የመንጋው በረከት


/ሁለት ተራኪዎች በጥግ በኩል ከውጭ ጃኖ ለብሰው መጻፍያ የዶሮ ላባና ወረቀት (ብራን) ይዘው ይታያሉ፡፡/


ሩፊኖስ ፡- ውድ ወንድሜ ተርቢኖስ ሆይ ታሪክ ልጽፍ ጥንታዊቷ ኢያሪኮ ግንብ ፍርስራሽ ስር ታሪክ ፍለጋ ስቆፍር ብዙ ታሪኮችን አገኘሁ ነገር ግን ብዙ ብደክምና ሰውነቴ ቢዝልም ቁፋሮዬን የሙጥኝ አልኩት፡፡ አንድ ሰው ሕፃንም ይሁን ትልቅ መልካም ፍሬ የሚያፈራው ብዙ መከራ አይቶ ደክሞና ከአጋንንት ጋር ተጣልቶ ነውና እኔም ታሪክ ጸሐፊ ነኝ ለማለት ምድር በውስጧ የያዘችው በሙሉ ማስተፋት ይገባኛል ለማስተፋትም እጅጉኑ መቆፈር፡፡ በቁፋሮዬም በዶማዬ ሹል ከመፈረካከስ የተረፈ ድንጋይ ላይ የተጻፈ ጽሑፍ አገኘሁ፡፡

ተርቢኖስ ፡- ምን ይሆን ወንድሜ ሩፋኖስ መቼም ከታላቅ የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊነትህ አንፃር ድንቅ ነገር እንዳገኘህ ይረዳኛል፡፡ የእኔና ያንተ ታሪክ ጸሐፊነት እንደ ሌሎቹ በስጋዊ ሀሳብ አድንቆ የሚያልፋቸው አይነት አይደሉም፡፡ ሰው ራሱን ማንነቱን ከምናስቀርለት ታሪክ መስታወት ውስጥ ራሱን ፈልጎ ሕይወቱን የሚያስተካክልበት እንጂ …

ሩፊኖስ ፡- /አቋርጦት/ ልክ ብለሀል ወንድሜ ተርቢኖስ እስራኤላዊያን ከ430 ዘመን ባርነት በእግዚአብሔር ፈቃድ በሙሴ መሪነት ነፃ ወጥተው ወደ ምድር ርስታቸው ከነአን ለመግባት 40 ቀን ብቻ ነበር የሚፈጅባችው እነርሱ ግን በአመፀኝነትና ለአምላክ አልታዘዝም በማለታቸው 40 ቀን 40 ዓመት ተለወጠባቸው ከኢያሱና ከካሌብ በስተቀር ከግብጽ የወጡት እስራኤላዊያን በሙሉ በምድረ በዳ ቀሩ ወደ ከነአንም የገቡት ልጆቻቸው ብቻ ነበሩ፡፡

ተርቢኖስ ፡- አዎ በአምላክ ላይ ማመፅ ማንጎራጎር በስራው ላይ ገብቶ ትክክል አይደለም ማለት ትርፉ እመቀመቅ መውረድ ብቻ ነው ወንድሜ ሩፋኖስ ሆይ ስለግኝትህ ቀጥልልኝ

ሩፊኖስ ፡- ግኝቴንም ከድካሜ በማረፍ ላቤን ከጠረኩ በኃላ ጽሑፍን ማንበብ ቀጠልኩ ልቤ እንዴት መሰለህ የተነካው በብራና ከትቤ  ለአንተ ልኬልሀለውና አንብበው

ተርቢኖስ ፡- ወንድሜ ሆይ በናዝራዊ በአምላካችን በኢየሱስ ስም የሐዋርያት በረከት ይደርብህ እኛም ክርስቲያኖች ከሩፊኖስ ታሪክ ጋር ሆነን ታሪኩን በማድመጥ ሕይወታችንን እንቃኛት፡፡

 

           (መጋረጃ ይከፈታል)

   /ረአብ በጭነረቀት ተውጣ መድረክ መሀል ተቀምጣ ተታያለች/

 

አማት ፡- /በአሮጊት የአለባበስ ስልት ተሽሞንሙነው የሚያስጠላ ሳቅ እየሳቁ/ "አላረጅም አሉ" ብለው ቅፅል ስም ያወጡልኝ ቆይ ምድር ብጣሻም ሁሉ ምንም እንኳን ፀጉሬ ሙሉ በሙሉ ነጭ ቢሆንም እኔ ገና ልጅ ነኝ (ወደ ረአብ እያዩ) አሉ እንጂ እዚህ ማንነታቸውን የማያውቁ አንቺ እንዴት ለእኔ "አላረጅም አሉ" ተብሎ ስም ያወጣልኛል  እኔ ከአንቺ በምን አንሼ ነው አሮጊት የምሰኘው ለዚያውም በትንሹ አንቺ በ15 ዓመት ባትበልጭኝ ነው ልጄ አንቺን ባያገባ ኖሮ አይሞትም ነበር

ረአብ ፡- ይተው እማማ ገፊ ብለው አይስደቡኝ ለነገሩ የእርሶ ስድብ የተለመደ ስለሆነ ትዝም አይለኝ እኔን ብርክ ያስያዘኝ የዚያ መንጋ ጉዳይ ብቻ ነው

አማት ፡-  /ይስቁባታል/ አንቺ ለዚህ የተልባ መንጋ ምን ልሁን ብለሽ ነው የምትጨነቂው የአገሬ ግዙፍና ጠንካራ ወታደሮች ንቀሽ ነው /አንድ ሰካራም ይገባል/ ደግሞ ትሰሚያለሽ እማማ ያልሻትን ቃል እንዳትዘነጊ /እያሾፉ/ ሞትሽ የቀረበ አሮጊት

ሰካራም ፡-  ኧ.....ሞትሽ የቀረበ አሮጊት....ማ ውቢቱ እንደ አጥቢያ የምታበራው ረአብ ጉድ እኮ ነው ባካችሁ....ይሰማሉ /እያሾፉ/ ሞቶት እጅግ በጣም የቀረበች አሮጊት

አማት ፡-  /እየገላመጡት/ ምንድን ነው ስለ አንቡላህ ንግግር ልታደርግ ነው

ሰካራም ፡-  አዎ ስለ አንቡላዬ ነው... በእርሶና በረአብ መካከል ያለውን የእድሜ ልዩነት በጣም የተራራወቀ ነው ረአብ ማለት የጠጅ ብርዝ እርሶ ደግሞ ለእንደኛ አይነት ሰካራም ለጉበታችን መፈንዳት ተጠያዊ የምናደርገው አንቡላ ኖት

አማት ፡- ማ... አንተ እኔ ነኝ አንቡላ ወይስ ተሳስተህ ይችን ጋለሞት ይሆን

ሰካራም ፡- አንቺ ልቧ የማይሞት አሮጊት ትሰሚያለሽ የአንቺ አሮጊትነት ከመጃጀትሽ አልፎ እድሜሽ እያሟጠጥሽ ነው

አማት ፡- አንቺ ገፊ ብለሽ ብለሽ አሮጊትነትሽን ለኔ ታወርሺኝ /ተመናቅረው ይወጣሉ/

ሰካራም ፡- ሄዱ እንዴ እማማ "አላረጅም አሉ" ወደ መቃብር ይውሰዶት ረአብ እኝህ አሮጊት ለምን እራሳቸውን እንደማያስረጁ ታውቂያለሽ /አንድ መኮንን ሳይቀርባቸው ይቆማል/ በእያሪኮ ያለው የዝሙት ፍልስፍና አልጠፋ ብሎባቸው እኮ ነው /ዞር ሲል ሰውየው አፍጥጥጦበታል/ ወይ የኢያሪኮ ጣኦት ድረስ

ረአብ ፡- ምን አልክ /ቀና ብላ/

ሰካራም ፡- ምንም አልሆንኩም በይ እንግዲህ ሰላም ሁኚ

ረአብ ፡- ምኑን ሰላም ሆንኩት

ሰካራም ፡- እኔ ስለሱ አያገባኝም ብቻ እንደ ሕፃን ልጅ የሚያባብሉሽ ስጋቸው በመብልና በወይን ስትፈላ ረአብ ዘማ የሚያሰኙሽ ስለ መጡ /ዞር ብላ ታየውና ታቀረቅራለች/ መድረኩን ለእርሳቸው እለቃለሁ /ሰላምታ ሰጥቷት ይወጣል/

መኮንኑ ፡- /ከቆመበት እየተንቀሳቀሰ/ ውዴ ኮከብ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን /ይንበረከክላታል/ የእኔ ቆንጆ የእኔ ውብ ማንም ከአንቺ የምትስተካከል በፍፁም የለኝም

ረአብ ፡- /አዘቅዝቃ እያየችው/ ወንድ መሆን ከንቱ ገና ለገና ሴት ናት ብለህ ልትሸነግለኝ አስበህ ከሆነ አትልፋ በውዳሴ ከንቱ አትካበኝ

መኮንኑ ፡- /ከተንበረከከበት እየተነሳ/ አንቺ ውብ ነሽ ለውበትሽ አድናቆቴን መግለጼ ነው

ረአብ ፡- ድንቅ ፍልስፍና ዳሩ ግን እኔን ያስጨነቀኝ ይህ አይደለም

መኮንኑ ፡- ምንድን ነው የእኔ ኮከብ (ዝም ትለዋለች) ከሩቅ ምስራቅ ጌጣጉጦች እንዲመጡልሽ ፈልገሽ ይሆን

ረአብ ፡- አይደለም

መኮንኑ ፡- በፋርስ ጥበብ የተካኑ የሀር ልብሶች ይሆን

ረአብ ፡- በፍፁም የምትደረድራቸው የለበስኳቸው ናቸው እኔን ያስጨነቀኝ ሌላ ነው

መኮንኑ ፡- ስለምን አትነግሪኝም

ረአብ ፡- ኢያሪኮን ሊወር የተዘጋጀው መንጋ ነው

መኮንኑ ፡-  አ.ሃ.ሃ.ሃ. /ይስቃል ረአብ በትዝብት ታየዋለች ጡንቻውን እያሳያት/ የእኛ የኢያሪኮያውያን አንዳችን ሳያማሽሽ እንዴት ጠላት ይከጅልብኝ የዱቄት ብናኝ ነው የምናደርጋቸው

ረአብ ፡- በጡንቻቸው የሚያስቡና የሚመኩ የድንጋይ ጡቦች ናቸው የዚያ መንጋ አምላክ ከዮርዳኖስ ማዶ ድንቅ ስራ እንደሰራላቸው ጭንቀቴን ልታስታውስልኝ ካልቻልክ ብቻዬን መሆን ስለምፈልግ ብትወጣልኝ /ቁጭ እያለች/

መኮንኑ ፡- እሺ የእኔ እመቤት እወጣልሻለሁ ድል ለኢያሪኮ /እያለ ይወጣል/

ረአብ ፡- /ታስብና/ አሁን ይህ መንጋ የተንቀሳቀሰ እንደሆነ ቤቴ የግንብ ጫፍ ላይ ስለሆነ ቅድሚያ የሚያጠፉኝ እኔን ነው አምላካቸው የዋዛ አይደለም ባህሩን ለሁለት ከፍሎ ህዝቡን በደረቅ አሻግሮአል ኢያሪኮ ደግሞ መንጋውን ንቃለች አይ አንቺ የምወደወሽ ኢያሪኮ  (ሁለት ወንድና የሁሉ ታናሽ የሆነች ሴት ልጅ እየተራራጡ ይገባሉ)     

 

1ኛውልጅ ፡- እማማ እማማ ምን ሆንሽ.... አመመሽ

2ኛውልጅ ፡- እኝህ እማማ "አላረጅም አሉ" ተቆጡሽ

ልጅት ፡- አይደለም ሁላችሁም አላወቃችሁትም

2ኛልጅ ፡- እሺምንድን ነው

ልጅት ፡- /ፊቷን እየዳሰሰች/ ርቧት ነዋ!

ረአብ ፡- ተውኝ ልጆቼ እኔን ያስጨነቀኝ ሞት ነው

1ኛውልጅ ፡- የምን ሞት በኃይል አሞሽ ነው

ረአብ ፡- አሞኝ አይደለም ከኢያሪኮ ማዶ ያለው መንጋ ሊጨርሰን ነው

ልጅት ፡- እማዬ እኔም እሞታለሁ

ረአብ ፡- /እያቀፈቻት/ አይዞሽ ለራሴ ተጨንቄ አስጨነኳችሁ

አማት ፡- /እየገቡ/ "አላረጅም አሉ" አሉ እነዚህ ቅራቅንቦ መሳቂያ መሳለቂያ ሁሉ እናንተ ምንድን ነው የሚያነፋርቃችሁ

2ኛልጅ ፡- እ....ዛ ያለው መንጋ ሊበላን ነው

አማት ፡- ማንን!

1ኛልጅ ፡- እኛን ሁላችንን

አማት ፡- እኔን ከፈሪዎች አትቀላቅሉኝ /ረአብን እያሽሟጠጡ/ መንጋው እኔን አይበላኝ

ልጅት ፡- አያቴ እርስዎን መንጋው የማይበላዎት ስለማይጣፍጡት ነው; /ሁሉም ይስቃሉ/

አማት ፡- እ … /ያንባርቃሉ ልጆቹም ደንግጠው ዝም ይላሉ/ ዳሩ ግን አንቺ ምን ታደርጊ እናትሽን ነበር አርባ መግረፍ ሰማሽ ብለሽ ብለሽ አትጣፍጪም እያልሽ ታስወሪ ጀመር ቅናተኛ ልጆቼን በፍርሀት አታስጨንቂብኝ ሺ መንጋ ቢንጋጋ ቁብም አንለው

ረአብ ፡- እፍ........አይነዝንዙኝ /እየተነሳች/ ልጆቼ ኑ ወደ ቤት

እንግባ ሁሉም ሲነሱ ሁለት የእስራኤላዊያን ሰላዮች እየሮጡ ይገባሉ/

አማት ፡- ኡ......ኡ......የእስራኤላዊያን ሰላዮች ...... ኡ ...... ኡ ውጡ ከዚህ ይህ የተከበረ የጦር መኮንን ቤት ነው ውጡ .... ኡ ...... ኡ..

ረአብ ፡- ግቡግቡ አትፍሩ ግቡ

አማት ፡- ግቡ!......ኡ.......ኡ /እየጮሁ ይወጣሉ/

ረአብ ፡- ኑ .....ኑ.....ከእልፍኝ ልደብቃችሁ /ይዛቸው ትገባለች ረአብ ትንሽ ቆይታ ትመጣለች/

አማት ፡-  ኑ እዚህ ገብተዋል.....ረአብ ደብቃቸዋለች

    

 (ሦስት ወታደሮች በጣም ተቆጥተው ይገባሉ)

 

ዋናው ፡- የተከበርሽ የኢያሪኮ ኮከብ የገቡት የእስራኤል ሰላዮች ናቸውና በፍጥነት ከደበቅሽበት ቦታ አውጪያቸው! አለበለዚያ

ረአብ ፡- /እጇን ከትከሻው ላይ ስታሳርፍ ቁጣው ሁሉ ሙሽሽ ይላል/ የኢያሪኮ ጠላት እንዴት ደብቀሻል ብለህ ትጠረጥረኛለህ

አማት ፡- ኤይ...... ሙትቻ /ከፈዘዘበት ወዝውዘው እየነቀነቁት/ ከእልፍኝ ደብቃቸዋለች /ዋናው ሮጦ ሲገባ ሁሉም ይከተሉታል/ ተንኮልሽን አፈረሱብሽ /ረአብ ተጨንቃ እም ትላለች/

ዋናው ፡- (ሌሎቹን አስከትሎ በቁጣ ይወጣል ) ሰላዮቹ ወዴት ነው የሄዱት /ጎራዴውን መዞ አንገቷ ላይ በማድረግ/

ረአብ ፡-  ወደ ሸለቆው ይመስለኛል

ዋነው ፡- /በትዕዛዝ/ በአስቸካይ ወደ ሸለቆው /ሁሉም እየሮጡ ይወጣሉ/

አማት ፡- እንከፎች... ዝም ብሎ መሮጥ ብቻ... አይ  ጎልጉዬ አወጣቸው የለ /ወደ እልፍኝ እየሮጡ ይገባሉ/

ረአብ ፡-  ወይ እዳዬ... እኝህን አሮጊት ምን ባደርጋቸው ይሻለኛል አሁን ቢያገኟቸው ሊያሲዛቸውም አይደል /ወደ እልፍኝ ልትገባ ስትል/

አማት ፡- /ሮጠው እየመጡ/ ዛሬ አያመልጡኝም ፍተሸዬ የማዕድ ቤት በርሜል ውስጥም ተደብቀው ቢሆን እንኳን ከመፈተሸ ወደ ኃላ አልልም /ወደ ሌላ አቅጣጫ ይወጣሉ/

ረአብጎሽ እኚህ አሮጊት ከሄዱልኝ እንኳን ሄጄ ከተደበቁበት ማውጣት እችላለሁ /ትገባለች/

አማት፡- /ረአብ መግባቷን አይተው ተንሾካሽከው ይመጣሉ ረአብ ወደገባችበት ይጠጋሉ/       አ …ዎ! ዛሬ እንደው አንላቀቃትም እቺ ከሀዲ አንገትሽን በአደባባይ ሳላሰይፍ! እ...ሳልፈትሽ የቀረኝ መፀዳጃ ቤት ብቻ ስለሆነ አሁን ሄጄ ላረጋግጥ /ብለው ይወጣሉ/

ረአብ ፡- / ከሰላዬች ጋር እየወጣች/ ኑ አይዟችሁ አትፍሩ አሳዳጃችሁ ሁሉ ሄደዋል /ሰላዬቹ ከግራና ቀኝ ያማትራሉ የደስታ ምልክት ከፊታቸው ይነበባል/ ግን በምን ምክንያት ወደ እዚህ ልትመጡ ቻላችሁ

1ኛሰላይ ፡- የእኛ እንኳን አመጣጥ ለስለላ ነው

ረአብ- ምን ልትሰልሉ እያሪኮን

2ኛሰላይ ፡- አዎን ኢያሪኮአችሁን.... ከ470 አመት በፊት አምላካችን አብርሀምን የሰጠው እኛም ከግባፅ ባርነት ነፃ ወጥተን እንወርወሳት ዘንድ ከአምላካችን የተነገረን ከነአን ምድራችን ናት በእግዚአብሔር ኃይል ኢያሪኮን አጥፍተን ከነአን እናሰኛታለን ኤናቃውያንን ፈጅተን እስራኤላዊያንን እንተክልበታለን /ረአብ ታለቅሳለች/ ምን ሆነሽ ነው የምታለቅሽው; ስለምንስ ታዝኛለሽ;

አብ ፡- የሚያወራ የሚናገረው ሁሉ እውነት መሆኑን ሳረጋግጥ የምወዳት ኢያረኮ ስትወድም አሳዝናኝ ነው አምላካችሁ ኃያል ከዮርዳኖስ ማዶ ባደረገው ተአምር ምንም ምን የማይሳነው እንደሆነ ስለማውቅ ድሉንም እንደሚሰጣችሁ ስለተረዳሁ /እግራቸው ስር ወድቃ/ እባካችሁ ይህችን የጨረቃ ከተማ አምላካችሁ ሲያጠፋት ራሩልኝ /ሁለቱም በመገረም ይተያያሉ/

1ኛሰላይ ፡- አይዞሽ /እያነሳት/ ከአረማውያን ወገን ሳለሽ ተአምር ያላደረገልሽ እግዚአብሔርን ማመንሽ በጣም ድንቅ ነገር ነው የሆነብን

2ኛሰላይ ፡- እኛ ይህችን ከተማ ስናጠፋ እግዚአብሔርን አምነሻልና...... ለእኛም ትልቅ ውለታ አድርገሻልና አንቺንና ቤተሰቦችሽን እንምራለን… በዚያች እለት ግን እንዳትወጪ ቀይ ፈትል ከቤትሽ አላማ አድርገሽ አውለብልቢ ይህ ቀይ ፈትል ከሌለ ግን መሀላችን ይፈርሳል

በአንቺና በቤተሰቦችሽ ላይ የኢያሪኮን ዕጣ ይወድቅባችኋል

ረአብ ፡- እሺ ... /እግሩ ስር ወድቃ/ ኑ ጊዜው እየመሸ ስለሆነ በምግብ ልባችሁን ደግፋችሁ ትሄዳላችሁ እኛም አሮጊት ሳይመጡ ቶሎ ከወገኖቻችሁ ትቀላቀላላችሁ /እየመራቻቸው ይገባሉ/

አማት ፡-  እየገቡ "አላረጅም አሉ" አሉኝ ቆይ አሳያቸዋለሁ ማንነቴን.... እነዚያን ሰላዮች አስይዜ በሰይፍ አንገታቸውን ሳስመትር ይታየኛል .. ያቺም ገፊ በአደባባይ ሳሰቅላት /እነ ረአብ ወደ ገቡበት አቅጣጫ እያዩ/ ምነው ዛሬ ያለወተሮዋ ከእልፍኝ ገብታ ተቀረቀረች… ቦቅቧቃ ይሄኔ እየነፈረቀች ነው /በሽኩ ሽኩታ ወደ እልፍኝ ሲጠጉ መጋረጃ ይዘጋል/

                 

 ገቢር ሁለት

 

ተርቢኖስ ፡- ወንድሜ ሩፋኖስ የሚያሳዝን ታሪክ ነው ረአብ ሀጢያት ባስመጣት ኢያሪኮን ተስፋ ባላገኘችበት ከተማ ውስጥ ሆና እንዳትሞት መጨነቋ ኢያሪኮዊያንን ክዳ ከእስራኤላውያን ጋር ማበሯ የሚያስገርም ነው ረአብ ትልቅ ትምህርት ሰጥታለች ኃጥያት ባጠቆራት አለም ውስጥ እኛነታችን ድንገት ሞት ሲመጣ መግቢያ ቀዳዳውን ከሚሰውርብን አስቀድመን አለማዊነታችንን መካድ ንስሐ ሳንገባ ሞት እንዳይቀድመን  መጨነቅ ዘወትር በጸሎት መትጋት ይገባናል እንዲሁም አለማዊነታችንን ክደን በተስፋ ሰማያዊያን ለመሆን መታገል አለብን ግን ወንድሜ ሩፋኖስ እኛ የስጋ ፍላጎት የሰይጣን ተምሳሌት አሮጊት ያሲይዟቸው ይሆን

ሩፋኖስ ፡- ወንድሜ ተርቢኖስ አትስጋ ረአብ ተስፋ ያላት ጠንካራ ሴት ናት ሁለቱን ሰላዮች በምሽት በግንብ አዘልላ ወደ ተራራው ሸሸተው እንዲቆዩ መክራ ሰዳቸዋለች ኢያሱና ካሌብ እስራኤልን የመምራቱ ነገር ሀላፊነት ከሙሴ ከተረከቡ ከኢያሱ ዘንድ ደርሰዋል ያ ዝምተኛ መንጋም ወደ ኢያሪኮ ለመንጎድ ታቦተ ሕጉን ከፊት አስቀድሞ መነቃነቅ ጀምሯል

 

    (ሁለቱም ይገባሉ ከህዝቡ መካከል ሦስት ሰዎች ወጥተው)

 

1ኛው ፡- ይገርማል እኮ ምን አይነት ዝምተኛ መንጋ ነው እጃቸውን ሊሰጡ ፈልገው ይሆን

2ኛው ፡- /ይስቅና/ እኔ ዘንድ አንድ ነገር ተከስቶልኛል ህዝቡን የሚመሩት ሰዎች ትኩስ ክብዶች ወይም ከእናታቸው ማህፀን ሲወጡ ቂል ሆነው የተፈጠሩ ሳይሆኑ አይቀርም በዚያ ላይ የሽኩሽኩታ ያህል ድምፅ አይሰማባቸውም በአርምሞ ነው የኢያሪኮን ቅጥር የሚዞሩት ይህም ዙረታቸው ለእኛ ከአጥሩ ላይ ወጥቶ ጥሩ የጊዜ ማሳለፊያ መዝኛዎች ሆነዋል

3ኛው ፡- ሞኝ አትሁን....""አንገት ደፊ አገር አጥፊ"" ሲባል አልሰማህም

2ኛው ፡- እንዴት

3ኛው ፡- ከኃላቸው ድብቅ ጦር አላቸው ተብሎ ይጠረጠራል

2ኛው ፡- አይመስለኝም ይልቅ ከዮርዳኖስ ማዶ ድል እያደረገ ያመጣቸውታላቅና ኃያል አምላክ አላቸው ከመንጋው ፊት ለፊት የሚጛዘውን አይተሀል አምላካቸው በእርሱ ላይ አድሮ የአሞራውያንን ንጉስ ሴዎንን የባሳንን ንጉስ አግን ድል ያደረገላቸው

1ኛው እና ታዲያ የፈለገ ድንቅ ተአምራትን የሚያደርግ አምላክ ቢሆን የጨረቃ ከተማችንን አይደፍራትም

3ኛው ፡- እንዲያ ነው እንጂ እንደ ኢያሪኮውያን ኮከብ እንደ ረአብ በጭንቀት ማዕበል ከምንዋጥ ዛሬ የዳንስ ምሽት ስላለ በርቸስቸስ እንበል

1ኛው ፡- ይህንማ እንተው ብንልስ መች ይተውና ተፈጥሮአችን እኮ ነው /ሁሉም ይገባሉ/

 

(መጋረጃ ሲከፈት የረአብ እልፍኝ ይታያል ረአብ ከልጆቻ ጋር ሆና ቀዩን ፈትል ሰቅላ ትታያለች)

 

አማት ፡- /እየገቡ/ ስድስት ቀን እዚህ መኮልኮላችሁ ምን ይሉታል አሁን  እነዚህ አቅመ ቢሶች ድል ያደርጉናል ብላችሁ ነው

ረአብ ፡- ይልቅ ከእኛ ጋር አርፈው ቢቀመጡ ጥሻላል

አማት ፡- ማ እኔ! ምን እንዳልሆን /ወደ ፈትሉ እየተመለከቱ/ ፈተሌን እዚህ ቤት አንጠልጥለሽ /ወንበር ላይ ወጥተው ያወርዱታል/

ረአብ ፡- ምን ያደርግሎታል

አማት ፡- ምን አገባሽ

ረአብ ፡- እሺ በብር ሽጡልኝ

አማት ፡- አልፈልግም "አላረጅም አሉ" አሉኝ ቆይ ብቻ(ይወጣሉ)

ረአብ ፡- ምን ልሁን ተስፋዬ ጨለመ ወዴትስ ልሂድ ከየትስ አገኛለሁ ልብሶቼ ሁሉ የሀር ፈትል ብቻ ናቸው ምነው ጣሬ በዛ ሰላዮቹ ደግሞ ያለ ቀይ ፈትል መሀላቸውን እንደሚያፈርሱ ነግረውኝ ነው የሄዱት /ታስብና/ ልጆቼ ከዚህ የትም እንዳትነቃነቁ....ገበያ ደርሼ መጣሁ /ሮጣ ትወጣለች/

አማት ፡- /እየገቡ/ እቺ አሮጊት እንዴት እንዴት ትሮጣለች ባካችሁ /ወደ ልጆቹ ዞረው/ ኑ ውጡ ከዚህ ውጡ

ልጅት ፡-  እማማ አትውጡ ብላናለች አንወጣም

አማት ፡-  ነይ ውጭ የእናቷ ልጅ /ይዘዋቸው ይወጣሉ/

 

     (ተርቢኖስና ሩፋሮስ የተለመደ ቦታቸውን ይይዛሉ)

 

ሩፊኖስ ፡- ወንድሜ ተርቢኖስ ከረአብ ታሪክ ምን ተማርክ

ተርቢኖስ ፡- ትጋትን ተስፋ አለመቁረጥን ክርስቲያን አምላኩን በሃይማኖት በምግባር በቀረበና ተስፋ ባደረገው ቁጥር ፈታኙ ዲያቢሎስ አንጀቱን ስነሚያር ክርስቲያንም ከእጁ ሊያመልጠው እንደሆነ ሲረዳ በክርስቲያኑ ላይ የሚከምርበት የፈተና አይነት የለም ግን ወንድሜ ሩፊኖስ ሆይ ረአብ ሰይጣን ያመጣባትን ፈተና ትወጣው ይሆን ያንንስ ወይ ፈትል ከየት ታገኛለች

ሩፊኖስ ፡- ፈተናዋን መወጣቱ እንኳን እንጃ የማውቀው ነገር የለም ሳታይ ያመነችው አምላክ በእርሱ መታመናን እስከ መጨረሻው ተስፋ ሳትቆርጥ ካፀናት የእርሱነቷን አይዘነጋውም ቀዩን ፈትል የማግኘቷ ጉዳይ ግን ያከተመለት ይመስላል ማክንያቱም ነጋዴው ሁሉ ወሬ ለማየት ሱቁን ጠረቃቅሞ ከግንቡ ላይ ነው የሚገኘው ካሌብም ከሩቅ ሆኖ ሲመለከት ቀዩ ፈትል የለም አዘነ ከማዘን ሌላ ምንም ሊያደርግላት አይችልም የእግዚአብሔር ሰው ቃልኪዳኑን አክባሪ በቃሉ የታመነ ነውና መንጋውም የኢያሪኮን ቅጥር ሊያፈርስ አስራሁለት ዙር ዞሮ የመጨረሻውንና 13ኛውን ለመጨረስ ግማሹን አገባዳDል

ተርቢኖስ ፡- ይህን 13ኛውን ዙር ከጨረሰ ኢያሪኮ ትጠፋለች ማለት ነው

ሩፊኖስ ፡- አዎን ኢያሪኮ ትጠፋለች ረአብም ቀዩን ፈትል ፍለጋ አሁንም እየተሯሯጠች ነው የኢያሪኮዋ ኮከብ በእንባዋ እየታጠበች ነው ድንገት አንዲት አሮጊት በስሟ ጠሯት ችግሯን ጠይቀዋት ቀይ ፈትል አንደምትፈልግ እርሳቸውም ቀዩን ፈትል በገንዘብ ሸጡላት የንጥቂያ ያህል ተቀብላቸው ከነፈች

ተርቢኖስ ፡- ወንድሜ ሩፊኖስ ...... ዘጠኝ ወር ሙሉ በማህፀኗ ተሸክማ የመለደቻቸው ልጆቻን ብታጣስ ምን ይውጣት ይሆን /እዛው ይቆማሉ/

ረአብ /ሮጣ ስትገባ/ ልጆቼ ምን በላቸው ልጆቼን /እያለቀሰች ቀዩን ፈትል ሰትሰቅል ሴት ልጇ ትገባለች/

ልጅት ፡- እማማ አንቺ እማማ እኚህ እማማ አላረጅማ አሉ ሲወስዱን ጊዜ ጥፍት ብዬ መጣሁ

ረአብ ፡- የት ናቸው ያሉት

ልጅት ፡- ሰካራሞቹ ቤት እዛ ሩቅ ነው! አጥራችን በር ጋ

ረአብ ፡- ከዚህ እንዳትነቃነቂ /ሮጣ ትወጣለች/

ተርቢኖስ ፡- ምንኛ የምታሳዝን ሴት ናት እግዚአብሔርን ብላ ነውና እርሱ ይርዳት

ሩፊኖስ ፡- ልጆቻን አግኝታቸዋለች ዳሩ ግን አንደኛው ልጅ አሮጊታ መልሰው ነጥቀዋት የቤቱን በር ከውስጥ ቆልፈውበታል ረአብም በሩን መደብደብ ተያይዛዋለች በድማሚት ቢመታ በሩ ክንፍች የማይል ነው መንጋው ዙሩን ሲጨርስ ምንም ያህል አልቀረውም ካሌብ ፈትል አይቶ ደስ ብሎታል ግን ረአብ የለችም ረአብ በፍጥነት ወደ ቤቷ ልትመለስ ካልቻለች የኢያሪኮውያን እጣ ለእርሳም ይደርሳታል

ተርቢኖስ ፡- ሰይጣን ምን ያህል  በክፉ ሰዋች ላይ አድሮ እንደሚጠቀም ታየኝ

ሩፊኖስ ፡- መች ጥርሱን አግጦ ፊት ለፊት መጣና እንደ ስጋዊ ምኞታችን ነው የሚመጣብን ለዚህም ነው በአሮጊታ  አድሮ ረአብን ያስጨነቃት ቀድሞ ቀዩን ፈትል አስነጠቃት አሁን ደግሞ ዘጠኝ ወር የማቀቀችበትን ልጃDን

ተርቢኖስ ፡- እንዴት ሆና ይሆን ምስኪን

ሩፊኖስ ፡- የመኝታ ቤቱን በር መደብደብ ተስፋ አስቆርጧት አንደኛውን ልጇንና ያገኘቻቸውን ዘመዶቻን ሰብስባ ሩጫዋን ወደ ቤት ተያይዛዋለች ምን ያጋጥማት ይሆን ዝም ብሎ ይጋዝ የነበረው መንጋ የመለከት ድምፅና ጩኧት ካሰማ ኢያሪኮ ድብልቅልቃ ይወጣል ቅጥሯም ይፈርሳል ረአብም ከቤት አልተገኘችምና ከአንድ ልጇና ዘመዶቻ ጋር ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ይቀራል ረአብ ለመዳን  የሚያስፈልጋት በሩቅ ባመነችው አምላኳ እርዳታ ጋር ከመጠን በላይ ትጋት ያለበት ሩጫ ብቻ

   

  (ረአብ ከነዘመዶቻ  ከቤት ስትገባ ድብልቅልቅ ይሆናል ጥሩንባ ይነፋል)

 

ረአብ ፡- /ቆማ እያየች/ እያሪኮ ጠፋች የጨረቃ ከተማ ወደምሽ አንዱን ልጄን ከፍርስራሽ ስር  አስቀረሽ /እያለቀሰች/

2ኛሰላይ ፡- /እየገባ ጦር ይይዛል/ በፍጥነት ...... በፍጥነት ውጡ /ይዟቸው ይወጣል/

ተርቢኖስ ፡- ውድ ወንወድሜ ሆይ በቁፋሮ ቃርምክ....በብራና የከተብከውን ታሪክ ስላስነበብከኝ እግዚአብሔር ይስጥልኝ

ሩፊኖስ ፡- አሜን አብሮ ይስጥልኝ ከታሪኩ ብዙ ቁም ነገር እንዳገኘህበት ይገባኛል ሰው መፈጠሩ በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ነውና ክርስቲያን በመንፈስ የሚያመልከው እግዚአብሄርን የአለም ወጥመድና የሴይጣን ተንኮል ቢደራረብበት አምላኩን ዘወትር ተስፋ ማድረግ ይገባዋል ያድነዋለወ....ይታደገዋል.......ያስብለታልም

ተርቢኖስ ፡- ሰይጣንን እንቢ በሉት

ሩፊኖስ ፡- እግዚአብሔርን እሺ በጄ በሉት

በህብረት ፡- የሰማዩን መንግስት ያወርሳችኋል

 

ወስብሀት ለእግዚአብሔር

በነሀሴ 27/1992 ዓም በአናንያ ምድብ ቀረበ

ምንጭ- ሀመር1ኛ ዓመት ቁ.6

አዘጋጅ- ዘነበ ክፍሉ

አቅራቢ- አናንያ ምድ                    

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine