የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት ምኵራብ ይባላል፡፡ ‹‹ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ›› የሚልና ይህን የመሰለ ጌታ በምኵራብ ማስተማሩን የሚዘከርበት' የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ዘመን በኢየሩሳሌም አይሁድ ቤተመቅደስ ነበራቸው፡፡ ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ ግን ቤተመቅደሱን አፈረሰ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚኖሩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎት ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ በሚያስተምርበት ጊዜ ግን ብዙ ምኩራቦች ነበሩ ሐዋርያት በሚያስተምሩበት ወቅት ከአንዳንድ ቦታዎች በቀር በምኵራቦች ገብተው ወንጌልን አስተምረዋል፡፡
በብሉይ ዘመን ቢያንስ ዐሥር የጎለመሱ ወንዶች (የቤተሰብ ኃላፊዎች) በቦታው ከተገኙ እነዚህ ምኵራቦችን ለመሥራት ይፈቀድላቸው ነበር፡፡በምኵራብ ውስጥም የሕግ መጻሕፍትና በነቢያት የተጻፉ ጽሑፎች በብራና ጥቅልል ይገኛሉ፡፡ ምዕመኑ እንዲሰማቸው እንደመድረክ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ካህናትና መምህራን ቆመው መጻሕፍትንና ቃለ እግዚአብሔርን ያስተምሩ ነበር፡፡ምኵራብን የሚመሩት አለቆች ጥፋተኛ ሰው ሲገኝ በመግረፍ ወይም ከምኵራብ በማስወጣት ሊቀጡ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ አገልጋይ ወይም የሚራዱ ወጣቶችም ልጆችም በማስተማር ጥቅሎችን በማቅረብ ሌላውን የአለቆችን ትዕዛዝ በመፈጸም ያገለግላሉ፡፡
በሰንበት ሕዝብ ሁሉ በምኵራብ ተሰብስበው አምልኮታቸውን ይፈጽሙ ነበር በአምልኮታቸው ውስጥ ጸሎት፤ ከሕግና ከነቢያት ንባብ፤ ስብከትና ቡራኬ ነበር፡፡ በዚህ ምኵራብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል፡፡ ወደ አደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሳ ሉቃ. 4፥16 ወደ ገዛ አገሩም ወጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኵራባቸው ያስተምራቸው ነበር ማቴ. 13፥53 ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምራቸው ጀመር፡፡ ማር. 6፥1
ምንጭ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት