ገብርኄር

የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብርኄር ይባላል፡፡ ስለ ኄር /ስለታማኝ/ አገልጋይ ያስተማረውን የሚያዘክር ምስጋና ይቀርብበታል፡፡ ይኸውም ማቴ. 25፥14-30 ላይ ይገኛል፡፡

ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ፡፡ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ፡፡

ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት ›› አለ፡፡ ጌታውም ‹‹መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባርያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› አለው፡፡ ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍኩበት›› አለ፡፡ ጌታውም ‹‹መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታ ደስታህ ግባ›› አለው፡፡

አንድ መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤እነሆ፥ መክሊትህ እነሆ›› አለው፡፡ ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡- ‹‹አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁበትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፡፡ ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት›› አለ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡

መክሊት የተባለ ጸጋ ስጦታ ሲሆን እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የተለያየ ስጦታ ሰጥቶናል፡፡ በተሰጠንም ስጦታ ልናገለግልበት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪ መክሊት ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ የሰማናትን ቃለ እግዚአብሔር ለሌላው ማሰማት ይገባናል ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ማሰማቱ ብቻ ነው፡፡ በልቦናው አድሮ ሥራ የሚሠራ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ማቴ. 25፥14-30

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine