ጥቅምት፡- 25 ዕረፍቱ ለአባ ቡላ (አቢብ )

        ቡላ ማለት ፍሬ ሃይማኖት ማለት ነው፡፡ አባታቸው አብርሃም እናታቸው ሐሪክ ልጅ አጥተው ሲያዝኑ በአንድ መልአክ የበሰለ ፍሬ ሲሰጣቸው አይተው ጸንሰዋቸዋልና፡፡ በተወለደም ጊዜ ከደጃቸውም ታላቅ ዛፍ በቅሎ  በቅጠሎቹም ላይ ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር የሚል ጽሑፍ በሮማይስጥ ቋንቋ ተጽፎ ተገኝቷል፡፡ ይህን እያደነቁ ዓመት ያህል ሳያስጠምቋቸው ቢቆዩ እመቤታችን ለሊቀ  ጳጳሳት ተገልጻ ከደጃቸው ይህን ምልክት ታገኛለህ ሕፃኑን ተቀብለህ አጥምቀው ስሙንም ቡላ በለው አለችው፡፡ ተቀብሎም አጥምቋቸዋል፡፡ ሲጠመቁም አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብለው አመስግነዋል፡፡ አባት እናታቸው ገና በልጅነታቸው ሞተዋል፡፡ በ10 ዓመታቸው ሃይማኖታቸውን ካዱ ለጣዖት ስገዱ የሚል ዐላዊ ንጉሥ ተነሣ፡፡ ሄደው ዘለፉት ሕፃን ነው ልራራለት ሳይል በችንካር አስቸንክሮ ገደላቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል በዘንጉ ነክቶ አስነሣቸው፡፡ ከሌላው ዐላዊ ሄደው መሰከሩ፡፡ በሰይፍ አስመትቷቸዋል፡፡ቅዱስ ሚካኤልም አንስቶ ከበረሃወስዶ ልብሰ ምንኩስና አልብሷቸው ቆብ ደፍቶላቸው ሄዷል፡፡  

        አባ ቡላ በእድሜ ትንሽ ቢሆኑም ቅሉ መንፈስ ቅዱስ ከኃጢአት ስላነጻቸው ለተጋድሎ ጽኑዕ አድረጓቸዋልና ከእድሜ ባለጸጋዎች በላይ በጾም በጸሎት ተወስነው በትምህርት ኗሪ ሆነዋል፡፡ ሥጋቸውን ለማድከም ሰውነታቸውን ሲገርፉ ፊታቸውን ሲነጩ ይኖሩ ነበር፡፡ የጌታም ሕማሙን ሞቱን እያሰቡ ከዛፍ ላይ ራሳቸውን ይወረውሩ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ጸንቶባቸው በደወቁበት ሞቱ፡፡ ጌታ 4 ባሕርያተ ሥጋ 3 ግብራተ ነፍስ አስማምቶ አስነስቶ እንግዲህ የብዙኃን አባት ትሆናለህና ስምህ አቢብ ይሁን ብሏቸዋል፡፡ አቢብ ማለት አቢብ ብዙኃን /የብዙዎች አባት/ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የጌታን ሕማሙን ሞቱን እያሰቡ 40 ዘመን እህል ውኃ ሳይጠጡ 12 ዓመት 6 ወር በራሳቸው ቆመው ሲያዝኑ ሲያለቅሱ ኖረዋል፡፡ በመጨረሻም ከዛፍ ወድቀው በጦር ተወግተው ዐርፈዋል፡፡ እመቤታችን መላእክትን አስከትላ መጥታ ‹‹ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ አቢብ›› አለቻቸው፡፡ በድናቸው ተነስቶ ሰላም ለኪ ኦ ንግሥተ ሰማያት ወምድር ብሎ እጅ ነስቷል፡፡ ጌታም ከሞት አስነስቶ በተስፋህ ያመነውን በቃል ኪዳንህ የተማጸነውን ሁሉ እሰከ 10 ትውለድ ድረስ እምርልሃለሁ ብሎ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ለይቶ በስሐበተ መላእክት በቃለ አቅርንት አሳርጓታል፡፡

የጻድቁ በረከት ቃል ኪዳን ተካፋዮች ያድርገን አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር  

በደሳለኝ አላምሬ ዘኆኅተ ብርሃን

 

ጥቅምት 12፡- በዓሉ ለቅዱስ ሚካኤል

ዘተፈነወ ኀበ ሳሙኤል ነቢይ 

ጌታ ሳኦልን አማሌቅን ምታ ያላቸውንም ሁሉ አጥፋ አለው፡፡ ምን በድለዋል? ቢሉ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ እየሸመቁ አውከዋቸው ነበርና በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሳኦል ግን ያልታዘዘውን ፈጽሞተመለሰ፤

ጌታ ሳሙኤልን‹‹ነሣዕኩ ዘአንገሥክዎ ለሳኦል - ሳኦልን ስላነገስኩት ተጸጸትኩ ›› አለው ሳሙኤልም ሳኦልን ቢገስጸውም ቅሉ ቀብቶ ያነገሰ አሱ ነውና ሲያዝንለት ሲያለቅስለት ኖሯል፡፡ ኋላ ግን መልዕቀርኒ ቅብዕ ወሑር ውስተ ቤተ ዕሴይ አራቱን ሽቱ አምስተኛ ዘይቱን አጣፍጠህ ቤተልሔም ወርደህ ከዕሴይ ልጆች የመረጥኩትን ቀባ አለው፡፡ ሁለት ላም አስነድቶ መስዋዕት እሰዋለሁ ብሎ ሄደ ነቢየ እግዚአብሔር አመጣጥህ በደህና ነውን? አሉት፡፡ መስዋዕት ልሰዋ ነው ተለዩልኝ ብሎ ዕሴይን ከሚሰዋበት ወስዶ ከልጆችህ የምቀባው አለኝና ልጆችህን አቅርብልኝ አለው፡፡ በኩሩ ኤልያብ ነው፡፡ ይዞት መጣ መልከ ቀና ነበርና ነዋ መሲሑ ለእግዚአብሔር ብሎ ሊቀባው ተነሳ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ‹‹ሰብእሰ ገጸ ይሬኢ ወእግዚአብሔር ልበ ይሬኢ›› ሰው መልክ ያያል ጌታ ግን ልብን ያያልና የመልኩን ማማር አትይ አለው፡፡

         እግዚአብሔር አልመረጠውም ብሎ መለሰው፡፡ ሁለተኛው አሚናዳብ መጣ ይህንም እግዚአብሔር አልመረጠውም ብሎ መለሰው፡፡ ከእርሱም በኋላ 5 ቱን ሁሉ መለሳቸው፡፡ በመጨረሻ ዳዊት ከበግ ጥበቃ ተጠርቶ ማጣ፡፡ ቅብዓ መንግስቱ ፈላ ፡፡ ነዋ መሲሑ ለእግዚአብሔር ብሎ በወንድሞቹ መካከል አቁሞ ቀብቶታል፡፡ 1ሳሙ. 16፥1-13

      ወመጽአ መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕለ ዳዊት ይላል ከዚህም ጋር ሰባት ሀብታት ተሰጥተውታል ምን ምን ናቸው? ቢሉ

1.  ሀብተ ኃይል - አንበሳ ጅብ በጡንቻ መቶ መግደል ነው 1ሳሙ. 17፥34

2.  ሀብተ መዊዕ - በጦር በጋሻ የተመካ ጎልያድ በጠጠር ማሸነፍ ነው 1ሳሙ. 18

3.  ሀብተ በገና - በገና መደርደር ነው፡፡ 1ሳሙ.16

4.  ሀብተ ፈውስ - ሳኦል መንፈሰ ሰይጣን አድሮበት ነበርና ሲጸናበት በገና እየደረደረለት ይፈወስ ነበር፡፡ 1ሳሙ. 16፥23

5.  ሀብተ መንግስት - እስራኤልን አንድ አድርጎ መግዛት ነው፡፡

6.  ሀብተ ክህነት - በስብሐተ ካህናት ጌታን ማመስገን ነው፡፡

7.  ሀብተ ትንቢት - ናሁ ሰማዕናሁ

በኤፍራታ መዝ. 131፥6 ብሎ ልደቱን

በመዝ. 113 ደግሞ ጥምቀቱን

‹‹ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ ›› መዝ. 21፥16 ብሎ ስቅላቱን

ወተንሥአ እግዚአብሔር መዝ. 77 ብሎ ትንሣኤውን አስቀድሞ መናገር ነው፡፡ እኚህም ሀብታት በዳዊት አድርጎ ከርሱ ለተነሱ  ላሉና ለሚነሱ ንጹሐን ካህናት የተሰጡ ናቸው፡፡

በዚህ ዕለት(ጥቅምት 12) ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ለነቢዩ ሳሙኤል ያደረገውን ተራድኦ እናስባለን፤፤ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልና ምልጃና ጸሎቱ፤ የነቢዩ ሳሙኤልና የልበ አምላክ ዳዊትም በረከታቸው፤ ከኛ ጋር ይሁን፤፤

ለ. ዕረፍቱ ለማቴዎስ ሐዋርያ (60 ዓ.ም ዕረፍቱ)

      ማቴዎስ ማለት ኅሩይ ማለት ነው፡፡ ከቀራጭነት ጌታ ሐዋርያ አድርጎ የመረጠው ነው፡፡ ማቴ. 9፡9 ቀዳሚ ስሙ ሌዊ ነበር፡፡ 2፡14 ትውልዱ ከነገደአሴር ሲሆን አባቱ ዲቁ እናቱ ከሩትያስ ይባላሉ፡፡ ብሔረ ውላዱ ናዝሬት ነው፡፡

ሀገረ ስብከቱ ፍልስጥኤም ናት ሲሄድ ከከተማው በር ሲደርስ ሪዙን ቆርጦ ፀጉሩን ተላጭቶ ካህናተ ጣዖቱ የሚለብሱትን ዓይነት ልብስ ለብሶ በእጁ ዘንባባ ይዞ ከቤተ ጣዖት ገባ፡፡

    ካህነ ጣዖቱ አርሚስ ይባላል፡፡ አርሚስ ተቀምጦ ሳለ ሄዶ ‘‘አንተ ወንድሜ ይህ ጣዖት ባየው ባየው አፍ እያለው አይናገርም ጆሮ እያለው አይሰማም እጅ ሳለው አይዳስስም እግር እያለው አይራመድም ለምን ይሆን?’’ አለው፡፡ ወዲያው ዓምደ ብርሃን ተተከለ ሰማያዊ ማዕድ ተሠራ፤ ሁኔታውን የተመለከትው አርሚስም ‘’አምላክ እንጂ እንዲህ ገባሬ ተአምር’’ ብሎ ‘’መኑ ውእቱ ስሙ ለአምላክከ የአምላክህ ስም ማነው?›› አለው፡፡ ሐዋርያው ማቴዎስም ‘’ኢየሱስ ክርስቶስ ውእቱ ስሙ ለአምላኪየ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው’’ አለው፡፡ በዚህ ጊዜ አርሚስ በመሻቱ አስተምሮት ከነ ቤተሰቡ አምኖ ተጠምቋል፡፡

       ከዚህ በኋላ የንጉሡ ልጅ ሞተበት፡፡ ‘’ሄዶ ባደርግልሀ ታምናለህ’’ አለው ንጉሡም ‘’አዎን’’ አለ ፡፡ ማቴዎስም ጸልዮ አድኖለታል፡፡ ንጉሡም አምኖ ተጠምቋል፡፡ ሕዝቡም ይህን አይተው አምነው ተጠምቀዋል፡፡

   ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ በአገልግሎት ዘመኑ ብዙ ተአምራትን የፈጸመ በመሆኑ ይህችን ለአብነት ያህል አነሳን እንጂ ገድሉ ሰፊ ነው፤፤

  ይህች እለትም (ጥቅምት 12) ያረፈባት በመሆኑዋ ከሐዋርያው በረከት ያሳትፈን ዘንድ ልናስባት ይገባል፤፤የሐዋርያው የቅዱስ ማቴዎስ ምልጃና ጸሎቱ ከኛ ጋር ይሁን፤፤

 

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine