ኅዳር 21 ፡- ታቦተ ጽዮን

እስራኤል በግብጽ ባርነት ሲኖሩ ጌታ ግብጻውያንን በዘጠኝ መቅሰፍት አሥረኛ ሞተ.በኵር በአሥራ አንደኛ ስጥመት አጥፍቶ ጸልየው እንዲድኑባት ሰውተው እንዲከብሩባት ታቦተ .ጽዮንን ሰጥቶ 40 ዘመን መና ከደመና እያወረደ ውኃ ከጭንጫ እያፈለቀ በሠናይ መግቦ ምድረ.ርስት አግብቷቸዋል ነህ 9 ፡21 ሐዋ 13፡18 ከዚህም በኋላ መስፍን ሲሞት መስፍን ካህን ሲሞት ካህን እየተተካ ሥርዓቱ ሳይጓደል ከዔሊ ደረሰ፡፡ ዔሊም ክህነት ከመስፍንነት አስተባብሮ ይዞ 40 ዘመን አስተዳድሮ ቢደክም አፍኒን ፊንሐስ የሚባሉ ልጆቹን ከበታቹ ሾማቸው፡፡ ይልቁንም ጌታን የሚያስቆጣ ሦስት ዐበይት ኃጣውእ ሠርተዋል፡፡ ሙሴ አሮን በሠሩት ሥርዓት በቀዳማይ ሰዓተ.ሌሊት በርቶ በቀዳማይ ሰዓተ.መዓልት ይጠፋ የነበረውን ፋና ከባዶ ቤት ሲበራ ቢያድር ምን ይረባል ብለው አስቀርተውታል፤ እስራኤል መስዋዕት በሚሰዉ ጊዜ ገና ስቡ ሳይጤስ የወደዱትን ሥጋ ነጥቀው ይበሉ ነበር፤ ሴቶችን ያስነውሩ ነበር፡፡

 

      አባታቸው ዔሊ ይህንን ሰምቶ /ደቂቅየ አኮ ሠናይ ዘእሰምዕብክሙ/ ልጆቼ ስለ እናንተ የምሰማው ደግ አይደለም፤ ሰው ሰውን ቢበድል በእግዚአብሔር ይታረቁታል ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል ግን በማን ያስታርቁታል ተው አይሆንም አላቸው፡፡ ዳሩ ግን ከጌታ ይልቅ ለልጆቹ አድልቶ ልሻራቸው ላዋርዳቸው ሳይል ቀረ፡፡

      ታቦተ .ጽዮንን እያገለገለ የሚኖር ሳሙኤል በዚያች ሌሊት ተኝቶ ሳለ ጌታ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው፡፡ ዔሊ የጠራው መስሎት እነሆኝ የጠራኸኝ አለ፡፡ አልጠራሁህም ሄደህ ተኛ አለው፡፡ ሁለተኛ ጠራው ከዔሊ ቀረበ፡፡ ዔሊ ይህ ብላቶና ራእይ ተገልጾለት ይሆናል ብሎ እንግዲህ ቢጠራህ ተነስተህ ታጥቀህ እጅ ነሥተህ ቁምና ጌታዬ እኔ ባርያህ እሰማለሁ በል አለው፡፡ ሦስተኛ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው፡፡ ተነሥቶ ታጥቆ እጅ ነሥቶ ቆመና ባርያህ እሰማለሁለና ተናገር አለ፡፡  ልጆቹን ከመበደል አልከለከላቸውምና እንድፈርድበት የነገሩሁትን በዔሊ እፈጽምበታለሁ ብሎ የእስራኤልን መመታት፣ የታቦተ.ጽዮንን መማረክ፣ የአፍኒን ፊንሐስን የዔሊን ሞት ነገረው ሲነጋ ዔሊ እግዚአብሔር የነገረህን አንዳችም ሳታስቀር ንገረኝ አለው፡፡ ነገረው፡፡ እግዚአብሔር የወደደውን ያድርግ አለ፡፡

      ከዚህ በኋላ ጌታ የማያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀርምና እስራኤል በኢሎፍላውያን ዘምተው በአንድ ጊዜ 4ሺህ ሰው አለቀባቸው፡፡ ይህ ነገር የሆነብን ታቦተ.ጽዮንን ስላልያዝን ነውና ታቦተ ጽዮንን ላክልን ብለው ወደ ዔሊ ላኩ፡፡ አፍኒን ፊንሐስ ታቦተ.ጽዮንን ይዘው ሄዱ፡፡ በእስራኤል ጦር ሰፈር ታላቅ ደስታ ተደረገ፣ እልልታው ደመቀ፡፡ ኢሎፍላውያን ድል ያደረግን እኛ ነን እነሱ ምን አግኝተው ይደሰታሉ? አሉ፡፡  በታቦተ.ጽዮን ምክንያት መሆኑን ሲያውቁ በግብጻውያን የሆነውን ሰምተዋልና ወዮልን ወዮልን አሉ፡፡ ኋላ ግን  ተጽናንተው ገጠሙ፡፡ እስራኤል ተመቱ፣ አፍኒን ፊንሐንስ ሞቱ፤ ታቦተ.ጽዮንም ተማረከች፡፡

      አንድ ብንያማዊ ልብሱን ቀዶ አመድ ነስንሶ ወደ ከተማ ተመለሰ፡፡ የኀዘን ምልክት ነው፡፡ ከዚያ ያሉት ከተማዋን በለቅሶ በዋይታ አናወጿት፡፡ በዚህ ጊዜ ዔሊ የዘጠና ዓመት ሽማግሌ ነበር፡፡ በደብተራ ኦሪት በመንበሩ ተቀምጦ የታቦተ.ጽዮንን ነገር ያወጣ ያወርድ ነበረ፤ ያ ብንያማዊ ከርሱ ዘንድ ሄደ፡፡ ማን ነህ ከወዴትስ መጥተሃል? አለው፡፡ ትላንትና ከሰልፍ ያመለጥሁ ነኝ አለው፡፡ እስኪ በል ንገረኝ እንዴት ሆነ?  አለው፡፡  እስራኤል ተመቱ አፍኒን ፊንሐስ ሞቱ ታቦተ.ጽዮንም ተማረከች አለው፡፡ ከወንበሩ ወድቆ የጎድኑ አጥንቱ ታጥፎ ሆዱን ወግቶት ሞቷል፡፡ 1ሳሙ 4፡9-17

      ፍልስጥዔማውያንም ታቦተ.ጽዮንን አዛጦን ወስደው በቤተ.ጣዖታቸው ከዳጎን ጋር አስቀመጧት፡፡ በማግሥቱ ሊያጥኑለት ሊሰውለት ቢገቡ ዳጎን በ ታቦተ.ጽዮን ፊት በግንባቱ ወድቆ አገኙት፡፡ ከቦታው መልሰውት ሄዱ፡፡ በሌላው ቀን ሲመለሱ እጅ እግሩ ቶራርጦ ደረቱ ለብቻው ቀርቶ አገኙ፡፡ ሰዎቹም በእባጭ ተመቱ ፡፡ መቅሠፍቱ ቢጸናባቸው ወደጌት ወሰዷት፡፡ የጌት ሰዎችም እንዲሁ በመቅሠፍት ተመቱ፡፡ ወደ አስቀሎና ቢወስዷት ልታስፈጁን ነውን መልሱልን አሏቸው፡፡ ከሰባት ወር በኋላ ወደ ሀገሯ ትመለስ ብለው ቀንበር ባልተጫነባቸው በሚያጠቡ ላሞች በሚሳብ አዲስ ጋሪ አድርገው የበደል መስዋዕት እንዲሆን በአምስቱ ከተሞቻቸው አምሳል አምስት የወርቅ አይጦች አድርገው ሰደዷት፡፡ ላሞቹ ወደ ግራ ወደ ቀኝ ሳይሉ ከኢያሱ እርሻ ደርሰው ቆመዋል፡፡  ታቦተ.ጽዮንን ከሐውልተ. ስምዕ አኑረው ሠረገላውን ፈልጠው ላሞቹን አርደው አወራርደው መስዋዕት አቀረቡ፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ታቦተ.ጽዮን በድፍረት በማየታቸው ከመካከላቸው 5ሺህ ያህሉ ተቀሰፉ ፈርተው ታቦተ.ጽዮንን መጥታለችና ውሰዱ ብለው ወደ ቂርያትይ ዓርም ላኩ፡፡ ወስደው በአሚናዳብ ቤት አድርገዋት ልጁ አልዓዛር 20 ዓመት አገልግሏታል፡፡ 1ሳሙ .7/2

                                          ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

                                 ምንጭ፡- መዝገበ ታሪክ /ከመምህር ኅሩይ ኤርምያስ/

 

                                     ክፍል 1 ገጽ - 74

 

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine