በዓለ ሆሣዕና

በስምንተኛው ሳምንት የሚከበር ሲሆን ከጌታ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ ሆሣዕና መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ይህም በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ በመቅደሱ ዙሪያ ያሉትን ለዋጮችና ሻጮችን ያስወጣበት' ቤተመቅደሱ የጸሎት ቤት መሆኑን ያወጀበትና ክብሩን የገለጸበት በዓል ነው፡፡ በዚህ ዕለት አቀባበል ያደረጉለት የሰው ልጆችም በቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ እንደተናገረው ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ አመስግነውታል፡፡ ማቴ. 21፥9 በጊዜው የነበሩ ፊሪሳውያን ይህን የእርሱን የአምላክነት ክብር ባለመቀበላቸው የሚቀርብለትን ምስጋና በመቃወማቸው ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ እራሱ ግን የሚገባው እንደሆነ አስረግጦ ነግሯቸዋል፡፡

Hosaena

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዓለ ሆሣዕና  የሚከበረው ከትንሣኤ በፊት ባለው እሑድ ነው፡፡ ሌሊቱን ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ ያድርና ጧት የቅዱስ ያሬድ መዝሙር እየተዘመረ በዐራቱም ማዕዘናት ዐራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ ከዚያም የዘንባባው ዝንጣፊ ተባርኮ ከቤተልሔም ተነሥቶ በካህናት ዝማሬ ታጅቦ ‹‹ይባዕ ንጉሠ ስብሐት ይባዕ አምላከ ምሕረት›› እየተባለ ወደ ቤተመቅደሱ ይገባና ለሕዝቡ ይታደላል፡፡ ምዕመኑም የመስቀል ምልክት በመሥራት በቤታቸው ይሰቅሉታል፤ በራሳቸውም እንደ አክሊል ይቀዳጁታል፤ አንዳንዶችም እንደ ቀለበት እየሠሩ በጣታቸው ያደደርጉታል፡፡ ዕለቱ የሰሙነ ሕማማት ዋዜማ ስለሆነና ሰሙነ ሕማማት የዓመተ ፍዳ' የአመተ ኩነኔ መታሰቢያ ሳምንት በመሆኑ ጸሎተ ቡራኬ' ጸሎተ ፍትሐትና ጸሎተ አስተሥርዮ ስለማይፈጸምበት በዚህ ዕለት ለሳምንቱ የሚገባው ሁሉ ይፈጸማል፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹የይፍቱኝ ዕለት›› እያሉ የሚጠሩት ብዙ ናቸው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች (በአክሱምና በእንጦጦ ማርያም) ደግሞ ምሳሌውን አጉልተው አህያ ላይ ሰው አስቀምጠው ሥርዓተ ዑደት ይፈጽማሉ፡፡

ምንጭ፡- በዓላት ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine