መፃጕዕ

የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት መፃጕዕ ይባላል፡፡ ጌታ ሕሙማን መፈወሱን ሙት ማስነሳቱን የሚያዘክር ምስጋና ይቀርብበታል፡፡ ማቴ. 8፥1-34 ፤ማር. 7፥24-37፤ ዮሐ. 5፥1-18 በመፃጕዕ የተሰየመው እርሱ ለእኛ ትምህርት ተግሳጽ እንዲሆነን አንጂ በዚህ ሳምንት የሚታሰበው በአጠቃላይ ሕሙማን መፈወሱ ሙት ማስነሳቱ ነው፡፡

በቤተክርስቲያን በሽተኞች በሦስት ስያሜ ይጠራሉ፡፡ የዕለት ሕመም ወይም ከአንድ ዓመት በላይ ሕመሙ የጸናበት መፃጕዕ ይባላል፡፡ ስለዚህ መፃጉዕ የተባለው ስለሕመሙ ጽናት እንጂ ስሙ አይደለም፡

 

በቤተ ሳይዳ ትርጉሙ /የምሕረት ቦታ/ በተባለች አንድ መጠመቂያ ነበር፡፡ በዚያም የውሃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞች ዕውሮች አንካሶች ሰውነታቸው የሰለሉ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠው የምሕረት ፈውስ ይዞ የእግዚአብሔር መልአክ ውሃውን ባርኮ ሲሄድ ቀድሞ የገባው በሽተኛ ይፈወስ ነበር፡፡ተስፋ ሳይቆርጥ ለ38 ዓመታት ድኅነትን እየጠበቀ በሕመሙም እየተሰቃየ በዚያ የተኛ አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ይህን ሁሉ ዓመት እንደተሰቃየ አውቆ ድኅነት ሊሰጠው ወዶ መጣ፡፡ ‹‹ልትድን ትወዳለህን›› ብሎ ጠየቀው፤ መጠየቁ ፍጹም የሰውን ሥጋ እንደተዋሐደ ሲያጠይቅ ነው፡፡ በተጨማሪም በዕለተ ዓርብ ራሱ አዳነኝ እንጂ መቼ አድነኝ አልኩት ብሎ ለመክሰስ ምክንያት እንዳያገኝ ጠየቀው ‹‹ጌታ ሆይ ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም›› አለው፡፡ የ30 ዓመት ጎልማሳ ነውና አንስቶ ይጨምረኝል ወይም አምስት ገበያ የሚያህል ሕዝብ ይከተለው ነበርና አዝኖልኝ ወደ መጠመቂያው ይጨምረኛል ብሎ ነው እንጂ እንዲሁ ይፈውሰኛል ብሎ አይደለም፡፡ ጌታ ግን ለመዳን መውደዱን ተመልክቶ ‹‹ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገኘው ፍጹም ድኅነት ነውና ወዲያው ሰውየው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሔደ፡፡ አልጋውንም ተሸክመህ ሒድ ያለው 38 ዓመት የተሸከመችው ጠንካራና የብረት አልጋ ስለነበረ ፍጹም መዳኑን እንዲያውቅ ነው፡፡ መፃጉዕ የተፈወሰው በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት ስለነበር በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር፡፡ በዕለተ ዓርብ የተደረገለትን ተዓምር ረስቶ ጌታን ከሰሰው በጥፊም መታው ወዲያው እጁ ሰለለ፡፡

በሽታ በተለያየ ምክንያት ይመጣል  

  • በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ በሽታ ዘኁ. 21፥4-9 እስራኤላውያን
  • የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ይገለጥ ዘንድ የሚመጣ በሽታ አለ ዮሐ. 9፥1-3
  • ሰዎች ከእግዚአብሔር ዋጋ እንዲያገኙበት ከዲያቢሎስ የሚመጣ ፈተና የሆነ በሽታም አለ እንደ ኢዮብ
  • ሰዎች በተሰጣቸው ጸጋ እንዳይታበዩ ለማሳወቂያ የሚሆን በሽታ አለ የቅዱስ ጳውሎስ ራስ ምታት
  • የበደለውን የሚቀስፍበት የሚቀጣበት ኃይል ፤ የመፃጕዕ እጅ የሰለለው
  • ያልታመመው እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን የታመመው ምሕረትን እንዲለምን የሚመጣ በሽታም አለ፡፡
ምንጭ፡- የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5 አንድምታ

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine