ኅዳር 7፡ በዓሉ ለቅዱስ ጊዮርጊስ

በዚህ ዕለት በዓል መሠራቱ ሰለ ሁለት ነገር ነው፡፡ መጀመሪያ በሕይወተ ሥጋ ሳለ ንጉሡ ዱድያኖስ በርሀብ ይሙት ብሎ የምትልሰው የምትቀምሰው ከሌላት መበለት ቤት አስገብቶ ከምሰሶው ቢያስረው ምሰሶውን አለምልሞ ቤቷን በበረከት መልቶ ልጅዋም ዕውረ ዓይን ጹቡሰ እግር ነበረ ፈውሶላታል፡፡

     ሁለተኛው ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ዕለት ነው፡፡ የተሠራውም በአባት በእናቱ ቦታ ላይ ነው፡፡ ሥጋውንም ብላቴኖቹ ወደዚያ አፍልሰውት ሕሙማንን ሲፈውስ ሙታንን ሲያስነሳ ይኖር ነበር፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ ሰይጣናዊ ቅንዓት አድሮበት አውህስን አጥፋ ብሎ ላከው፡፡ ቢሄድ ምእመናን ለሥዕሉ መብራት አብርተው ሲሳለሙት አገኘ፡፡ መብራቱን በሰይፍ ቆረጠው፡፡ ሣይታወቀው ሰባራው በራሱ ላይ ወድቆ አቃጠለው፡፡ ሰውነቱ እንደሰነበተ አስከሬን ሸተተ፡፡ ሠራዊቱ በመርከብ ተሳፍረው ይዘውት ሲመለሱ ማዕከለ ባሕር ሲደርሱ ሞተ፡፡ ከባሕሩ ጥለውት ሔደዋል፡፡ እንዲህ ሆነ ብለው ነገሩት፡፡ ሠራዊቱን አስከትሎ ሄደ፡፡ ከዐውደ ምሕረት መንበሩን ዘርግቶ በትዕቢት ተቀምጦ ሳለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቅዱስ ሚካኤል ጋራ መጥቶ ከነመንበሩ ገልብጦታል፡፡ በመንበረ እጄታዎች ነበሩ ሁለት ዘንጎች ዓይኖቹን አውጥተውት ታውሮ ሠራዊቱም ትተውት በአንቀጸ ቤተ ክርስቲያን ከነዳያን ጋር እየለመነ በኃሣር ሞቷል፡፡  

ምንጭ፡ መዝገበ ታሪክ

ኅዳር 6፡ ዕረፍቱ ለቅዱስ ፊልክስ የሮሜ ሊቀ ጳጳስ

የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ክርስቲያኖች ናቸው የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት አስተማሩት የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት እንጦንስም ዲቁና ሾመው ደግሞ የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ዮስጦስም ጠባን ጽድቁንና የቱሩፋትን ደግነት አይቶ ቅስና ሾመው፡፡ ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮናስስ በዐረፉ ጊዜ ይህን አባት ፊልክስን መረጡት በእግዚአብሔርም ፈቃድ በሮም ሀገር ሊቀ ጵጵስና ሾሙት የክርስቶስንም መንጋዎች በመልካም አጠባበቅ ጠበቀ፡፡ ትሩስ ቄሳርም ከሞተ በኋላ ቴድሮስ ቄሳር ነገሠ እርሱም በምእመናን ላይ ታላቅ መከራን አብዝቶ ጭንቅን በሆነ ሥቃዮች አሰቃያቸው፡፡ ብዙዎችም በእርሱ እጅ በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡

ይህም አባት ከዚህ ከሀዲ ታላቅ መከራና ስቃይ ደረሰበት፡ ስለ እርሱም ወደ እግዚአብሔር ማለደ ክብር ይግባውና ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ ይህን ከሀዲ በ2ኛው ዘመነ መንግሥቱ አጠፋው፡፡ ከዚህም በኋላ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ ጊዜ ክርስቲኖችን አብዝቶ ማሰቃየት ጀመረ፡፡ ይህም አባት ፊልክስ የክሪስቲያኖችን ስቃይ እንዳያይ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በዲዮቅልጢያኖስም በመጀመርያው ዘመነ መንግሥቱ ዐረፈ፡፡ ይህ አባት ብዙዎች ድረሳናትንና ተግሳጾችን ደርሷል ስለ ውግዘትና ስለ ቀናች ሃይማኖት ተመላለሱበት አለ እነዚህም ለክርስቲያን ወገን እጅግ የሚጠቅሙ በጎዎች ናቸው፡፡

                                                                    ምንጭ፡ ስንክሳር

ተያያዥ ገጾች

ጥቅስ

‹‹ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› ( ሲራክ 5፡7)

‹‹ፈጥነህ ስማ፤ ቃልን ለመመለስ ግን የታገስክ ሁን›› (ሲራክ 5፡11)

‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ቃሉን አይረሱም›› (ሲራክ 2፡15)

Joomla templates by Joomlashine