ኅዳር 12 በዓሉ ለቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት

በዚህ ዕለት የሚከበረው እስራኤልን ከምድረ ግብፅ እየመራ ማውጣቱን በማዘከር ነው፡፡ ይህስ እንደምን ነው? ቢሉ አብርሃም ይስሐቅን ይወልዳል፣ ይስሐቅ ያዕቆብን ይወልዳል፣ ያዕቆብ ይሁዳንና ዐሥራ አንድ ወንድሞቹን ወልዷል፡፡  ዐሥራ አንደኛው ዮሴፍ ነው፡፡ ወንድሞቹ ጠልተው ተመቅኝተው ለእስራኤላውያን በ20ብር ሸጡት እነዚህም ግብፅ ወስደው ለፈርዖን ቢትወደድ ለጲጥፋራ በ30 ብር ሸጡት 10 ዓመት በአገልግሎት 10 ዓመት በግዞት ቆይቷል፡፡ መተርጉመ ሕልም ነበር፡፡ ፈርኦን የሕልሙ ትርጓሜው ጠፍቶት ሳለ ዝናውን ከጠጅ ቤቱ ሰምቶ ከግዞት አስጠርቶ ተርጉምልኝ አለው፡፡ ተርጉሞለት አፈ ንጉሥ አደርጎ ሾሞታል፡፡

ከሰባት ዓመት በኋላ በምድር ላይ ጽኑ ረሃብ ሆነ፡፡ ወንድሞቹ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ መጡ፡፡ መጀመሪያ አልነገራቸውም በሁለተኛው  . . . እኔ ዮሴፍ ወንድማችሁ ነኝ  ሔዳችሁ አባቴን አምጡልኝ አላቸው፡፡ ያዕቆብ አውሬ በላው ብለውት ሲያዝን ይኖር ነበርና ልጅህ በብሔረ  ባዕድ ከብሮ ይኖራል ሲሉት ከሞት እንደተነሳ ቆጥሮት ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን አስከትሎ በምድረ ጌሴም ተቀምጧል፡፡

ከብዙ ዘመናት በኋላ የዮሴፍን ዝና ያልሰማ ፈርኦን ነገሠ እስራኤል ከእኛ ይልቅ በዝተዋል ጠላት ቢነሳብን ተደርበው ያጠፉናል ብሎ አገዛዝ አጸናባቸው ፍርድ እንዳለባቸው እስራኤል መከራ እየተቀበሉ ሲሰቃዩ ኖሩ፡፡ የቆዮት 430 ዘመን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ምክንያት ይዞ ያድናቸዋል፡፡ ራሔል የምትባል ደርበሽ እርገጪ ተብላ ጭቃ ስትረግጥ ምጥ ይዟት ጥቂት ልረፍ አለች፡፡ ግብፃዊው ርገጭ ብሎ አስገደዳት፡፡ ሁለት ሕፃናት ከእግሯ ሥር ወደቁ፡፡ የልጅ ደም ግንብ ያጠነክራል ብሎ ከጭቃው ጋር አስረገጣቸው፡፡ መብትና አቅም ቢኖራት ያንጊዜ እሱንም ከጭቃው በቀላቀለችው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ራሷን ይዛ ታለቅስ ጀመር፡፡ ዕንባዋንም ወደ ሰማይ ዘራችው ፡፡ የእስራኤልን ዕንባ ሁሉ ይዛ ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰች፡፡

 

 ጌታም ለሙሴ ‹‹የሕዝቤን መከራ አይቼ ለቅሶአቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድኩ አሁንም ና ወደ ግብፅ ልላክህ ሕዝቤ እስራኤልን ልቀቅ በለው››አለው፡፡ ሙሴም ጌታዬ አኔማ ዲዳ ነኝ አከናውኖ የሚናገርልህን ላክ እንጂ አለ፡፡ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው እሱ ይንገርልህ አለው፡፡ ያስ ይሁን ማን ላከኝ ልበል? ምንስ ምልክት ላሳየው? አለ፡፡ ኤልሻዳይ ላከኝ በለው፡፡ ምልክቱንም በትርህን ከምድር ጣለው አለው፡፡ ቢጥላት እባብ ሆነች ፈርቶ ሲሸሽ ዥራቷን ይዘህ አንሳት አለው ቢያነሳት እንደ ቀድሞው ሆነች፡፡  ዳግመኛ እጅህን ከብብትህ አግባ አለው፡፡ አግብቶ ቢያወጣው ለምጽ ሆነ ሁለተኛ አግብቶ ቢያወጣው ደኅና ሆነ ይህን አድርገህ አሳየው አለው፡፡

ከምድያም ተነሥቶ ሲሄድ አሮንን ከሴኬም ሲወጣ አገኘው ተያይዘው ገቡ፡፡ ሙሴ ኤልሻዳይ እግዚአብሔር ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤ እስራኤልን ልቀቅ ብሎሃል አለው ፈርኦንን፡፡ ምን ምልክት አለህ? አለው፡፡ በትሩን ከምድር ጣላት እባብም ሆነች ዥራቷን ይዞ ቢያነሳት ደኅና ሆነች፡፡ ዳግመኛ እጁን ከብብቱ አግብቶ ቢያወጣው ለምጽ ሆነ ሁለተኛ አግብቶ ቢያወጣው ደኅና ሆነ፡፡ ይህንንማ የእኔም ጠቢባን ያደርጉታል ብሎ ኢያኔስና ኢያንበሬስን አስጠራ፡፡ በትሮቻቸውን ጣሉ እባብ ሆኑ ቢያነሷቸው ደኅና የማይሆኑ ሆነ፡፡ እጃቸውን ከብብታቸው አግብተው ቢያወጡ ለምጽ ሆነ ሁለተኛ አግብተው ቢያወጡ ለምጹ የማይጠፋ ሆነ፡፡ ሙሴም በትሩን ጣለ እባብ ሁና የነዚያን በትር ውጣ ልትነድፋቸው ቢሆን ፈርተው ሸሽተዋል፡፡ ፈርዖንም ለጊዜው ፈርቶ እለቃለሁ አለ፡፡ ኋላ ግን እግዚአብሔርን አላውቅም እስራኤልንም አልለቅም አለ፡፡ ከዚህ በኋላ በዘጠኝ መቅሰፍት በዐሥረኛ ሞተ በኵር ግብፃውያንን መታቸው፡፡

መማክርቱ ገብተው ንጉሥ አንተ በኵር ሚስትህ በኵር ልጅህ በኵር እናንተ ከሞታችሁ መንግሥት ለማን ሊሆን ነው? ልቀቃቸው ይሂዱ አሉት፡፡ እነ ሙሴን አስጠርቶ ልጆቻችሁን ከብቶቻችሁን ትታችሁ ሂዱ አላቸው፡፡ ልጆቻችን ቢቀሩማ ሥርዓትን ከማን ይማራሉ ከብቶቻችንንም ሠዉ የሚለንን አናውቀውም በዚያውም ላይ ንጹሕ ልብስ ለብሳችሁ ሠዉ ይለናል እንዴት እናድርግ? አሉት፡፡ ከጌቶቻችሁ ከእመቤቶቻችሁ ተዋሱ ብሎ አዋጅ ነገረላቸው፡፡ ወንድ ከጌታው ሴቲቱም ከእመቤቷ ልብስ ቀለበት (ወርቅ) ተውሰው ልጆቻቸውን ይዘው ከብቶቻቸውን ነድተው ወጡ፡፡

በሦስተኛው ቀን ፈርዖን ከሰገነቱ ሆኖ ከተማው ጭር ብሎ አይቶ የሦስት ቀን ጎዳና ሄደን ሰግደን ሠውተን እንመለሳለን ብለውት ነበርና ወይኔ ከገንዘቤ ወይ ከባሮቼ ሳልሆን ቀረሁ ብሎ ተቆጭቶ በፈረስ በሠረገላ ሆኖ ሠራዊቱን አስከትሎ በሦስት ቀን የሄዱት በአንድ ቀን ተጉዞ ደረሰባቸው፡፡ እስራኤል ባሕረ ኤርትራ ተከፍሎላቸው ተሻገሩ፡፡ ፈርዖን እሻገራለው ብሎ ገባ፡፡ እስራኤል ወዮ አሉ፡፡ ሙሴ ወደ ጌታ ቢያመለክት በበትርህ ባሕሩን ምታው አለው፡፡ ባሕሩን በበትሩ ቢመታው እንደ ግድግዳ ጸንቶ የነበረው ውሃ ተንዶ ፈርዖንን ከነሠራዊቱ አስጥሞታል፡፡ ወዲያውም ሙሴና አሮን የወንድ እኅታቸው ማርያም የሴት አቀንቃኝ ሆነው ማርያም ከበሮ እየመታች ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ እያሉ አመስግነዋል፡፡

      ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል እየመራቸው እየረዳቸው 1መቃ.13÷21 መና ከደመና እያወረደላቸው ውሃ ከጭንጫ እያፈለቀላቸው ያን እየተመገቡ አርባ ዘመን ተጉዘው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ ሲገቡም በሰባት ደመናት ተከልለው አንዱ ዋዕየ ፀሐይ እንዳይሰማቸው ከላይ አንዱ ቁረ ምድር እንዳይሰማቸው ከታች አራቱ ጠላት እንዳይጣላቸው ከግራ ከቀኝ ከፊት ከኋላ እየሆኑላቸው፣ አንዱ የሁለት የሦስት ቀን ጎዳና አልፎ እየሄደ መንገድ ሲጠርግላቸው ውሎ ሲመሽ እንደ አምደ ብርሃን ሆኖ በደብተራ ኦሪት ሲያበራላቸው እያደር እንዲህ ብለው ገብተዋል፡፡ ዘኁ. 9÷15

 ምንጭ፡- መዝገበ ታሪክ ክፍል 1

/ከመምህር ኅሩይ ኤርምያስ/

 

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine