ግጥሞች

ምን አለ ቢቀጥል

በጣም ያምር ነበር ቢሆን ለሁል ጊዜ

መጾም መጸለይ እስኪ ጠፋ ወዜ

ለኃጢአት ብዛት እንባዬን ማፍሰሴ

ድካሙን በመቻል ቆሜ ማስቀደሴ

ዘወትር በኪዳን መትጋቴ

ሌሊት በሰዓታት ቤቱ መገኘቴ

የሰርኩን ጉባኤ ማታ መካፈሌ

መሃላ ማቅረቤ እስኪፋቅ በደሌ

ንሰሐ አባቴ ዘንድ ቀርቤ መማሬ

ስርየት ለማግኘት ልቤን ማስመረሬ

እንዴት ያምር ነበር ቢሆን ለሁል ጊዜ

ለነፍሴ ማሰቤ ማዘን መተከዜ

ለምስጋና ብቻ አፌ መከፈቱ

ጸሎትን ማድረጌ ሁሌም በሰዓቱ

ጉልበቴ እስኪ መለጥ መውደቅ መነሳቱ

ሥጋም ቢቀርባት የምግብ አይነቱ

ልቤም በፍቅር ዓይን ሁሉን መመልከቱ

እግሬም መሸ ጠባ ቤቴል መገስገሱ

በምጽዋት ሥራ እጄም መቀደሱ

የንሰሐ እንባ በጉንጬ መፍሰሱ

እንዴት ያምር ነበር ይህ ሁሉ ቢቀጥል

መታዘዝ ትህትናው በጾም ብቻ ባይቀር

ባይሆን ጥሩ ነበር እንዲሁም ለጊዜው

እስከ ዕለተ ሞቴ ቢቀጥል ሱባኤው

ግን ምን ያደርጋል በቀን ተገድቧል

በጎ ሥራ ሁሉ በጾም ወቅት ሁኗል

ሌላ ጊዜማ ጽድቅን ማን ያስባል

መጾም መጸለይ እንኪጠፋ ወዜ

ኃጢአትን በመሸሽ በጽድቅ መጓዜ

እንዴት ያምር ነበር ቢሆን ለሁል ጊዜ

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine