስራኤል ልጆች እንዲያርዱት ያዘዛቸው በግ ቀንዱ ያልከረከረ ጥፍሩ ያልዘረዘረ ጠጉሩ ያላረረ ዓመት የሆነው ጠቦት ነበር በጉንም  በሰርክ ሰዓት አርደው በሚበሉበት ቤት ደሙን በሁለቱ መቃኖች እንዲቀቡት ነበር የበጉን ሥጋም ሲበሉ የተጠበሰው እንጅ ብርንዶውንና ቅቅሉን እንዳይበሉ ታዘው ነበር ሲበሉትም ወገባቸውን በዝናር ታጥቀው ጫማቸውን በእግራቸው በትራችሁንም በእጃችሁ አድርገው እየቸኮሉ እንዲበሉት ነበር፡፡

እስራኤላውያንም እንደታዘዙት አደረጉ በዚያ ሌሊት መልአከ ሞት መጥቶ የግብፃውያንን በኵር ከሰው እስከ እንስሳ ሲፈጅ ወይም ሲገድል የእስራኤላውያንን ግን በበራቸው የተቀባውን ደም በማየት እያለፈ ከሰውም ከእንስሳም ምንም አልገደለም ነበር፡፡

‹‹ወሶበ ኮነ መንፈቀ ሌሊት ቀተለ እግዚአብሔረ በምድረ ግብፅ እም በኵረ ፈርዖን ዘይነብር ዲበ መንበረ መንግሥት እስከ በኵረ ፂውውት ቀዳሒት ወኵሎ በኵረ እንስሳ›› የሌሊት እኩሌታም በሆነ ጊዜ በዙፋን ከሚቀመጥ ከፈርዖን የበኵር ልጅ ጀምሮ ወሃ እስከምትቀዳ አገልጋይ ልጅ ድረስ በግብፅ አገር የበኵር ልጁን ሁሉ ከከብትም መጀመሪያ የተወለደውን ሁሉ ገደለ እንዲል ዘጸ. 029

እንግዲህ ይህን ሁሉ ለትምህርታችን መንደርደሪያ እንዲሆነን የተረክነው ምሳሌያዊ ወይም ጥላ ነበረ ወይም ስለ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ ክቡር ደም የተመሰለ ትንቢት ነበረ፡፡

-   የአንድ አመቱ በግ የወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ መሆኑ

-  12 ሆናችሁ ብሉት መባሉ በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ቁርባንን ሲመሠርት በ 12 ሐዋርያት መካከል መሆኑን

-  ነውር የሌለበት በግ መመረጡ የእግዚአብሔር በግ የተባለ ክርስቶስ በአንደበቱ ሐሰት በሰውነቱ ኃጢአት አንዳልተገኘበት ለማጠየቅ ነው፡፡

-  በ10 ጨረቃ ያዙት መባሉ ጌታችን ላይ አይሁድ በ10 ጨረቃ ቁርና ምክር መምከራቸው

-  በ14 ጨረቃ እረዱት እንደተባለ መጋቢት  በ14 ጨረቃ ጌታችን በመልዕልተ መስቀል ለመሰቀሉ

-  ደሙን ከመቃን ከመድረኩ ቀቡት ማለት የከናፍረ ካህናት ሲሆን ምሥጢሩ ግን ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉትን ሁሉ ሰይጣን አይቀርባቸውም ለማለት መሆኑ

-  ኮፌት /ቆብ/ አድርጉ መባሉ አክሊለ ሦክ መናገሩ ሲሆን

-  ወገባችሁን ታጥቃችሁ ጫማ አድርጋችሁ መባሉ ንጽሕናን ይዛችሁ ፍቅርን ተላብሳችሁ ቁረቡ ለማለት ሲሆን

-  የተጠበሰውን ብሉ መባሉ ዕሩቅ ብእሲ ሳትል በልቡናችሁ ኑፋቄ ሳታስገቡ እሳተ መለኮት የተዋሐደው ነው እያላችሁ ብሉት ለማለት ሲሆን

-  ሐሞት እየረበረባችሁ ብሉ መባሉ ስለ ፍቅረ ሰብእ ሐሞትና ከርቤ መጠጠቱን መናገሩ መሆኑ

-  ከአንዱ ወደ አንዱ አይሂዱ ማለቱ ቁርባን ከአንዱ ተሠርቶ ወደ አንዱ ቤተክርስቲያን አይሂድ ማለት ነው፡፡

-  የተረፈውን በእሳት አቃጥሉት መባሉ የተቻላችሁንና እግዚአብሔር የገለጠላችኑን ያህል ተመራምራችሁ የቀረውን ለእግዚአብሔር ስጡ ለማለት መሆኑ ባጠቃላይ በሐዲስ ኪዳን ስለሚመሠረተው ሥርዓተ ቁርባን መስበኩ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

ሐዲስ ኪዳን በብሉይ ተሠውራ እንደመቆየቷ ብዙ የጥንት ሥርዓቶች በራሳቸው ምሉዕ ከመሆን ይልቅ ለሐዲስ ኪዳን በምሳሌነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ ያየነውንም የፋሲካውን በግ ምሳሌነት ሊቃውንት ከዚህ በበለጠ አስፍተውና አምልተው በክርስቶስ አማናዊ መስዋዕትነት ምሳሌነቱ በስፋት ይተነትኑታል፡፡

እስራኤላውያን በግ አርደው ደሙን በመቃናቸው በመቀባት በግብፅ ከመጣው ሞተ በኵር እንደዳኑ ሁሉ መድኃኔዓለም ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ነፍሳትን ከዲያብሎስ ግዛት ከሲኦል እስራት ነጻ አውጥቶአል፡፡ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ የሐዲስ ኪዳን በግ ስለመሆኑ በብዙ ቦታ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ የመጀመሪያ አዋጅ ነጋሪ መንገድ ጠራጊ የተባለው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ስለዚህ አማናዊ በግ ሲናገር ‹‹ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢአተ ዓለም›› እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ዮሐ.19 በማለት እውነተኛው የፋሲካ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ይነግረናል፡፡

ስለ ክቡር ደሙም ሲናገር ወደሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያነጽሐነ እም ኵሉ ኃጣውኢነ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ ‹‹ወባሕቱ አምሳለ ኮነ ለዝ መዋዕለ ዘቦቱ ያበውኡ ቁርባነ ወመሥዋዕተ ዘኢይክል ፈጽሞ ለዘያቄርብ ዘእንበለ መባልዕት ወበዘይሰትዮ ወጥምቀታት ዘዚአሁ እንተ ይእቲ ሕገ ሥጋ እስከ አመይትራታዕ ተሠርዓ›› ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፡፡ እንደዚህም መባና መሥዋዕት ያቀርባሉ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ ስለ ምግብና ስለ መጠጥ ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በሕሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም፡፡ ዕብ. 99-0 በማለት የኦሪቱ ኃላፊ ወይም ምሳሌያዊ መሆኑን የሐዲስ ኪዳኑ ግን ዘላለማዊ መሆኑን ያስተምረናል፡፡

በአጭሩ ለመግለጽ እንደሞከርነው በኦሪት ዘመን ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ብዙ እንስሳት ለመሥዋዕትነት ቀርበዋል፡፡ ብዙ የእንስሳት ደም ፈሷል ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ምሳሌያዊ ወይም የወደፊቱን የመዳን ተስፋ የሚያመለክቱ ነበሩ እንጅ ከሥጋዊ ደኅንነት ያለፈ ምንም ፋይዳ አልነበራቸውም፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ ፈቃድ ከሰመየ ሰማያት ወርድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ እራሱን መሥዋዕት አድርጎ በቅዱስ ሥጋው እና በክቡር ደሙ አማካኝነት የዘለዓለም ደኅንነትን ሰጠን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ አዳነን፡፡

ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እኁሁ ለባስልዮስ እንዲህ በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹ወርደቱ እመስቀሉ ውስተ ሲኦል ወፈትሐ እለ ሀለው ህየ ጻድቃነ ወሙቁሐነ በኃጢአተ አዳም አቡሆሙ ወአንሰአነ በጽድቅ ትንሣኤሁ አምነሙታን ወአርኀወ ለነ ኆኅተ ንሰሐ››

ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣ በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን የንስሐንም በር ከፈተልን፡፡ ሃይማኖተ አበው ፴6፥፴

ስለዚህ እውነተኛው የፋሲካ በግ መሆኑን ተገንዝበን ስለእኛ ቤዛነት የሞተልንን የሕይወትን የትንሣኤ ባለቤት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ቅዱስ ሥጋውን በልተን ክቡር ደሙን ጠጥተን ጽድቁን መንግሥቱን እንድንወርስ የእርሱ ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን አሜን፡፡

                                         

 

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine