ቅዱስ መስቀል

                                       በደሳለኝ አላምሬ ዘኆኅተ ብርሃን

        መስቀል የሚለው ቃል ሰቀለ ከሚለው የግእዝ ሥርወ ቃል የወጣ ሲሆን መሰቀያ ማለት ነው፡፡ ጌታችን አይሁድን ፈሪሳዊውያንን ሕጋቸውን ቢነቅፋቸው ግብራቸውን ተመልክቶ ቢገስጻቸው ጠልተውት በስቀል ሰቅለውታል፡፡ ኋላም መስቀሉ ሽባዎችን ሲተረትር ጎባጣወችን ሲያቀና ለምጻሞችን  ሲያነጻ ተአምራት ሲያደርግ አይተው ለተንኮል ለምቀኝነት የማያንቀላፉ ናቸውና ጉድጓድ አስምሰው ቀበሩት፡፡ ተቀብሮም እንዳይወጣ ብዙ ቆሻሻ ሲጥሉበት፣ሰያስጥሉበት ኖረዋል፡፡

        ከሁለት መቶ ዘመን በኃላ የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ዕሌኒ ልጇ ቆስጠንጢኖስ ደገኛ ሃይማኖተኛ ይሆንላት ዘንድ በዘመኑ የሃይማኖት ተቆርቋሪ (ስለቆመ) ከአረማዊያን ወገን ስለነበረች ከነሱ መከራ ከጠበቅኸኝ አይሁድ በክፋት የቀበሩትን መስቀልህን አወጣለሁ ብላ ብጽዐት ገብታ ነበርና ብጽዓቷን ለመፈጸም በ319 ዓ.ም ኢየሩሳሌም ወረደች፡፡ ዘመኑ ርቆ ነበርና የሚውቅላት አጥታ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊን ጨው የበዛበት ምግብ አብልታ ውሃ ከልክላው ለውኃ ሲል ‹‹በውል ለይቼ አላውቀውም አባቶቻችን ከነዚህ ከ3ቱ ተራሮች አንዱ ነው›› ይሉ ነበር ብሎ አመለከታት፡፡ ካህናቱን ሰበስባ ደመራ አስደምራ ዕጣን ብታጤስበት ጢሱ ወደ ሰማይ ወጥቶ ብርሃን ተስሎበት ተገኝቷል፡፡ ሕሙማንን ፈውሷል ዕውር አብርቷል፡፡ በቦታው ላይ ለትንሣኤው መታሰቢያ ታላቅ ቤተክርስቲያን አሳንጻበታለች፡፡

        ጊዜው ወርኃ ጾም ስለነበርና በጾሙ ምክንያት በዓል ማድረግ ስለማይችሉ ቦታው በተገኘበት ቁፋሮ በተጀመረበት በዚህ ዕለት በዓል እንዲደረግ ሥርዓት ሠርተዋል፡፡ ከጊዜያት ባንዱ ምእመናን አጎበር ጥለው ተሰብስበው ሲያከብሩ ይስሐቅ የሚባል ሳምራዊ አምላካችሁ ይህን ቆሻሻ ውኃ ንጹሕ  ቢያደርገው ባመንሁ ነበር አለ፡፡ አንጋቢስ የተባለ ካህን ጸልዮ ንጹሕ አድርጎት ምእመናን ጣፈጧቸው ጠጥተውታል፡፡ እሱም እጠጣለሁ ብሎ ቢሄድ አንደ ወትተ ነጽቶ የነበረው ጠቁሮ እንደ ማር ጣፍጦ የነበረው መሮ የማይጠጣው ሆነ፡፡ ንስሐ ገብቶ አምኖ ተጠምቋል፡፡ ይህም የመስቀሉ ክብር ነው፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን የመስቀሉን ክብር በረከት ረድኤት በማሰብ መስከረም 16 እና 17 በየዓመቱ ደመራ በመደመር በሁሉም አድባራትና ገዳማት እናከብራለን፡፡ ‹‹ክብር የሚገባውንምሰ አክብሩ››ሮሜ 13፣7

 ምንጭ፡- መዝገበ ታሪክ 1 እና 2 ገጽ፡- 32 እና 7

ክብረ ቅዱስ መስቀል

ቅዱስ መስቀል ስንል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ከሞት፣ ከመከራ፣ ከስቃይ፣ ከኃጢአት፣ለማዳን በቀራንዮ የተሰቀለበት የመስቀል ዕፅ ማለታችን ነው፡፡ ለቃነ ካህናት መስፍኑ ጲላጦስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት በፈረደበት ጊዜ ወታደሮቻቸው ጌታችንን አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት፡፡ ‹‹መስቀሉን ተሸክሞ ቀራንዮ ወሰዱት ›› እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዮሐ19፣17

ጌታችንኢዮሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲጓዝ እያጣፉና እየገፉ ሲወስዱት እጅግ ደከመ በዚህን ጊዜ ስምዖን የተባለ ሰው ቀሪናዊ ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኃላ የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም ጫኑበት፡፡ ሉቃ 12፥26 ከዚህም እንደገና ራሱ ጌታችን መስቀሉን ተሸክሞ ቀራንዮ ደረሰ እንደ ደረሰም በመስቀል ሰቀሉት በቀኙና በግራውም በኩል ሁለት ወንበዴዎችን ሰቀሉ ጌታችን ኢየሱስም በመስቀል ላይ ሆኖ መከራ መስቀልን በመቀበል በዕለተ ዓርብ በዘጠኝ ስዓት በፈቃዱ ስለ እኛ ሞተ፣ በ11 ስዓት ገደማም ዮሴፍ ዘአርማትያስና ኒቆድሞስ ከመስቀል አውርደው በአዲስ መቃብር ቀበሩት ሉቃ. 23፥30-44 ዮሐ. 19፥38-42 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ቅዱስ ደሙ ሰላምን አወጀ፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ሰለዚህ ታላቅ ምሥጢር ሲናገር ‹‹በመስቀሉ ደም ሰላምን አደረገ በሰማያትም በምድርም ላሉት እርቅን፣ ሰላምን አደረገላቸው›› ቈላ. 1፥19 በመስቀል ጠላታችን ዲያብሎስን ገደለልን በመስቀሉ ቀጥቅጦ ከእግራችን በታች ጣለው ሰላሙን ለሁላችን ሰጠን የሰላም ባሌበት አለቃ አርሱ ነውና፡፡

‹‹አሁን ግን ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀረባችሁ፡፡ ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላማችን እርሱ ነውና በሥጋውም በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ጥልን ሻረ፡፡ ሁለቱን አድሶ አንድ ያደረጋቸው ዘንድ በሥርዐቱ የትእዛዝን ሕግ አጠፋ እርቅንም አደረገ፡፡ በመስቀሉም በአንድ ሥጋው ሁለቱን ወደ እግዚአብሔር አቀረባቸው በእርሱም ጥልን አጠፋ››፡፡ ኤፌ 2፥13-18 ስለዚህ ቅዱስ መስቀል ከርስቶስ የተሰዋበት በቅዱስ ደሙ ያከበረውና መለኮታዊ ደሙም የፈሰሰበት ስለሆነ በእውነት ክቡር፣ በእውነት ቅዱስ ነው፡፡ በመሆኑም ሐዋርያው እንዲህ እንዳለ በእውነት ከርቶሳዊያን የሆን ሁሉ በጌታችን በክቡር መስቀሉ እንመካለን፡፡ ገላ. 6፥14 ‹‹እኔስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ››

ምንጭ፡- አቡነ ገብርኤል ክብረቅዱሳን በሚል ርእስ በ1990 ከአሳተሙት የተወሰደ    

 

ወስብሐት  ለእግዚአብሔር

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine