ኆኅተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ወደ ጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የበጎ አድራጎት ጉዞ አዘጋጀች

በወለተ ትንሣኤ

‹‹መልካም ሥራ የክፉ ቀን ስንቅ ነው ››

በሰባተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት (ኒቆዲሞስ) የኆኀተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና የአካባቢው ምዕመናን  በሰንበት ትምህርት ቤቱ በጎ አድራጎት ክፍል አስተባባሪነት  እሑድ መጋቢት 20 ቀን ፣ 2007 ዓ.ም. በሕመም የተጎዱ ወገኖችን የመጠየቅ መርሐ ግብር ተከናውኗል ፡፡

 

በ2:15 ሰዓት የደብሩ አገልጋይ በሆኑት በአባ ኃይለ ማርያም መርሐግብሩ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ በ2:25 ሰዓት መድረሻውን እንጦጦ ማርያም ከሚገኘው የጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ  ማዕከል ያደረገው ጉዞ ተጀመረ፡፡ ጉዞው  የንስሐ መዝሙራትን በመዘመር ቀጠለ፡፡ በ 3:00 ሰዓት የሰ/ት/ቤቱ የበጎ አድራጎት ዋና ክፍል ሰብሳቢ የሆነው መምህር ደረጀ … ‹‹ የሚሰጥ በልግስና እና በደስታ ይስጥ ›› ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክት መነሻነት ለ15 ደቂቃዎች … ያህል አስተማረ፡፡ ትምህርቱ አምላካችን ክርስቶስ ዳግመኛ በሚመጣ ጊዜ የሚጠይቀንን ‹‹ ተርቤ አብልታችሁኛልን ፣ ተጠምቼስ አጠጥታችሁኛልን ፣ እንግዳ ሆኜስ ተቀብላችሁኛልን ፣ ታርዤስ አልብሳችሁኛልን ፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛልን ፣ታሥሬ ወደ እኔ መጥታችኋልን ???››  የሚሉትን የፍቅር ጥያቄዎች ለመመለስ ምን ያህል እንደተዘጋጀን የጠየቀ እንዲሁም ዛሬ በምናደርገው መልካም ሥራ ለሰማያዊ ቤታችን መሠረት እየጣልን እንደሆነ ያስገነዘበ ነበር፡፡

 

ከዚህ በኋላ ሰንበት በመሆኑ የመጓጓዣው መኪና ውስጥ ተጓዡ የተዘጋጀለትን ቁርስ እንዲበላ ተደረገ፤ ከረፋዱ 3:25 ሰዓት ላይ መኪናው ጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ደረሰ፡፡ ተጓዡ እንደ አቅሙ ለሕሙማኑ ያዘጋጀውን ስኳር ፣ በሶ ፣ ቆሎ ፣ጤፍ ፣ አልባሳት አንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ሳሙና ፣ ሶፍት ፣ ቅባት ለማዕከሉ ካስረከበ በኋላ ከ 3:30-4:20  በቡድን በቡድን በመከፋፈል ሕሙማኑን ከመጠየቅ ባሻገር ሊታዩ የሚገቡ ቦታዎችን በመጎብኘት የበረከት ተካፋይ ሆኗል፡፡

 

በዛፎች በተከበበው በዚህ አካባቢ የተለየ ደስታን የሚሰጥ ርጥበት ያለው አየር ይነፍሳል ፤ አልፎ  አልፎ ከሕሙማን ከሚወጣው ድምጽ ውጭ ብዙም ድምጽ አይሰማበትም፤ ጠባብ ከመሆኑ በስተቀር በንጽህናና በአግባቡ የተያዘ እንደሆነ መናገር ይቻላል ፡፡  መጀመሪያ የተጎበኘው የእኅቶች መኖሪያ  ጠባብ ክፍል ሆኖ በሥርዐት የተደረደሩ ተደራራቢ አልጋዎች ፣ በአግባቡ የተወለወለ የላስቲክ ምንጣፍ ተነጥፎ የሚታይበት ነው፡፡ በዚህ ክፍል ሕሙማን ራሳቸውን እምብዛም የማያውቁ በመሆናቸው ሽንትና ሰገራቸውን አልጋ ላይ እንደሚጸዳዱ እንዲሁም ቶሎ ካላጸዱት  እርሱኑ ለመመገብ እንደማይመለሱ በጊዜው የተደረገው ገለፃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ የተነሣም ወደ ክፍሉ ሲዘለቅ አፍንጫን የሚሰረስር ሽታ ጎብኚን ይቀበላል፡፡  ሕሙማኑ አንዳንዴ ከቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ ለማሠሪያነት የሚጠቀሙባቸው ሰንሰለቶችም በአልጋቸው ላይ ተንጠልጥለዋል፡፡ ከዚህ ክፍል በመቀጠልም ይህንኑ ክፍል የመሰለ የወንዶች ማደሪያ ይገኛል ፡፡

 

በሌላኛው ክፍል የአእምሮ ሕሙማን ያልሆኑ አልያም ከሕመማቸው ያገገሙ እኅቶች ይገኛሉ፡፡ እኛ በተገኘንበት ቀን በቅርብ ከተወለደ  ጤነኛ ልጇ ጋር አንድ እናትንም ተመልክተናል፤ በዚሁ ተመሳሳይ የወንዶች ክፍል የሚገኙ በአግባቡ ያገገሙና ራሳቸውን የሚያውቁ ከዚህ አልፎም ውኃ በመቅዳት ፤ ታማሚዎችን በማስታመም ሁሉ እየረዱ ያሉ ተረጂዎች እንዳሉ ለመገንዘብ ችለናል፡፡

ከነዚህ ክፍሎች በተጨማሪ የመመገቢያ ክፍል ፣ የጸሎት ቤት ፣ የመጸዳጃ ቤትም በማዕከሉ ውስጥ ይገኛሉ ፡፡

በስተ መጨረሻ የተጎበኘው ክፍል ስለ ማዕከሉ አጠቃላይ መረጃ የተገኘበት ነው ፡፡ ማዕከሉ ከተመሠረተበት ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ 119 ሰዎች በጠቅላላ የተረዱ ሲሆን ከነዚህም መካከል 57 በመረዳት ላይ ያሉ ፣ 52 ፈውሰ ሥጋን አግኝተው የተሰናበቱ እንዲሁም 10 በሞት የተለዩ መሆናቸው ተገልፆልናል፡፡ በዚህ ክፍል በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድና ማዕከሉ   በነበረው በጎ ሥራ ፈውሰ ሥጋን አግኝተው የተሰናበቱ ፣ በሞት የተለዩ እንዲሁም የተሻላቸው ሥራ ሲሠሩ የሚያሳይ በተጨማሪም በተለያየ ጊዜ የጎበኙ ወገኖች ፣ ሕሙማን በዓላትን ከወገኖች ጋር ሲያከብሩ የሚያሳዩ ምስሎች ግድግዳው ላይ ተለጥፈዋል፡፡

 

ከዚህ በኋላ የሰ/ት/ቤቱ አባላትና ምዕመናን ከማህበሩ መስራች ከወንድም መለስ ጋር ጥቂት ቆይታ ካደረጉ በኋላ  የሕሙማኑን እግር በማጠብ ፣ ጥፍሮቻቸውን በመቁረጥ ፣ የሴቶቹን ጸጉር ሹሩባ በመሥራት በረከትን አግኝተዋል፡፡ በመጨረሻም አገልግሎቱ እንዴት ይቀጥል በሚል መነሻ ሐሳብ ውይይት ተደርጎ  እግዚአብሔር እንደፈቀደ 5:50 ላይ የመልስ ጉዞ ተጀምሯል፡፡

 

ጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን ማዕከል የብዙዎችን በተለይም በሕክምና ሙያ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ድጋፍ የሚፈልግ እንደሆነ በመርሐ ግብሩ የተካፈለ ሁሉ ያስተዋለው ከመሆኑም ባሻገር የማኅበሩ መሥራችም አጽንዖት ሰጥቶ ያሳሰበው ጉዳይ ነው፡፡ የቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤትም ይህን የሚያነብ ሁሉ የቻለውን ያደርግ ዘንድ በበጎ አድራጎት ዋና የአገልግሎት ክፍሏ በኩል በእግዚአብሔር ስም ታሳስባለች፡፡

 

ሰንበት ትምህርት ቤቷ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ጊዜ ተመሳሳይ የበጎ አድራጎትና ገዳማትን የመደገፍ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት በብዙዎች ጸሎት የምትታሰብ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በቀጣይም በጎ አድራጎትና ገዳማትን መርዳት የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅዷ አካል እንደመሆኑ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ይበልጥ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት ትተጋለች፡፡

 

እግዚአብሔር አገልግሎታችንን ይቀድስልን፤ አሜን፡፡

 

                                                                                                             ቸር እንሰንብት !

ተያያዥ ገጾች

Joomla templates by Joomlashine