በዓለ ቅድስት ሥላሴ (ጥር 7) 2004

በዓለ ቅድስት ሥላሴ (ጥር 7)

በሰ//ቤቱ ትምህርት ክፍል

ሥላሴ የሚለው ሠለሰ ሦስት አደረገ ከሚለው የግእዝ ሥርወ ቃል የተገኘ ሲሆን ሦስት ሦስትነት ማለት ሲሆን በያዘው ምሥጢር ግን አንድም ሦስትም /አንድነት ሦስትነት/ ተብሎ ይተረጎማል፡፡ ሦስትነታቸው በስም በአካል በግብር፤ አንድነታቸው በባሕርይ በህልውና በመለኮት በሥልጣን በፈቃድ ነው፡፡

  

  

1.   የሥላሴ ሦስትነት

ሀ. የስም ሦስትነት ፡- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ‹‹እንግዲህ አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ . . .›› ማቴ. 28፥19

      ለ. የአካል ሦስትነት፡- ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ፣ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ አለው፡፡ (ሃይማኖተ አበው) አካል ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር ያለው ነው፡፡ ገጽ ማለት ደግሞ ፊት ነው፡፡ መልክም ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር ያለ ነው፡፡ አካልም እንዳላቸው ሲያጠይቅ ነቢዩ ዳዊት ‹‹የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮዎቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው፡፡›› መዝ. 33፥15 ‹‹እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም›› መዝ. 118፥73 ኢሳይያስም ‹‹እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፡- ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት ›› ብሏል ኢሳ. 66፥1 ለአብርሃም በመምሬ አድባር ዛፍ ስር ዘፍ.18፥1-4 ለዮሐንስ በዮርዳኖስ ተገልጸዋል ማቴ. 3፥16-17

      ሐ. የግብር ሦስትነት፡- የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ፣ የወልድ ግብሩ መወለድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው፡፡ አብ ቢወልድ ቢያሠርጽ እንጅ እንደ ወልድ አይወለድም እንደመንፈስ ቅዱስ አይሠርጽም፣ ወልድም ቢወለድ እንጂ እንደ አብ አይወልድም አያሠርጽም እንደ መንፈስ ቅዱስ አይሠርጽም፣ መንፈስ ቅዱስም ቢሠርጽ እንጅ እንደ አብ አይወልድም አያሠርጽም እንደ ወልድ አይወለድም፡፡ አብን ወላዲ አሥራጺ ወልድን ተወላዲ መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ስላልን የሚበላለጡ አይደሉም አንድ ናቸው፡፡ ጌታ አንድነታቸውን ሲያጠይቅ ‹‹እኔ እና አብ አንድ ነን›› ብሏል፡፡ ዮሐ. 10፥30  አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ‹‹ኢይልህቅ አብ እም ወልዱ ወልድኒ ኢይልህቅ እምመንፈስ ቅዱስ ወመንፈስ ቅዱስኒ ኢይንዕስ እምወልድ ወወልድኒ ኢይንዕስ እምአቡሁ›› ብሏል፡፡ ይህ ማለት ሦስት አምላክ ማለት አይደለም፡፡ አንድ አምላክ ይባላሉ አንጂ፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም‹‹ወመለኮትሰ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ›› ብሏል፡፡

 

ምሳሌም፡-  ፀሐይ ክበብ ሙቀት ብርሃን፤ እሳትም ነበልባል ፍሕም ሙቀት አላቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ፀሐይ አንድ እሳት ቢባሉ እንጅ ሦስት ፀሐይ ሦስት እሳት አይባሉም፡፡

     እንዲሁ ሥላሴም በአካል በግብር በስም ሦስት ቢባሉም ቅሉ አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም፡፡

2. የሥላሴ አንድነት

     ሥላሴ በባሕርይ በህልውና በመለኮት በሥልጣን በፈቃድ አንድ ናቸው፡፡

     የህልውና አንድነታቸው፡- በአብ ልቡናነት ወልድ መንፈስ ቅዱስም ያስባሉ፤ በወልድ ቃልነት አብ መንፈስ ቅዱስም ይናገራሉ፤ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት አብ ወልድም ህልዋን ሆነው ይተነፍሳሉ፡፡ ‹‹አሐዱ ህላዌሆሙ ለሥላሴ እንዘ ይሄልው በበአካላቲሆሙ ወዕሩያን እሙንቱ በህልውና አብኒ ልቦሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ፣ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ፣ ወመንፈስ ቅዱስ,ኒ እስትንፋሶሙ ለአብ ወለወልድ›› አንዲል ሃይማኖተ አበው

ቅድስት የሚል የሴት ቅጽል የተቀጸለላቸው ባሕርያቸው ታይቶ ነው፡፡

-   ልጅ ከእናቱ ባሕርይ እንዲገኝ ይህም ዓለም ከሥላሴ ባሕርይ ተገኝቷልና፤

-   እናት ለልጇ የሚያሻውን አስባ እንድታቀርብለት ሥላሴም ለፍጥረት ሁሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ አስቀድመው ያዘጋጁለታል ይሰጡታልም፡፡ ማቴ. 6፥32

-   አንድም እናት ልጇ ቢያስቀይማት ፈጽማ እንዳትጣላው ሥላሴም ሠርቀው አመንዝረው ቢበድሏቸው ንስሓ ገብተው ቀኖና ይዘው ቢለምኗቸው ይቅር ይላሉና፡፡ማቴ. 6፥14

     ሥላሴ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ካለመኖር ወደመኖር አምጥተው የፈጠሩ ሕማም ድካም የማይሰማቸው በሞት የማይለወጡ ገዥ ፈጣሪ ናቸው፡፡ ሥላሴ እንደዛሬ ሁሉ ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ባሕርያቸው ባሕርያቸውን ሲያመሰግን ይኖር ነበር ኋላ ግን ሰውና መላእክትን ስማቸውን ለመቀደስ ክብራቸውን ለመውረስ ፈጠሩ፡፡ ሌላውን ግን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ ፈጥረውታል፡፡

                       

     የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳም እና ሔዋን በገነት 7 ዓመት ከ1ወር ከ17 ቀን በገነት ኖረው በዕፀ በለስ ምክንያት ከገነት ወጥተው በምድረ ኤልዳ ተቀመጡ፡፡ ኩፋ. 5፥6 ሥላሴም ‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት›› ብለዋቸው ወልደው ተዋልደው በዙ፡፡ የእነሱ ዐሥረኛ ትውልድ ኖኅ ይባላል፡፡ በዘመኑ የሰው ልጆች ምድርን በኃጢአት አረከሷት፡፡ ሥላሴ ኖኅንና 7 ቤተሰቦቹን አስቀርተው ሌላውን የሰው ዘር በንፍር ውኃ አጠፉት፡፡ ዘፍ. 7 እና 8 ከዚህ በኋላ የኖኅ ልጆች ወልደው ተዋልደው ብዙዎች ሆኑ፡፡

     በባቢሎንም የነበሩ በሰናዖር ምድር ሰፊ ሜዳ አግኝተው ሳንሞት ስም ማስጠሪያ ግንብ እንገንባ ብለው መክረው ታላቅ ግንብ ገነቡ፡፡ አለቃቸው ናምሩድ ይባላል  እሱም ሞትን የሚያመጡብን ሥላሴ ናቸውና እነርሱን ወግተን ሞትን እናርቅ አላቸው፡፡ ከዚያ ጦር እየሰበቁ ይወረውሩ ጀመር ሰይጣንም ከደመና በምትሀት ደም እየቀባ ይልክላቸዋል፡፡  እነሱም ደሙን እያዩ አሁን አብን ወጋነው አሁን ወልድን ወጋነው ይሉ ጀመር፡፡ ሥላሴ ምንም እንኳ ምሕረታቸው የበዛ ቢሆኑም ዲያብሎስ ስለሠለጠነባቸው ‹‹ኑ እንውረድ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው›› ብለው ቋንቋቸውን ለያዩባቸው፡፡ ውኃ ሲለው ጭቃ ጭቃ ሲለው ደንጊያ የሚያቀብለው ሆነ እንዲህ የማይግባቡ ቢሆኑ ተበታትነዋል፡፡ ባለማስተዋል የሠሩትንም ሕንፃ ዓመጻ ነፋስ ጠራርጎ አጥፍቶታል፡፡ ዘፍ. 11፥1-9

     በዘመነ አብርሃምም የሰዶምና ገሞራ ሰዎች ወንድ ከወንድ እስከመጋባት ድረስ ኃጢአት ሠሩ እግዚአብሔርን በደሉ፡፡ የአብርሃም የወንድም ልጅ ሎጥ በዚያ ይኖር ነበር፡፡ ሊያድኑት ቢሹ ሁለቱን መላእክት ልከው እግዚአብሔር ሰዶምና ገሞራን አጠፋለሁ ብሏልና ሚስትህንና ልጆችህን ይዘህ ወደ ዞዓራ ሂድ ስትሄድም ወደ ኋላ ዙረህ አትመልከት አሉት፡፡ ማልዶ ተነሥቶ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ከከተማው ወጣ፡፡ ሰዶምና ገሞራ ባሕረ እሳት ሆኑ፡፡ የሎጥ ሚስት ወይኔ ሀገሬ ብላ መለስ ብትል የጨው ሐውልት ሁና ቀርታለች፡፡ ዘፍ. 19፥1-29

     ይህ የተደረገ በወርኃ የካቲት እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ፡፡ ፍሬ ነገሩ ግን ይህን ያደረጉ ሥላሴ እንደመሆናቸው በዚህ ዕለት ይዘከራል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine