ጾመ ነነዌ

 

                      በየመንዝወርቅ ኪዳኔ ዘኆኅተ ብርሃን

 ጾመ ነነዌ

ጾም ማለት ከቃሉ ብንጀምር ከሥጋ ፈቃድ መከልከል መወሰን በደልን አስቦ ሥጋን አድክሞ ነፍስን ማዳን ማለት ነው፡፡ በጾም የሚገኘውን በረከት የሚያውቀው ክርስቲያን ብቻ ነው፡፡ አዳም አምላኩ ካዘዘው ቃል ወጥቶ ከአምላኩ እቅፍ ከወጣ በኋላ ወደ አምላኩ የተመለሰው በጾም እና በጸሎት ነው፡፡ በደሉን አውቆ የሚፀፀት፣  ንሰሐ የሚገባ እና የአምላኩን ትዕዛዝ የሚፈጽም ሰው ዘወትር ከአምላኩ ጋር ነው፡፡

 እኛም በክርስቶስ አምላክነት እና በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ ለሚያምኑ ክርስቲያኖች በሙሉ እንኳን ለዚች ለተቀደሰች ጾም በሰላም አደረሳችሁ እያልን ይኸችን ጾም የነነዌ ሰዎችን በዮናስ አማካኝነት በሦስት ቀን ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት አማካኝነት የዳኑበት ሲሆን፣ የሰው ልጅም ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ከተጸጸተ እግዚአብሔር መልስ እንደሚሰጥ የተረዳንበት ጾም ናት፡፡ ይህች ጾም የሦስት ቀን ብትሆንም   ብዙ በረከት እና ረድኤት የምናገኝባት ጾም ነች፡፡ በዚህም ጾም የነነዌ ሰዎች ከትልቅ እስከ ትንሹ ንጉሡንም ጨምሮ ልባቸውን ሰብረውና ተጸጽተው አምላክ ምሕረትን ይሰጣቸው ዘንድ ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው የጸለዩበት ጊዜ ነው፡፡ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርም ከልብ መጸጸታቸውን አይቶ ከቁጣው ተመልሶ ሊመጣባቸው ከነበረው ጥፋት ድነዋል፡፡ እኛም ክርስቲያኖች ይህን በማዘከር ንስሐ ብንገባ እንደ ነነዌ ሰዎች ከተቃጣው ማንኛውም መቅሰፋት እንድናለን፡፡ በማለት በየዓመቱ ከዓብይ ጾም መግቢያ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ ካለው ከዕለተ ሰኞ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ “ጾመ ነነዌ” በማለት እንጾማለን፡፡

 እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ የሚመጣብንን መቅሰፍት የሚያይ አምላክ ከሚመጣብን መከራና መቅሰፍት ሁሉ ይጠብቀን እመ ብርሃን ቅድስት ድንግል እናታችን በምልጃዋ አትለየን፡፡ አሜን!!!

 

 

ነቢየ እግዚአብሔር ዮናስ

 ዮናስ ማለት የዋህ ርግብ ማለት ነው፡፡ ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ነው፡፡ የተወለደው በሰራፕታ ነው፡፡ በዘመኑ የነበረ ነቢይ ኤልያስ ነው፡፡ ይህም ነቢይ  በዘመኑ ንጉሥ አክአብ ንግሥቲቱ ኤልዛቤል 850 ነቢያተ ሐሰት ካህናተ ጣዖት አቁመው ጣዖት ሲያመልኩ ተው ቢሏቸው አልመለስም ቢሉ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ሰማይ ዝናም እንዳይዘንም አድርጓል፡፡ 1ነገ.18፥1-46፤ ያዕ. 5፥17

ከዚህ በኋላ ምግቡን ያመላልሱለት የነበሩ ቁራዎች ቀርተውበት ውኃውም ደርቆበት ወደ ጌታ ቢያመለክት ‹‹ወደ ሰራፕታ ሂድ በዚያም አንዲት መበለት ሴት ትመግብሃለች›› ብሎት ሰራፕታ የዮናስን እናት አግኝቷት ‹‹ውኃ አጠጪኝ ጥቂት ቁራሽም አምጪልኝ›› አላት፡፡ ‹‹ሕያው እግዚአብሔርን እፍኝ ዱቄት አለችኝ ጋግሬያት አንተም እኔም ልጄም (ዮናስ) በልተናት እንሞታለን›› አለችው፡፡ ኤልያስም የረሀቡ ዘመን እስኪያልፍ ይበርክት አላት፡፡ ብትገባ ዱቄቱ በማድጋው ዘይቱ በማሰሮው መልቶ አገኘች፡፡

ልጅዋ ዮናስም ታሞባት በሞተ ጊዜ ሄዳ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስን ሳይገባኝ ከቤቴ ገብተህ ኃጢአቴን ተመራምረህ ልጄን ትገድልብኝ አለችው፡፡ እጁን ከእጁ እግሩን ከእግሩ ገጥሞ እየወደቀ እየተነሣ ቢጸልይ በሰባተኛው ተነሥቷል፡፡ 1ነገ. 17፥1-24

 

Read more: ነቢየ እግዚአብሔር ዮናስ

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine