ጸሎት /ለሕፃናት/

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ዛሬ ስለ ጸሎት ምንነት እን አደራረግ ዝግጅቱን በተመለከተ ትማራላችሁ፡፡ በደንብ ተከተሉኝ እሺ፡፡

ጸሎት “ጸለየ” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ የቃሉ ፍችም አመሰገነ፣ ለመነ፣ ዘመረ ማለት ሲሆን ጸሎት ማለት ልመና ፣ ምስጋና ፣ ዝማሬ ይኸውም ከአምላክ ጋር መነጋገር ማለት ነው፡፡

ጸሎት የሚቀርበው ለእግዚአብሔር/ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡ ጌታችንም ”ለምኑ ይሰጣችኋል ፈልጉ ታገኛላችሁ ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋል” ማቴ. 7፥7 በማለት መጸለይ እንደሚገባን አስተምሮናል፡፡

ጸሎት ጥቅም

ጸሎት ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ለዚህ ትምህርት እንዲሁኑ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እንመለከታለን።-

-    እግዚአብሔርን ለማመስገን ይጠቅመናል፡፡

-    በጸሎት በደላችንን ኃጢአታችንን ለእግዚአብሔር እንናዘዛለን(እንናገራለን) ይቅርታውንም እንለምናለን፡፡

-    ከእግዚአብሔር ዘንድ የፈለግነውንና የጎደለንን ለማግኘት ያስችለናል፡፡

-    መንፈሳዊ ኃይል እንድናገኝ ያስችለናል፡፡

እንግዲህ ጸሎት ይህን ያህል ጥቅም እንዳሉት ከተረዳን እንዴት መጸለይ እንደሚገባን እንደሚከተለው እንማማራለን፡፡

ጸሎት እደራረግ ሥርዓትና ዝግጅት

ልጆችዬ ጸሎት በቤተክርስቲያን በዘፈቀደ የሚከናወን ሳይሆን ራሱን የቻለ ሥርዓት ያለው ነው፡፡ ይህም ከመጸለያችን በፊት በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ማድረግ የሚገባንን ዝግጅት ለመረዳት ያስችለን ዘንድ በሁለት ወገን ከፍለን እንመለከተዋለን፡፡ ከእነዚህም አንዱ ውጫዊ /አፍአዊ ዝግጅት/ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውስጣዊ ዝግጅት ነው፡፡ በዛሬው ትምህርታችን ውጫዊ /አፍአዊ ዝግጅቶች/ ውስጥ የሚጠቃለሉትና ማድረግ የሚገባንን እንመለከታለን፡፡

ውጫዊ/አፍአዊ/ ዝግጅት

ሀ. መታጠብና አለባበስን ማስተካከል

-       ከመኝታ ተነስተን ወደ ጸሎት ከመሄዳችን በፊት እጅንና ፊትን መታጠብ ያስፈልጋል

-       ነጠላ መስቀለኛ ማጣፋት

-       ወደ ቤተክርስቲያን ሲኬድ ረዥም ልብስ መልበስ

-       ሴቶች በጸሎት ጊዜ ጸጉርን መከናነብ ቀሚስ መልበስ ይገባል፡፡

ለ. መብራት ማብራት

-       በጸሎት ጊዜ መብራት ማብራት መጽሐፍ ቀዱሳዊ ትምህርት የሚሰጥ ሰማያዊ ምሳሌ ያለው ነው፡፡

-       የሚበራውም መብራት የእግዚአብሔርና የቅዱሳኑን ብርሃንነት ያስታውሰናል፡፡ ማቴ. 5፡16

-       ጧፍ ወይም ሻማ አብርተን ስንጸልይ ቅዱሳን መላእክት በዙሪያችን  እንዳሉ ያሳስበናል፡፡

ሐ. አቋቋም /ቀዊም/

-       ለጸሎትና ለምስጋና በምንቆምበት ጊዜ በቅዱሳን ሥዕላት ፊት በመቆም እንደሥዕሉ ባለቤት የሥላሴ /የእግዚአብሔር ወልድ ከሆነ የአምልኮት፣ የእመቤታችን ና የቅዱሳን ከሆነ የጸጋ የአክብሮት ስግደት በመስገድና በመሳለም ለሥዕሉ ባለቤት ያለንን ፍቅር አንገልጥባቸዋለን፡፡

-       ዓምድ /ግድግዳ/ሳይደገፉ፣ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ መቆም ይገባል፡፡ “በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ” እንዲል ቅዱስ ዳዊት መዝ. 5፥3

-       እግርን አጣምሮ መቆም አይገባም፡፡

-       ካልታመሙ ለመቆም የማያስችል ችግር ከሌለ ተቀምጦ/ተኝቶ/ መጸለይ አይገባም፡፡

-       ቅዱሳን ሥዕላት ከሌሉ ፊትን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ወደ ግራና ቀኝ ሳያዩ መቆም እጆቻችንን ከሰውነታችን መስቀለኛ አድርጎ በመዘርጋት “በሌሊት በቤተ መቅደስ እጆቻችሁን አንሱ እግዚአብሔርንም አመስግኑ” መዝ.133፥2 እንዲል ቅዱስ ዳዊት

-       ዓይንን ወደ ሰማይ በማንሳት መጸለይ ይገባል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ዓይንን ከፍቶ ወደ ሰማይ አቅንቶ መጸለይን ነው፡፡ ለዚህም አልዓዛርን ባስነሳው ጊዜና ኅብስቱን አበርክቶ ሲያበላ ያደረገውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዮሐ. 11፥41፤ 17፥1

መ. ማማተብ

-       ጸሎት ሲጀመርና ሲፈጸም አመልካች ጣትን ከሌሎች ጣቶች ጋር አመሳቅሎ በትእምርተ መስቀል አምሳል ከላይ ወደ ታች ከግራ ወደ ቀኝ በማድረግ ሳይፈጥኑና እጅን ሳያወራጩ ረጋ ብሎ ማማተብ ይገባል፡፡

-       መስቀልን የሚያነሳ ቃል ስንጣራም ማማተብ ያስፈልጋል፡፡

-       ስናማትብ “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አአትብ ገጽየ ወኩለንታየ በትእምርተ መስቀል ” እያልን ነው፡፡

-       ስናማትብም የዲያብሎስ ሠራዊትን እናርቅበታለን የጠላትን ኃይል ድል እንነሳበታለን፡፡

ሠ. አስተብርኮ \ስግደት\

-       በጸሎት መጀመሪያና መጨረሻ ጉልበትን በማስተብረክ መስገድ መጸለይ ይገባል፡፡

-       ስግደትን የሚያነሳ አንቀጽ  ሲደርሱም ለእግዚአብሔር መስገድ ያስፈልጋል፡፡

-       በዕለተ ሰንበት (ቅዳሜ እና እሑድ)፣ በበዓለ ሃምሳ በበዓለ ወልድ በ29፣ በእመቤታችን፣ በ21 በቅዱስ ሚካኤል በ12፣ ሥጋና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ በነዚህ ቀናት ጉልበት ምድር አስነክቶ መስገድ አይገባል፡፡

ረ. ደረትን መድቃትና ዕንባን ማፍሰስ

-       ስንጸልይ በትሕትና በጸጥታ ሆነን ለሌላ ሰው እንዳይሰማ ለራሳችን ጆሮ ብቻ እንዲሰማን አድርገን ኃጢአታችንን እያሰብን ደረታችንን መድቃት ይገባናል፡፡

-       ኃጢአታችንን በማሰብ ማልቀስም ያስፈልጋል፡፡

ሰ. ጸሎትን አለማቋረጥ

-       ጸሎትን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ በቃልም ሆነ በምልክት መነጋገር አይገባም

-       ጸሎቱን የሚያቋርጥ ችግር ከገጠመን አባታችን ሆይ ብለን ጸልየን ንግግራችንን ስንፈጽም ወደ ጸሎት ስንመለስ በድጋሚ አባታችን ሆይ ብለን ያቋረጥነውን መቀጠል ይኖርብናል፡፡

-       ጸሎት መጸለይ ከጀመርን ጀምሮ አንድ ቀን መተው በሌላ ቀን መጸለይ ሳይሆን ከጀመሩ አለማቋረጥ ተገቢ ነው፡፡

ማጠቃለያ

-       እንግዲህ ልጆች ጸሎት ንጹሕ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሔርን የምንነጋገርበት እንዲሁም አምላካችን እግዚአብሔር ያከበራቸውን ቅዱሳንን የምናናግርበት እንዲያማልዱን የምንማጸንበት መሆኑን አውቃችሁ በንጽሕናና በሥርዓት መጸለይ፣ ከመጸለያችሁ በፊትና በጸሎት ጊዜ መደረግ ያለበትን ዝግጅት በተማራችሁት መሠረት በሚገባ መፈጸም ይጠበቅባችኋል፡፡

-       ልጆችዬ እስከ ዛሬ ጸሎት ያልጀመራችሁ ካላችሁ ጀምሩ፤ የጀመራችሁ ደግሞ ሳታቋርጡ አጠናክራችሁ ቀጥሉበት፡፡ ይህንን ስታደርጉ አምላካችን እግዚአብሔር ይወዳችኋል፡፡

-       በመጨረሻም ለመጸለይ ውስጣዊ ዝግጅት እና የጸሎት ጊዜያትን በተመለከተ በክፍል ሁለት ትምህርት እስክንገናኝ መልካሙንና የተወደደውን ነገር ሁሉ እመኝላችሁአለው፡፡

በሉ ደኅና ሁኑ ልጆች

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

በፍሬሕይወት ጸጋዬ ዘኆኅተ ብርሃን

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine