ዐቢይ ጾም

እንኳን ታላቅ በረከትና ጸጋ ለምናገኝበት ፤ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ለጾመው ለዐቢይ ጾም በሰላምና በጤና አደረሰን፤ አደረሳችሁ፡፡ በበዓላት እንኳን አደረሳችሁ እንደምንባባለው ሁሉ በጾም መግቢያ ላይም እንኳን ለወርኃ ጾም አደረሳችሁ መባባል ይገባል፡፡ የጾም ወቅት የሚናፍቅ መሆን አለበት ምክንያቱም ጾም ፈቃደ ነፍስ ፈቃደ ሥጋን የምትገዛበት ከልዑል እግዚአብሔር የምንገናኝበት በረከት የምንቀበልበት ልዩ ወቅት ስለሆነ ነው፡፡ከአጽዋማት ሁሉ ታላቅ መሆኑን ስሙም ጭምር የሚጠቁመው ዐቢይ ጾም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ከተጠመቀ በኋላ በገዳም ገብቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት የጾመው ጾም ሲሆን በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራል፡፡ ማቴ. ፬ ከቁጥር ፩ ጀምሮ፡፡

 

ዐቢይ ጾም፡- 

ዐቢይ ማለት ታላቅ ማለት እንደሆነ ሁሉ ይህ ጾም ራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም በመሆኑና ከጾሞች ሁሉ ትልቅ በረከትን የምናገኝበት በመሆኑ ታላቅ የሚለው ስያሜን ይዟል፡፡ በቀኑም ብዛት ከሌሎች አጽዋማት ይበልጣል፡፡

የሁዳዴ ጾም፡-

የጥንት ዘመን ገበሬዎች ለባለርስቱ የሚያርሱት መሬት (ሁዳድ) ይባል እንደ ነበር ይህም ጾም ሠራዔ ሕግ ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ምዕመናንም ይህንን እያሰቡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ (ከትንሽ እስከ ትልቅ) የሚጾሙት ስለሆነ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል፡፡

የካሣ ጾም፡-

የቀድሞዎቹ አትብሉ የተባሉትን በመብላታቸው ከገነት ለመባረር ለውርደት ለሞት ለሲዖል ባርነት ተዳርገዋል፡፡ ዳግማዊ አዳም የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመብል ምክንያት ድቀት አግኝቶት ረሀበ ሥጋ ረሀበ ነፍስ ደርሶበት የነበረው ቀዳማዊ አዳምንና ልጆቹን በፈቃዱ በጾመው ጾም፤ ረሀበ ሥጋችንን እና ረሀበ ነፍሳችንን ሊያርቅልን ስለጾመው የካሣ ጾም ይባላል፡፡

 

የድል ጾም፡-

አዳምና ሔዋን ከዚህ ዓለም ርቃ በምትገኝ በገነት ሳሉ በምክረ ከይሲ ተታለሉና ድል ሆኑ፡፡ ተስፋ አበውን ሊፈጽም የመጣ ክርሰቶስም ዲያቢሎስን ድል ያደርግልን ዘንድ ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ከዚህ ዓለም ርቆ ወደ ገዳም በመሄድና ከሰው ተለይቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት በመጾም ዲያቢሎስን ፈቃደ ሥጋችንን ድል የምናደርግበት ኃይል አጎናጽፎን ሦስቱን የኃጢአት ራስ የተባሉት ድል የተነሱበት ዲያቢሎስ ያፈረበት ስለሆነ የድል ጾም ይባላል፡፡

የመሸጋገሪያ ጾም፡-

ነቢዩ ሙሴ 40 ቀንና 40 ሌሊት በሲና ተራራ ጾሞ እስራኤል ዘሥጋን ከሕገ ልቦና ወደ ሕገ ኦሪት ያሸጋገረ ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስራኤል ዘነፍስ የተባልነውን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል 40 ቀንና 40 ሌሊት በመጾም ያሸጋገረን በመሆኑ የመሸጋገሪያ ጾም ተብሎ ይጠራል፡፡ይህ ጾም አብዛኛውን የየካቲትና የመጋቢት ወራትን የሚይዝ ሲሆን የሚያዚያንም ወር የሚጨምርበት ጊዜ አለ፡፡ እስከ ቀዳም ስዑር ለ55 ቀናት ይጾማል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው 40 ቀናት ሲሆን እኛ ለ55 ቀን የምንጾምበት ምክንያት በ55 ቀን ውስጥ 8 ሳምንታት (8 ቅዳሜና 7 እሑድ) ይገኛሉ፡፡ አንድ ላይ ዐሥራ አምስት ቀን ይሆናሉ፡፡ እነዚህን ሰንበታት ከጥሉላት (ሰውነትን ከሚጠግኑ) እንጂ ከእህልና ከውሃ ስለማይጾም የእሑድና የቅዳሜን ምትክ ዐሥራ አምስት ቀን ተጨምረው ይጾማሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀንና ሌሊት የጾመበት ምክንያት-   

ነቢያት 40 ቀን ጾመዋልና 40 ጾመው ትንቢት የተናገሩለት እርሱ መሆኑን ለማጠየቅ-    ቀድሞ ነቢያት 40 ቀን ጾመዋል ጌታችንም ከ40 ቀን ቢያተርፍ አተረፈ ቢያጎድል አጎደለ ብለው ሕገ ወንጌልንም እንዲሁም ጌታን ላለመቀበል ምክንያት እንዳያደርጉ-    ነቢዩ ሙሴ 40 መዓልትና ሌሊት ጾሞ ሕገ ኦሪትን ሠርቷል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም 40 መዓልትና ሌሊት ጾሞ ሕገ ወንጌልን የሚሠራ ነውና፡፡-    አዳም በ40 ቀን ያገኘውን ልጅነት አስወስዶ ነበርና ለእሱ እንደ ካሳ ለማጠየቅ ኢንዲሁም በ40 ቀን ተስዕሎተ መልክ ለተፈጸመለት ሰው ሁሉ ለካሳ እንዲመጣ ለማጠየቅ

በ55 ቀን ውስጥ 8 ሳምንታት አሉ እያንዳንዱ ስያሜ አላቸው፡፡

  • አንደኛው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡
  • ሁለተኛው ሳምንት ቅድስት ይባላል፡፡
  •  ሦስተኛው ሳምንት ምኵራብ ይባላል፡፡
  •  አራተኛው ሳምንት መፃጕዕ ይባላል፡፡
  •  አምስተኛው ሳምንት ደብረዘይት ይባላል፡፡
  •  ስድስተኛው ሳምንት ገብርኄር ይባላል፡፡
  •  ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡
  •  ስምንተኛው ሳምንት ሆሣዕና ይባላል፡፡
ዘወረደ ወይም ሕርቃል

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡ ‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ›› የሚልና ይህንን የመሳሰለ ጌታ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡ ሌላም ስም አለው ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ሕርቃል ማን ነው? ለምንስ በስሙ ተሰየመ?በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡ እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡ በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡                                   

ወስብሐት ለእግዚአብሔር                                               

ምንጭ፡- ጾምና ምጽዋት 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine