ሰሙነ ሕማማት ክፍል-1

(ክፍል-1 ከእሑድ እስከ ሐሙስ)

መድኃኔዓለም ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ የተመላለሰው ከክብሩ የተዋረደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ ሊመልሰው ፈቅዶ ነው፡፡ ይህንኑ ሲያጸና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር ይኸውም ዲያብሎስ ነው በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡›› /ዕብ. 20405//// ብሏል፡፡ አምላክ በፍጹም ፍቅር ተስቦ የሰውን ልጅ ሊያድን ቢወድም የሰው ልጅ ግን በመልካም አልተቀበለውም፡፡ ‹‹የእርሱ ወደ ሆነው መጣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም››  /ዮሐ. 101/ ቢራቡ ስላበላቸው ቢታመሙ ስለፈወሳቸው ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር›› ሆነና እንዲሞት ተማከሩበት፡፡ ከመሆኑ ከመታሰቡ አስቀድሞ ሁሉን የሚያውቀው አምላክ ግን ብዙ ጊዜ ሊይዙት ቢሞክሩም ጊዜው አልደረሰም ነበርና በእጃቸው አልወደቀም ነበር፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓለም ሥራውን ሲፈጽም ሳለ የሰው ልጅ ድኅነት እጅግ ውድ የሆነ ካሳን የሚጠይቅ ነበርና ያን ለመክፈል በፈቃዱ ራሱን ለሕማምና ለሞት አሳልፎ ሰጠ ይህም ድኅነታችን የእግዚአብሔር ልጅ ደሙን እስኪያፈስለት ድረስ የቱን ያህል ውድ መሆኑን የሚያስተምር ነው፡፡ ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፉ ‹‹መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ መኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ታርደሃልና በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው በምድርም ላይ ይነግሣሉ፡፡›› /ራዕ. 590/ በማለት ድኅነታችንን በታላቅ የደም ካሳ የተገኘ መሆኑን የገለጸው፡፡

ሰሙነ ሕማማት የሚለውም ቃል ይኸው የድኅነት ሥራ የተፈጸመበትን ሰሙን (ሳምንት) የሚያመለክት ነው፡፡ ሕማማት የሚለው ቃል ሐመ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ሕማማት እያልን የምናነሳው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ ድኅነት ሲል ወዶ የተቀበላቸውን ልዩ ልዩ ጸዋትዎ መከራዎች የሚመለከት ነው፡፡

በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ በፊት ያለው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ሰሞን ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን ቤተክርስቲያን ባወጣችው ሥርዓት ጸሎት መሠረት የተደረገላቸውን ታላቁን ውለታ በማሰብ በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው ከበፊቱ አብዝተው በመጾም በመጸለይና በመስገድ ከኃጢአት እርቀው የሕማሙን ነገር የሚያወሳ ዜማ ሲያዜሙ ግብረ ሕመማት በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ ሲያነቡ ይሰነብታሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ ሕመማትን መቀበሉ ስለምን ነው ቢሉ፡-

·         ፍቅሩን ለመግለጽ፡- ለፍጥረቱ ይልቁንም ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅሩን ይገልጽ ዘንድ  ‹‹. . . እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡ ›› /ዮሐ. 306/ ‹‹ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከማኖር ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም፡፡›› /ዮሐ. 0503/ ምንም በደል ሳይኖርበት ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡

·         የኃጢአት ፍዳ ከባድነት ለማሳየት፡- እርሱ ጻድቅና ንጹሕ ሆኖ ሳለ ሰውን ወዶ ይህን ያህል መከራ ከተቀበለ ሰው ኃጢአት በመሥራት ቢመላለስ የኃጢአትን ውጤት ከባድነት ያስተምረናል፡፡ ራሱ ጌታችንም ከጲላጦስ ግቢ እስከ ቀራንዮ አደባባይ መስቀል ተሸክሞ ሲንገላታ ላለቀሱለት ለኢየሩሳሌም እናቶች ‹‹በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ በደረቀውስ እንዴት ይሆን?›› /ሉቃ. ፳3፥፴1/ በማለት ገልጽዋል፡፡

·         ቤዛ ለመሆን፡- በኦሪት ዘመን ሰዎች ለሰሩት ኃጢአት ኃጢአታቸውን ለማስተስረይ ነውር የሌለበትን በግ ቤዛ እንዲሆናቸው መስዋዕት ያቀርቡ ነበር ይህ ግን ከአዳም የተወረሰውን ኃጢአት ማስቀረት ስላልቻለ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ መጣ፡፡ ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› /ዮሐ. 1፥፳9/

·         እርግማናችንን ለማስቀረት፡- ‹‹በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለእኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን›› /ገላ. 303/ በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው እርግማናችን ተሸክሞ ሕማማትን መቀበሉ የቀድሞው ኃጢአት ምንም ያህል ከባድ ቢሆን በታላቅ መስዋዕትነት እንዳስቀረልን ሊያስተምረን ነው፡፡

·         የድኅነታችንን ክቡርነት /ውድነት/ ሊያስረዳ፡- ድኅነታችን የእግዚአብሔር ልጅ ደሙን እስኪያፈስለት ድረስ እጅግ ውድ መሆኑን ሊያስተምረን፡፡

የሰሙነ ሕማማት ዕለታት

1.  እሑድ /ሆሣዕና/

      የመጀመሪያው ቀን ሆሣዕና ይባላል ትርጉሙም ‹‹እባክህ አሁን አድን›› ‹‹መድኃኒት›› ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን የማዳን ሥራውን ወደ ሚፈጽምባት ወደ ኢየሩሳሌም መግባት ይነገርበታል፡፡ ሲመጡም ሳሉ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ ያስፈልጉኛልና የታሰሩትን አህያና ውርጫ ይዛችሁልኝ ኑ ብሎ ላካቸው፡፡ በምሥጢሩ እኛን ከታሰርንበት የኃጢአት ማዕሰር ሊፈታን እንደ መጣ ለማጠየቅ ነው እነርሱም እንደታዘዙት ይዘው መጡ ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተመቅደስ 16 ምዕራፍ ሲሆን 14ቱን በእግሩ ሂዶ 2ቱን በአህያ ሂዶ ቤተመቅደሱን 3 ጊዜ በውርንጫዋ ዙሮ ወደ ቤተ-መቅደስ ገባ፡፡ ቀድሞ ነቢያት ዘመነ ጸብዕ (ጥል) በሆነ ጊዜ በፈረስ ተቀምጠው የጦር ዕቃ ይዘው ይታዩ ነበር ዘመነ ሰላም የሆነ ጊዜ ደግሞ በአህያ ተቀምጠው መነሳነስ ይዘው ይታያሉ እርሱም ዘመነ ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲል በአህያ ተቀምጦ መጣ፡፡ ‹‹ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል፡፡›› /ሉቃ. 09፥፵2/ ነቢዩ ዘካርያስም በትንቢቱ በአህያ እንደሚመጣ ሲናገር ‹‹ . . . ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡›› /ዘካ. 99/ በግራና በቀኝ የነበሩትም እንኳን አንተ የተቀመጥክባትም አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም እያሉ ግማሹ ልብሱን ግማሹ የዘንባባ ዝንጣፊ አነጠፉለት፡፡ አብርሃም ይስሐቅን ይስሐቅ ደግሞ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ እስራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ ዮዲት ሆሎፎርአስን በገደለች ጊዜ ዘንባባ ይዘው አመስግነው ነበርና በዚያ ልማድ ጌታችንንም ዘንባባ ይዘው ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ አመሰገኑት፡፡

      ከዚህ በኋላ ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ በዚያ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል እናንተ ግን የወንበዴ ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ በመቆጣት የለዋጮችን ገበታ እየገለበጠ አስወጣቸው፡፡ አይሁድም ሕጻናት ሲያመሰግኑት ሰምተው በቅንአት በታወረ ልቦናቸው ‹‹ዝም አስብላቸው እንጂ›› ቢሉት ‹‹ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋና ለራስህ አዘጋጀህ››       /መዝ. 82//የሚለው የመጽሐፍ ቃል ጠቅሶ አሳፍሮአቸዋል፡፡

2.  ሰኞ /ሁለተኛው ቀን/

በዚህ ዕለት የተደረጉት ዐበይት ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፡፡

·         መርገመ በለስ /ያላፈራችውን በለስ አረገመ/፡- ጌታችን በቢታንያ አድሮ ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበና ፍሬ ባገኝባት ብሎ ከመንገድ ዳር የነበረችውን በለስ ተመለከተ ፍሬ ስላጣባትም ‹‹ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ›› ብሎ ረገማት፡፡ በማርቆስ ወንጌል የበለስ ጊዜ አለመሆኑን ይገልጻል፡፡ ታዲያ ለምን እያወቀ እንዲህ አደረገ ቢባል አውቃለሁ ብሎ ሥራውን ከመሥራት እንደማይተው ሊያስተምረን ፈቅዶ ነው፡፡ በምሥጢሩ ከበለስ ፍሬ መሻቱ ከሰው ፍቅር ተርቦ በለስ እስራኤልን በኢየሩሳሌም አገኘ ሃይማኖት ምግባር አገኝባቸው ብሎ ቢያይ አጣባቸው፡፡ በዚህም ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡

·         አንጽሖተ ቤተመቅደስ፡- በሆሣዕና ዕለት ቤተመቅደሱን ከነጋዴዎች እንዳጸዳ የተረፈውን ጥቃቅኑን ደግሞ በዚህ ዕለት አጽድቶአልና አንጽሖተ ቤተመቅደስ ይባላል፡፡

3.  ማክሰኞ /ሦስተኛው ቀን/

በዚህ ዕለት የተደረጉት ዐበይት ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፡፡

 • ደቀመዛሙርቱ የበለሷን መድረቅ አይተው ሲገረሙ ጌታችን ሃይማኖት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩ ይህን ተራራ ከዚህ ተነስተህ ከባሕር ግባ ብትሉት ይቻላችኋል ብሎ ስለ እምነት አስተምሯቸዋል፡፡

o   ማቴ. ፳1፥፳-፳1 ፣ ማር. 01፥፳-፳6  ዮሐ. 041

 • በቤተመቅደስ ሲያስተምር ሳለ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች መጥተው ከምድራውያን ካህናት ወገን ያይደለህ ከምድራውያን ነገሥታት ወገን ያይደለህ ይህን የምታደርግ በምን ሥልጣንህ ነው ብለው ጠየቁት እርሱም ከእናንተ አኔ ቅድሚያ አለኝ ሲል ጠየቃቸው ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነው?›› (ዮሐንስ ማስተማሩ በማን ፈቃድ ነው?) እነሱም ከሰማይ እንዳይሉ አያምኑበት ከምድር እንዳይሉ ሕዝቡን ፈሩትና አናውቅም አሉት እርሱም እኔም አልነግራችሁም ብሎ ረታቸው፡፡

o   ማቴ. ፳1፥ ፳3-፳7 ፣ ማር. 01፥፳7‐፴3 ሉቃ. ፳፥፳1‐፵

 • አይሁድም ተሰብስበው ሳሉ ክርስቶስ ስለ ራሱ ማንነት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም የዳዊት ልጅ ነው ብለው መለሱለት እርሱም ‹‹እግዚአብሔር ጌታዬን …›› /መዝ.፻91/ በመጥቀስ የዳዊት ልጅ ከሆነ እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው እነርሱም አንዲት ቃል እንኳን ሊመልሱለት ተስኗቸው ዝም አሉ፡፡

o   ማቴ. ፳2፥፵1‐፵6    ማር. 02፥፴5‐፴6    ሉቃ. ፳፥፵1-፵4

 • ጸሐፍት ፈሪሳውያንን በግብዝነታቸው እየወቀሰ ለሐዋርያቱና ለሕዝቡ ‹‹በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋልና ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም ነገር ግ እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ፡፡ ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ እነሱ ግን በጣታቸውስ እንኳ ሊነኩት አይወዱም›› በማለት እየወቀሰ ተናግሯል፡፡

o   ማቴ. ፳31-፴9    ሉቃ. ፳፥፵5-፵7

 • ጌታ በምጽዋት ሳጥን ፊት ተቀምጦ ሳለ ያለትን ሁሉ ምንም ሳታስቀር የሰጠችውን የድሀዋን መበለት ስጦታ አደነቀ፡፡ ምንም እንኳን ከሀብታሞቹ ያነሰ ብትሰጥም እርሷ ያላትን ሁሉ ስትሰጥ እነርሱ ግን ከትርፋቸው ሰጥተዋልና፡፡

o   ማር. 02፥፵1-፵4    ሉቃ. ፳11-4

 • ስለዳግም ምጽአቱ ሰፊ ትምህርት የሰጠበትም ዕለት ነው፡፡ ከላይ ‹‹ደብረዘይት›› በሚለው ክፍል የተገለጸው በዚህ ዕለት የተነገረ ነው፡፡
 • በአጠቃላይ ይህ ዕለት በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ ጥያቄ የቀረበበትና መልስ የተሰጠበት ዕለት ስለሆነ የጥያቄ ቀን፣ ሰፊ ትምህርት ያስተማረበት ዕለት በመሆኑም የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡

4.  ረቡዕ /አራተኛው ቀን/

በዚህ ዕለት የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰብስበው እንዴት በተንኮል እንደሚይዙትና እንደሚያስገድሉት ምክር የቆረጡበት ዕለት ነው፡፡ ነገር ግን የፋሲካ በዓል ቀርቦ ስለነበር ሕዝቡም በትምህርቱ ተመስጦ በተአምራቱ ተማርኮ ስለነበር ሁከት እዳይፈጠር እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ሲጨነቁ ከጌታ ደቀመዛሙርት መሃል ይሁዳ ከምክራቸው በመቀላቀል ጭንቃቸውን አቀለለላቸው፡፡

    ማቴ. ፳635       ሉቃ. ፳21-6         ማር. 041እና2

ክርስቶስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በማዕድ ተቀምጦ ሳለ ማርያም መግደላዊት የምትባል ዘመኗን በዝሙት ያቃጠለች የመግደሎን አገር ሴት መጣች፡፡ ይህች ሴት ቀረሽ የማትባል ቆንጆ ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ሰውነቷን በመስታወት ተመልክታ ፈራሽ በስባሽ መሆኑን ስትረዳ በዚህ ገላዋ ባፈራችው ገንዘብ የማያልፈውን መንግሥት ለማግኘት ኃጢአቷን ለማስተሰረይ ቆርጣ ሽቶ ልትገዛ ሄድኖክ ከሚባል ነጋዴ ለነገሥታት የሚገባ ሽቶ ስጠኝ ብላ 3፻ ወቄት ወርቅ ሰጠችው፡፡ እርሱም በዘመናቸው ሐሰት የለም ነበርና ይህን ያህል የሚያወጣ የለኝም አላት ነገር ግን እናቱ የምታውቀው ዳዊት ሰሎሞን ተቀብተውበት የተረፈ ነበርና እርሱን ሸጠላት፡፡ እርሷም በስምዖን ቤት ገብታ በእግሩ ሥር በመደፋት ስለ ኃጢአቷ አነባች ንስሐዋንም ተቀብሎ ይቅር አላት፡፡ ያንንም ሽቶ አምጥታ ራሱን ቀባችው፡፡ ይህ ያዩ ሐዋርያት ተቆጡ ለምን ተሸጦ ገንዘቡ ለደሀ አይሰጥም ሲሉ፡፡ ነገር ግን ምሥጢሩ ጌታን ለመቃብሩ ስታዘጋጀው ነበር፡፡ ይህ ያስከፋው ይሁዳ ለድሆች ከሚሰጠው ገንዘብ ለራሱ ያስቀር ስለነበር ድርሻውን ለማስመለስ ጌታውን በ30 ብር ለመሸጥ በቃ፡፡ ለማርያም ግን ጌታችን ‹‹. . .  እርስዋ ያደረገችውን ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል›› እንዳለላት ይህንን ታሪክ አራቱም ወንጌላውያን መዝግበውታል፡፡

    ማቴ. ፳66-03      ማር. 043-9        ሉቃ. 7፥፴7-፴9         ዮሐ. 021-8

5.  ሐሙስ /አምስተኛው ቀን/

በዚህ ዕለት የተደረጉ ዐበይት ድርጊቶች፡-

 • የትህትና መምህር የሆነው ጌታችን ወደ አብ የሚሄድበት ጊዜ በመቅረቡ ትህትናን ሊያስተምር የደቀመዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ጀመረ ‹‹እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል›› በማለት የትህትናን ትምህርት አስተምሯል፡፡ /ዮሐ. 031-፳/
 • ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻዋን እራት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲበላ ምሥጢረ ቁርባንን ከዚህች ዕለት መስርቷል፡፡ ‹‹ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራውን አንስቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀመዛሙርቱ ሰጠና እባካችሁ ብሎ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡  ጽዋውንም›› አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፡፡ ሁለታችሁም ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡ በማለት ስለኛ በፈሰሰ ደሙ በኃጢአታችን ይቅርታ አድርጎ እንደታረቀን እንዲህ በማለትም አረጋግጧል፡፡‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፡፡›› /ዮሐ. 0505/

ማቴ. ፳6፥፳6-፳9         ሉቃ. ፳27-፳3

 • ጌታችን ደቀመዛሙርቱ ሁሉ በአይሁድ እጅ ሲወድቅ ጥለውት እንደሚሸሹ የመጽሐፍ ትንቢት ጠቅሶ ቢነግራቸው /ዘካ. 037/ ቅዱስ ጴጥሮስ  ጌታዬ ሞትህን ሞቴ ያድርገው እንጂ አልክድህም አለው፡፡ ጌታም ዶሮ ሳይጮኽ በዚህች ሌሊት ሦስት ጊዜ እንደማታውቀኝ ትክደኛለህ አለው፡፡

ማቴ. ፳6፥፴-፴5       ማር. 04፥፳6-፴1      ሉቃ. ፳2፥፴1-፴4    ዮሐ. 03፥፴6-፴8

 • ደቀመዛሙርቱ ወደ አብ እሄዳለሁ ባላቸው ጊዜ ልባቸው ታወከ እርሱም ‹‹እመኑብኝ እኔ የምሄደው በአባቴ ቤት ካለው ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው›› በማለት አጽናናቸው፡፡ ከሐዋርያት አንዱ ፊሊጶስ አብን አሳየን ቢለው ‹‹እኔን ያየ አብን አይቷል›› በማለት አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ፣ ወልድ በአብና በመንፈስ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስ በአብና በወልድ ሕልዋን እንደሆኑ አስተማራቸው፡፡ አስቀድሞ ከእናንተ እለያለሁ ሲላቸው ብቻቸውን የሚተዋቸው መስሏቸው ታውከው ነበርና እንዲጽናኑ አጽናኝ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጣቸው በመግለጽ አረጋጋቸው፡፡ /ዮሐ. 041-07/
 • ክርስቶስ ሊቀበላት ያለችው መከራ ቀርባለችና ጌቴሴማኒ ወደ ምትባለው የአትክልት ቦታ ገብቶ ወደ አባቱ ጸለየ እናንተም መከራ በመጣባችሁ ጊዜ አስቀድማችሁ ጸልዩ ለማለት አብነት ሲሆነን እንዲህ አደረገ፡፡ እዚህ ላይ ግን ጌታችን መጸለዩ የሚመጣበትን መከራ በመፍራት አይደለም፡፡ አስቀድሞ በዮሐንስ ወንጌል ‹‹ነፍሴን አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል እኔ በፈቃዱ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም›› /ዮሐ. 007-08// እንዳለ የሚሞተው በፈቃዱ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ከመሆኑ በፊት ሁሉን የሚያውቀው ክርስቶስ በዚያች ሌሊት ሊይዙት እንደሚመጡ ያውቅ ስለነበር ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ የአይሁድ ጭፍሮችም እርሱን ለመያዝ የደፈሩት ‹‹የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ›› በማለት ካደፋፈራቸው በኋላ ነበር፡፡

ማቴ. ፳6፥፴6-፵6        ማር. 04፥፴2-፵2     

 • ከደቀመዛሙርቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ጌታውን በመሳም ለአይሁድ አሳልፎ ሰጠ ጌታም ትእምርተ ፍቅሩን /የፍቅሩን ምልቱን/ ትእምርተ ጽብእ /የጠብ ምልክት/ አድርገኸው መጣኽን በማለት ተናገረው፡፡ ጭፍሮቹም የመላእክት አለቆች በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን ወደ ፊትና ወደ ኋላ እያንገላቱ ወሰዱት በዚያችም ሌሊት አንደበት ከሚገልጸው በላይ አሰቃይተውታል፡፡

ማቴ. ፳6፥፵7-፶6        ማር. 04፥፵3-፶   

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine