ጥቅምት፡- 25 ዕረፍቱ ለአባ ቡላ (አቢብ )

        ቡላ ማለት ፍሬ ሃይማኖት ማለት ነው፡፡ አባታቸው አብርሃም እናታቸው ሐሪክ ልጅ አጥተው ሲያዝኑ በአንድ መልአክ የበሰለ ፍሬ ሲሰጣቸው አይተው ጸንሰዋቸዋልና፡፡ በተወለደም ጊዜ ከደጃቸውም ታላቅ ዛፍ በቅሎ  በቅጠሎቹም ላይ ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር የሚል ጽሑፍ በሮማይስጥ ቋንቋ ተጽፎ ተገኝቷል፡፡ ይህን እያደነቁ ዓመት ያህል ሳያስጠምቋቸው ቢቆዩ እመቤታችን ለሊቀ  ጳጳሳት ተገልጻ ከደጃቸው ይህን ምልክት ታገኛለህ ሕፃኑን ተቀብለህ አጥምቀው ስሙንም ቡላ በለው አለችው፡፡ ተቀብሎም አጥምቋቸዋል፡፡ ሲጠመቁም አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብለው አመስግነዋል፡፡ አባት እናታቸው ገና በልጅነታቸው ሞተዋል፡፡ በ10 ዓመታቸው ሃይማኖታቸውን ካዱ ለጣዖት ስገዱ የሚል ዐላዊ ንጉሥ ተነሣ፡፡ ሄደው ዘለፉት ሕፃን ነው ልራራለት ሳይል በችንካር አስቸንክሮ ገደላቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል በዘንጉ ነክቶ አስነሣቸው፡፡ ከሌላው ዐላዊ ሄደው መሰከሩ፡፡ በሰይፍ አስመትቷቸዋል፡፡ቅዱስ ሚካኤልም አንስቶ ከበረሃወስዶ ልብሰ ምንኩስና አልብሷቸው ቆብ ደፍቶላቸው ሄዷል፡፡  

        አባ ቡላ በእድሜ ትንሽ ቢሆኑም ቅሉ መንፈስ ቅዱስ ከኃጢአት ስላነጻቸው ለተጋድሎ ጽኑዕ አድረጓቸዋልና ከእድሜ ባለጸጋዎች በላይ በጾም በጸሎት ተወስነው በትምህርት ኗሪ ሆነዋል፡፡ ሥጋቸውን ለማድከም ሰውነታቸውን ሲገርፉ ፊታቸውን ሲነጩ ይኖሩ ነበር፡፡ የጌታም ሕማሙን ሞቱን እያሰቡ ከዛፍ ላይ ራሳቸውን ይወረውሩ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ጸንቶባቸው በደወቁበት ሞቱ፡፡ ጌታ 4 ባሕርያተ ሥጋ 3 ግብራተ ነፍስ አስማምቶ አስነስቶ እንግዲህ የብዙኃን አባት ትሆናለህና ስምህ አቢብ ይሁን ብሏቸዋል፡፡ አቢብ ማለት አቢብ ብዙኃን /የብዙዎች አባት/ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የጌታን ሕማሙን ሞቱን እያሰቡ 40 ዘመን እህል ውኃ ሳይጠጡ 12 ዓመት 6 ወር በራሳቸው ቆመው ሲያዝኑ ሲያለቅሱ ኖረዋል፡፡ በመጨረሻም ከዛፍ ወድቀው በጦር ተወግተው ዐርፈዋል፡፡ እመቤታችን መላእክትን አስከትላ መጥታ ‹‹ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ አቢብ›› አለቻቸው፡፡ በድናቸው ተነስቶ ሰላም ለኪ ኦ ንግሥተ ሰማያት ወምድር ብሎ እጅ ነስቷል፡፡ ጌታም ከሞት አስነስቶ በተስፋህ ያመነውን በቃል ኪዳንህ የተማጸነውን ሁሉ እሰከ 10 ትውለድ ድረስ እምርልሃለሁ ብሎ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ለይቶ በስሐበተ መላእክት በቃለ አቅርንት አሳርጓታል፡፡

የጻድቁ በረከት ቃል ኪዳን ተካፋዮች ያድርገን አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር  

በደሳለኝ አላምሬ ዘኆኅተ ብርሃን

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine